1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ፣ የዕድገት ማቆልቆልና ድህነት

ረቡዕ፣ ግንቦት 12 2001

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ በጅምሩ አፍሪቃን አሁን በሚታየው መጠን ከባድ ፈተና ላይ ይጥላል ብሎ ያሰበ ብዙ አልነበረም። አፍሪቃና ባንኮቿ ከዓለም የፊናንስ ገበዮች ብዙም ያልተሳሰሩ በመሆናቸው ችግሩ ለክፍለ-ዓለሚቱ የዕድገት ዕርምጃ ያን ያህል መሰናክል ሊሆን አይችልም ተብሎ ነበር የታመነው።

https://p.dw.com/p/HuBD
ምስል AP Graphics/DW

ግን አሁን ቀውሱ በአፍሪቃ ኤኮኖሚ ላይ ያለው ተጽዕኖ እጅግ ከባድ እየሆነ መሄዱ በጣሙን ግልጽ ነው። በተለይ ከሣሃራ በስተደቡብ ለሚገኘው የድሃ-ድሃ የሆነ ሰፊ ሕዝብ ችግሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆን ይዟል። ድሀነትን እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ በግማሽ ለመቀነስ የታለመለት የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ግብም የሩቅ ሕልም እየሆነ ነው። በዓለም ገበያ ላይ የጥሬ ሃብት ዋጋ መውደቅ፣ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችና የባንኮች ቁጥብነት፤ እንዲሁም በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች የሚላከው ገንዘብ ማቆልቆል ተጽዕኖ አፍሪቃን ዘግየት ብሎም ቢሆን እየተሰማት ነው።

ችግሩ በጅምሩ እንደታሰበው በበለጸገው ዓለም ብቻ ተወስኖ አልቀረም። በየጊዜው አንዴ ናዳ፣ ሌላ ጊዜም ነውጽ ወይም ማዕበል የሚል ስያሜ በየመልኩ ሲሰጠው የቆየው ዓለምን ከሰላሣኛቹ ዓመታት ወዲህ አቻ ባልታየለት ሁኔታ በከፋ መጠን የመታው የፊናንስ ቀውስ ቀደም ሲል አንዳንዶች እንዳሉት አፍሪቃን ተሻግሮ አላለፈም። አፍሪቃ በፊናንሱ ገበዮች ንግድ ውስጥ ጠልቃ ባለመግባቷ ችግሩ ሩቅ ነው፤ አይሰማትም ያሉት ምዕራባውያን የኤኮኖሚ ጠበብት ብቻ አልነበሩም። በጊዜው ለምሳሌ እንደ ካሜሩኗ የፊናንስ ሚኒስትር እንደ ኤሢሚ ሜንዬ ሁሉ በርካታ የአፍሪቃ ባለሥልጣናትም ይህንኑ ነበር ያሰቡት።

“ይህ ማዕበል በአናታችን ላይ ከንፎ የሚያልፍ ነገር ነው። ምክንያቱም ባንኮቻችን በዓለም ከፍተኛ የፊናንስ ገበዮች ላይ ተሳታፊዎች አይደሉም። በኒውዮርክ ወይም በለንደን መዋዕለ-ነዋይ አያደርጉም”

ለነገሩ የአፍሪቃ ባንኮች በአብዛኛው ለብሄራዊ ደምበኞች ብድር በመስጠት የሚነግዱ ሲሆን በውጭ የፊናንስ ንግድ የሚሳተፉት ከስንት አንዴ ቢሆን ነው። ለዚህም ነበር የዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ አሻራ በመጀመሪያ በክፍለ-ዓለሚቱ ጎልቶ ያልታየው። ግን ማዕበል የሚመጣው ነውጽን ተከትሎ ነውና የኋላ ኋላ ተጽዕኖው ሲስፋፋ በዚህ በያዝነው ዓመት ደግሞ ሁኔታው እንዲያውም እየከፋ መቀጠሉ የማይቀር ነው። የበለጸጉት መንግሥታት የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ኦ.ኢ.ሲ.ዲ. በቅርቡ ባወጣው ዓመታዊ ዘገባ የአፍሪቃ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት በያዝነው 2009 በግማሽ እንደሚቀንስ ነበር የተነበየው።

ነዳጅ ዘይት ወይም ሌላ የተፈጥሮ ጸጋ ያላቸው የአፍሪቃ ሃገራት ባለፉት ዓመታት በምርት ዋጋ ማደግ ሳቢያ ተጠቃሚዎች ሆነው ነበር። አሁን ግን በምርቱ ዋጋ መልሶ ማቆልቆልና የፊናንሱ ቀውስ በተዘዋሪ መልክ ባስከተለው አስቸጋሪ ሁኔታ የተነሣ የኤኮኖሚ ዕድገታቸው እየተሰናከለ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ጥር ወር ባወጣው የዓለም ኤኮኖሚ ሁኔታና የወደፊቱ ሂደት ዘገባው የአፍሪቃ አገሮች ዕድገት በዚህ ዓመት ከ 0,1 በመቶ በላይ እንደማያልፍ ነበር። ዕድገት ጨርሶ አይጠበቅም ማለት ነው።

