1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃውያን ስደተኞች በእስራኤል

ዓርብ፣ ነሐሴ 22 2007

እስራኤል፣ በረሃ ውስጥ በሚገኘው በሆሎት የስደተኞች ማቆያ ማዕከል ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት የሰበሰበቻቸውን አፍሪቃውያን ስደተኞች በዚህ ሳምንት ለቃለች። ሆኖም ወደ ቴላቪቭና ወደ ኤይላት ከተሞች እንዳይገቡ ታግደዋል። ስደተኞችም ሆነ የስደተኞች መብት ተሟጋቾች እርምጃውን አወድሰው ወደ ሁለቱ ከተሞች እንዳይሄዱ መታገዳቸውን ግን ተቃውመዋል።

https://p.dw.com/p/1GNaM
Israel Fluchtlinge in Holot Haftanstalt
ምስል Getty Images/AFP/O. Ziv

[No title]

የእስራኤል መንግሥት ኔጌቭ በረሃ ውስጥ በሚገኘው በሆሎት የስደተኞች ጣቢያ ያስቀመጣቸውን አፍሪቃውያን ስደተኞች መልቀቅ የጀመረው ባለፈው ማክሰኞ ነዉ። በዚሁ ዕለት 750 አፍሪቃውያን ስደተኞች ከመጠለያው ሲወጡ ሌሎች ቁጥራቸው ወደ 600 የሚጠጋ ደግሞ ከትናንት በስተያ ከማዕከሉ ተሰናብተዋል። ስደተኞቹ በዚህ ማዕከል ውስጥ ከአንድ ዓመት በላይ እንዲቆዩ ተደርጓል። ይህ የሆነውም እስራኤል ሕገ-ወጥ የምትላቸውን ስደተኞች ፍርድ ቤት ሳታቀርብ ለ20 ወራት መያዝ የሚያስችላት ሕግ ከአንድ ዓመት በፊት ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ነው። ሆኖም የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት ሕጉን በመሻር፣ ስደተኞቹ በሁለት ሳምንት ውስጥ ከጣቢያው እንዲለቀቁ በወሰነው መሠረት ነው በዚህ ሳምንት ከመጠለያ እንዲወጡ የተደረገው። እርምጃዉ በመብት ተሟጋቾች ተወድሷል። ሆኖም ግን ስደተኞች በተለይ ቴልአቪቭና ኤልያት እንዳይገቡ መታገዳቸውን ተቃውመዋል። ከነዚህም አንዱ እስራኤል ውስጥ የተቋቋመው «ጠበቃ» የተባለው የመብት ተሟጋቹ ድርጅት ኃላፊ አቶ ፈንታሁን አሰፋ ዳዊት ናቸው ። አቶ ፈንታሁን አስተያየታቸውን መስጠት የጀመሩት ከውሳኔው በጎ ጎን በመነሳት ነበር ።ስደተኞቹ ከቴላቪቭና ከኤይላት የታገዱት የሁለቱ ከተሞች ነዋሪዎቹ ስደተኛ እንዲመጣባቸው ባለመፈለጋቸው መሆኑ ተነግሯል። በቴላቪቭ ብቻ ከ30 እስከ 35 ሺህ የሚደርሱ አፍሪቃውያን ስደተኞች እንዳሉ ይገመታል። የከተማዋ ከንቲባ ስደተኞቹ ቴላቪቭን እንዳያጨናንቁ በተለያዩ የእስራኤል ከተሞች ሄደው መሥራት የሚያስችላቸው የሥራ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ሃሳብ አቅርበዋል። አራድ የተባለችው የሌላ ሶስተኛ ከተማ ከንቲባም ስደተኞች ወደ ከተማይቱ እንዳይገቡ እንደሚደረግ አስታውቀዋል። እነዚህ መሰል እገዳዎች በሌሎች ከተሞችስ አያሰጉ ይሆን ?
አፍሪቃውያኑ ስደተኞች በሆሎቱ ማዕከል ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ ነበር የተወሰነው። በዚያም ቆይታቸው ቀን ቀን ከመጠለያው መውጣት ቢፈቀድላቸውም፤ ማታ ደግሞ ተመልሰው መምጣት ይጠበቅባቸው ነበር። አሁን ይሄ ሁሉ ቀርቶ ስደተኞች ከተከለከሉባቸው ከተሞች ውጭ ወደፈለጉበት ቦታ እንዲሄዱ ተፈቅዶላቸዋል። ይህን በበጎ እርምጃነቱ የተቀበሉት አቶ ፈንታሁን በሰብዓዊ መበት ተሟጋቾች ትግልና ግፊት ወደፊት በእስራኤል የስደተኞች ይዞታ እየተሻሻለ ይሄዳል የሚል ተስፋ አላቸዉ።መንግስት እንደሚለው እሥራኤል ውስጥ ሕገ-ወጥ የሚባሉ ስደተኞች ቁጥር 45 ሺህ ይደርሳል። ከነዚህም አብዛኛዎቹ ከኤርትራና ከሱዳን የመጡ ናቸው። ሁለት ሶስተኛው ኤርትራውያን መሆናቸውም ተዘግቧል።

Flüchtlingslager Holot für afrikanische Asylsuchende in Israel
የሆሎቱ የስደተኞች ጣቢያምስል picture-alliance/dpa

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሰ