1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ፣ ካሪቢያን፣ ፓስፊክ እና የአውሮጳ ኅብረት

ዓርብ፣ ሰኔ 10 2008

40 ዓመታት የዘለቀው የአፍሪቃ፣ የካሪቢያንና የፓስፊክ ሃገራት እና የአውሮጳ ኅብረት የአጋርነት ስምምነት ዘመን ከ 4 ዓመት በኋላ ያበቃል። ሁለቱ ወገኖች በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም ግንኙነታቸውን ለማደስ ናሚብያ ውስጥ በዚህ ሳምንት መክረዋል።

https://p.dw.com/p/1J8k6
Symbolfoto Afrika EU
ምስል Getty Images/AFP/L. Healing

[No title]

ካለፈው ማክሰኞ እስከ ሐሙስ የተካሄደው የአሁኑ ስብሰባ ሁለቱ ወገኖች በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚያካሂዱት ስብሰባ አንዱ ነው።
የአውሮጳ ፓርላማ እና የ79ኙ በእንግሊዘኛው ምህፃር ACP የሚባሉት የአፍሪቃ፣ የካሪብያንና የፓስፊክ ሃገራት ተወካዮች ከተነጋገሩባቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል የስደተኞች ጉዳይ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ድህነት እና ሌሎችም ጉዳዮች ይገኙበታል። በናሚብያ ዋና ከተማ ዊንድሁክ ውስጥ በዚህ ሳምንት ለሦስት ቀናት የተካሄደው የሁለቱ ወገኖች ስብሰባ ከተያዙት ወቅታዊ አጀንዳዎች በተለየ ትልቅ ቦታ የተሰጠው የኮቶኑው ስምምነት ነበር። በአውሮፓ ህብረት እና በACP መካከል የሚካሄደውን ትብብር የሚቆጣጠረው የኮቶኑው ስምምነት በጎርጎሮሳዊው 2020 የሥራ ዘመኑ ያበቃል ።ከዚያ በኋላ ምን እንደሚከተል ግን አሁን ግልፅ አይደለም። ከጎርጎሮሳዊው 2014 እስከ 2020 የACP ሃገራት ከአውሮፓ ህብረት የልማት እርዳታ 29 ቢሊዮን ዩሮ ማለትም 32.5 ቢሊዮን ዶላር ይሰጣቸዋል ። ከዚሁ ጋር በአውሮጳ ገበያ ውስጥ ቦታ የማግኘታቸው ጉዳይም አለ ። የአውሮጳ ህብረት ከACP ሃገራት ጋር በአጋርነት ለመቀጠል ቢፈልግም ለዚህ ቡድን ግን ቅድሚያ ትኩረት አይሰጥም ። በቅርቡ የአውሮጳ የልማት ፖሊሲ ማዕከል እንዳካሄደው ጥናት ከሆነ የACP ሃገራት ከፍ ያለ ጥቅም ከሚያገኝ ወዳጅ ፣ወደ ዝቅተኛ ወዳጅነት ዝቅ ብለዋል ።የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት መንግሥታት ስደት እና ሽብርን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከአፍሪቃ መሪዎች ጋር በሚያካሂዱት መደበኛ ጉባኤ ላይ በቀጥታ መነጋገር ነው የሚፈልጉት ።ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአውሮጳ እና የአፍሪቃ ህብረት የራሳቸው የድርጊት መርሃ ግብር አላቸው ።ከዚህ በተጨማሪ የአውሮጳ ህብረት ከሰሜን አፍሪቃ ሃገራት ጋር በተጠናል ተደራድሯል ። በአውሮጳ ህብረት ፓርላማ የክርስቲያን ዲሞክራት ህብረት ፓርቲ ተወካይ እንዲሁም የአውሮጳ ፓርላማ እና የACP ሸንጎ የጋራ ኮሚቴ አባል ሚሻኤል ጋህለር በሰጡት አስተያየት እነዚህን የተለያዩ አሰራሮች ማቀናጀቱ ይሻላል ወይስ አይሻልም የሚለው አጠያያቂ ነው ይላሉ ።
«ጥያቄው አሁን ያለውን አወቃቀር ማለትም ከልማት እርዳታ የሚገኘውን ገንዘብ እና ለሰሜን አፍሪቃ አጋርነት የሚውለውን ፋይናንስ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ከአውሮፓ ህብረት በጀት ለፓን አፍሪቃ መርሃ ግብር የሚሰጠውን እርዳታ በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ ማምጣቱ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል አይሆንም የሚለው ነው ። »
በጎርጎሮሳዊው 1975 የአውሮጳ ህብረት እና ACP በሎሜው ስምምነት ወዳጅነት ሲመሰርቱ ግንኑነታቸው ግልፅ ነበር ። የACP ሃገራት ሁሉም ማለት ይቻላል የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት የቀድሞ ቅኝ ግዛቶች ነበሩ ። ከዚያ ወዲህ ግን ሃገራቱ በፖለቲካውም ሆነ በኤኮኖሚው በተለያየ አቅጣጫ እየተጓዙ ነው ። ለምሳሌ ካሪብያን ውስጥ ያለችው ደሴቲቷ ዶሚኒክ ሪፐብሊክ ወደብ አልባ ከሆነችው ከዛምቢያ ጋር ሲነፃጸር ተግዳሮቶቿ የተለዩ ናቸው ።ጋህለር አሁንም ሌላ ጥያቄ ያነሳሉ ።
«የካሪብያን ወይም የፓስፊክ ሃገሮች ከዚህ ቀደም ቅኝ ከመገዛታቸው ውጭ አሁን ከአፍሪቃ ጋር ምን የጋራ ጉዳይ አላቸው ? ከዚያ ይልቅ በተናጠል ከየሃገራቱ ጋር ይበልጥ በተለየ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሥራ ማከናወን አንችልም ነበር ? ።»
የአፍሪቃ ሃገራት ስለወደፊቱ ትብብር ሊወያዩባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ ። ለምሳሌ የኤኮኖሚ አጋርነት ስምምነቶችን መጥቀስ ይቻላል ። የኮቶኑው ስምምነት የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪቃ ሃገራት ምርቶች የነፃ ገበያ እድል እንዲያገኙ ሃሳብ ያቀርባል ። ሆኖም ብዙ የአፍሪቃ ሃገሮች ይህን እየተቃወሙ ነው ። አንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት ቁጥጥር የማይደረግባቸው የአውሮጳ እቃዎች ኤኮኖሚያችንን ሊያደቅ ይችላል ብለው ይፈራሉ ።እቃዎች ከቀረጥ ነጻ መግባታቸውም የበጀት ገቢን ያሳንሳል ።ይሁንና በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት በዚህ ባይስማሙም የአውሮጳ ህብረት ግን ይህ ስምምነት ውሳኔ እንዲያገኝ ግፊት አድርጓል ።

Malta EU Afrika Gipfel in Valetta
ምስል Reuters/D. Zammit Lupi
Infografik Gruppe der afrikanischen, karibischen und pazifischen Staaten Englisch