1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ፣ አውሮጳ እና ፍልሰት

ረቡዕ፣ ኅዳር 8 2008

ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚደረገው ፍልሰት፣ በተለይ ካለፉት ዓመታት ወዲህ የሚታየው ሕገ ወጡ ፍልሰት ትልቅ ችግር ደቀኖዋል። ሁለቱ አህጉራት የፍልሰትን ተግዳሮት በመወጣቱ አኳያ የተለያየ አመለካከት ይዘዋል። ፍልሰት ለሁለቱም ወገኖች ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል የጀርመናውያኑ የፍሪድሪኽ ኤበርት የጥናት ተቋም ከጥ/ጊዜ በፊት ባካሄደው ሴሚናር ጠቁሞዋል።

https://p.dw.com/p/1H81l
Symbolbild Afrika Flüchtlinge
ምስል Getty Images/AFP/M. Turkia

[No title]

ስደተኞች ወደ አውሮጳ በመምጣት ላይ ያሉበት ሁኔታ ያስከተለው ውዝግብ ዓቢይ የመነጋገሪያ ርዕስ ከሆነ ሰንበት ብሎዋል። ለዚሁ ችግር መፍትሔ ለመሻት የአውሮጳ ህብረት ከአንዳንድ አፍሪቃ ሃገራት ጋር ባለፈው ሳምንት በሞልታ ርዕሰ ከተማ ቫሌታ ጉባዔ ማካሄዱ የሚታወስ ነው። ከጉባዔው ቀደም ሲል በአዲስ አበባ የሚገኘው ፍሪድሪኽ ኤበርት የተባለው የጀርመናውያኑ የጥናት ተቋምም፣ ስለዚሁ ጉዳይ ለመወያየት ከደቡባዊ አፍሪቃ አገናኝ ጽሕፈት ቤት እና ከአውሮጳ የልማት ፖሊሲ ማዕከል ጋር ባንድነት ሴሚናር አካሂዶ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ዋነኞቹ ተዋንያን ፣ ማለትም፣ የአውሮጳ ህብረትን እና የአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት፣ እንዲሁም፣ ሌሎች የተመድን እና ሲቭል ማህበረሰቦች ስለፍልሰት አወያይቶዋል። የፍሪድሪኽ ኤበርት ተቋም ኃላፊ ፍሎሪያን ኮኽ የሴሚናሩን ዓላማ እንደሚከተለው አስረድተዋል።

« የዚሁ ስብሰባ ዓላማ እና ጥረት ለቫሌታው ጉባዔ ተጨማሪ ግብዓት ለማቅረብ ነበር። ምክንያቱም፣ አፍሪቃውያኑ እና አውሮጳውያኑ በፍልሰት አኳያ፣ በተግዳሮቱ አኳያ ያላቸው አመለካከት፣ የተለያየ በመሆኑ እነዚህን ሁለት አመለካከቶች ለማቀራረብ ነበር። ከዚህ ባለፈ ደግሞ የአፍሪቃ ህብረት ባለፈው ሰኔ በደቡብ አፍሪቃ ጆሀንስበርግ ከተማ ባካሄደው ጉባዔው ባወጣው መግለጫ ላይ ስላሰፈረው፣ ብሎም፣ አፍሪቃውያኑ መንግሥታት፣ በአገሮቻቸው መካከል ያለውን የሕዝብ እና እቃ ዝውውርን በተመለከተ የሚከተሉትን አሰራር ማሻሻል፣ ፍልሰትን በአካባቢያዊው ውህደት ውስጥ እንዴት ማካተት ስለሚችሉበትም ጉዳይ ለማወያየት ነበር። »

Logo Friedrich-Ebert-Stiftung

የፍሪድሪኽ ኤበርት ተቋም ኃላፊ ፍሎሪያን ኮኽ አክለው እንዳስረዱት፣ በስብሰባው ላይ በተለይ የፍልሰትን በጎ ጎን፣ ማለትም፣ ለአፍሪቃ እና ለአውሮጳ የያዘውን አዎንታዊ ጎን ያጎሉ ሀሳቦች ቀርበዋል።

« የፍልሰት ጥቅም በምዕራባውያቱ እና በዐረባውያቱ ሃገራት የሚኖሩት ዘመዶቻቸውን ለመርዳት ወደ ትውልድ ሃገራቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሪ በዚያ የስራ ቦታ ለመፍጠር፣ ፍልሰትን ለማስቀረት የሚያግዝ አንድ የልማት ዘዴ በመሆን ያገለግላል። እንደሚባለው ይህ የሚላከው ገነዘብ ከልማቱ ርዳታ በሶስት እና በአራት እጥፍ ይበልጣል። ወደ ሃገራቸው የሚመለሱት የያዙት ተጨማሪ የስነ ቴክኒክ እውቀት ም ለትውልድ ሃገር ልማት ድርሻ ያበረክታል። ፈላስያኑን የሚያስተንግዱት ሃገራትም እነዚሁ ከሚከፍሉት ግብር ተጠቃሚ ከመሆናቸውም ሌላ ፣ በተለይ በብዛት በዕድሜ የጠኑ ዜጎች ላሉዋት አውሮጳ ኤኮኖሚ ወጣት የሰው ኃይል ማቅረብ የቻለ አዎንታዊ ሂደት ሆኖ ሊታይ ይችላል። »

Symbolbild Überweisungen nach Afrika
ምስል picture-alliance/Godong

ይህ የፍልሰት አንዱ ጎን ቢሆንም፣ በስደት እና ፍልሰት ላይ የመከረው የቫሌታው ጉባዔ ፍልሰትን፣ በተለይ ግን ሕገ ወጡን ስደት ለመቆጣጠር ይረዳል ያለው አንድ የድርጊት መርሃግብርማውጣቱ ይታወሳል። መርሃግብሩ ልማትን ለማስፋፊያ እና የስራ ቦታ ለመፍጠር የሚረዳ 1,8 ቢልዮን ዩሮ ርዳታ አዘጋጅቶዋል። ፍሎሪያን ኮኽ መርሃግብሩ መውጣቱን ቢያሞግሱም፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ለሚወቀሱት ጨቋኝ ለሚባሉ ኤርትራን እና ሱዳንን ለመሳሰሉ አፍሪቃውያት ሃገራት ገንዘብ ለመስጠት እና አብሮ ለመስራት ማሰቡን አዳጋች ሆኖ ከማየታቸው ሌላ ተግባራዊነቱንም ይጠራጠሩታል። ምክንያቱም ይላሉ፣

«አሁን በወጣው የድርጊት መርሃግብር በቂ ገንዘብ አለመመደቡ፣ በሕጋዊው ፍልሰት ላይ በቂ ውይይት አለመደረጉ፣ በካርቱም ሂደት ላይ የተደረሰውን ስደትን እና ድንበሮችን ለመቆጣጠር ተግባር ለማዋል መታሰቡ ትልቅ ችግር ሆኖ አየዋለሁ። በተለይ ግን አውሮጳውያኑ ፍላጎታቸውን ያጎሉበትን መርሃ ግብሩን ለማስፈፀም የፖለቲካው ፈቃደኝነት መኖሩን ጠብቆ ማየቱ ተገቢ ይሆናል። »

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