አሃዙ ከ 2007 ዓ.ም. 6 ከመቶና ከተካታዩ 2008 5,1 ከመቶ አማካይ የዕድገት መጠን እንጻር ተሥፋ አስቆራጭ ሲሆን በብዙ የአፍሪቃ አገሮች በጀት ላይ ብርቱ ተጽዕኖ ይኖረዋል። የተወሰኑት እንዲያውም ከአሁኑ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት። የለየለት ብሄራዊ ክስረት ያሰጋቸውም አይታጡም። በአጠቃላይ የከፋ ጊዜ ከፊታቸው ከተደቀነባቸው አገሮች መካከል ለምሳሌ ናይጄሪያም ትገኝበታለች። የአገሪቱ የፊናንስ ሚኒስትር ማንሱር ሙህታር እንደሚሉት ችግሩ እንዳይባባስ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸገው ዓለም ኤኮኖሚ ማገገም ወሣኝነት አለው።

“በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉት አገሮች ዕድገት ገሃድ ሊሆን ካልቻለ የኛም ምርት ተፈላጊነት ይብስ እየወደቀ ነው የሚሄደው። የውጭ ንግዳችን፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም መንግሥታዊ ገቢያችን ያቆለቁላል ማለት ነው”

ናይጄሪያ ከ 80 በመቶ በላይ በጀቷን የምትሸፍነው ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ በምታገኘው ገንዘብ ነው። ግን በቀውስ ወቅት የኤነርጂው ጥም ጋብ ብሏል። እናም ከአንድ ዓመት ወዲህ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ሰባ ከመቶ ገደማ ነው የቀነሰው። አገሪቱ እንግዲህ ከወዲሁ በብዙ ሚሊያርድ ዶላር የሚቆጠር ገቢ አጥታለች ማለት ነው። የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችም በቀውሱ ሳቢያ ብዙ ፕሮዤዎቻቸውን እየዘጉ በመሄድ ላይ ናቸው። ባንኮችም እንዲሁ ጥንቁቅነት ያበዛሉ።
በዚሁ የተነሣ እንደ ናይጄሪያ ላሉ ታዳጊ አገሮች ብድር ማግኘቱ ከባድ ነው የሚሆነው፤ የሆነውም። በዚሁ አጠቃላይ ሁኔታ የተነሣ የናይጄሪያ ባንኮች አክሢዮኖች ወድቀዋል፤ የአገሪቱ ብሄራዊ ምንዛሪ የናይራም ዋጋ እያቆለቆለ ነው። ይህ ደግሞ ከጎረቤቲቱ ቤኒን የኮቶኑ ወደብ አሮጌ አውቶሞቢሎችን እያስገባ በመሸጥ የሚተዳደረውን ኢብራሂም ኦቤሮንጋን የመሳሰሉ አያሌ ነጋዴዎችን ክፉኛ መጉዳቱ አልቀረም።

“ከአራት ከአምሥት ወራት ወዲህ ገበያው ሙሉ በሙሉ በቀውስ ተመትቷል። በንግዱ በመቀጠላችን ራሱ ልንደሰት ይገባናል። እዚህ ኮቶኑ ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ነው የሚከፈለው። በዶላር፣ በኤውሮ! እና የናይጄሪያ ናይራ ከነዚህ ምንዛሪዎች አንጻር ውድቀት ደርሶበታል። የመለዋወጫው ተመን ከፍተኛ ነው። እጅግ ከፍተኛ ነው”

ለነገሩ ናይጄሪያ እንደ አውሮፓ ሁሉ በደጉ ጊዜ ያከማቸችውን አቅም በመጠቀም ኤኮኖሚዋን መልሶ ለማነቃቃትና አገሪቱን ከከፋው የፊናንስ ቀውስ ተጽዕኖ ለመሰወር መጣሯ አልቀረም። ያለፉት ዓመታት ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ካዝናዋን ሞልቷል። አገሪቱ በመሠረቱ በዓለም ገበያ ዋጋ ማቆልቆል የተነሣ ከባድ ቀውስ ላይ ከወደቀችበት ከ 80ኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ በተሻለ ሁኔታ ላይ ነው የምትገኘው። የነዳጅ ዘይት አምራችና ሻጭ አገሮች ድርጅት ኦፔክም ባለፉት ወራት የነዳጁን ዋጋ መልሶ ለማሳደግ ምርቱን ቀነስ አድርጓል። ይሁን እንጂ ዕርምጃው ፍሬ ሰጥቶ ድህነትን ለመቀነስ መርዳቱን የዘርፉ አዋቂዎች ይጠራጠራሉ።

ድህነትን በመታገሉ ረገድ አብዛኛውን ጊዜ ጭብጥ ዕርዳታ ሆኖ የሚታየው በውጭው ዓለም የሚኖሩ አፍሪቃውያን ዘመዶቻቸውን ለመደገፍ ወደ ምንጭ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ ነው። ሤኔጋልን እንደ ምሳሌ ብንወስድ በውጭ የሚኖሩ ተወላጆቿ ባለፈው ዓመት ወደ አገር የላኩት ገንዘብ 850 ሚሊዮን ኤውሮ ገደማ ይጠጋ ነበር። የብዙዎች ሕልውና በዚህ ድጋፍ ላይ ሲበዛ ጥገኛ ነው። ይህ ገንዘብ ባይኖር በአገሪቱ ላይ ከባድ ቀውስ እንደሚከተል ማሰቡ አያዳግትም። ሌላው ቀርቶ ለብዙዎች የሚቀመስ ነገር እንኳ ባልተገኘ ነበር። የኢትዮጵያም ሁኔታ ከዚህ እምብዛም የተለየ አይደለም። በውጭ የሚኖሩ የአገሪቱ ተወላጆች የሚያስገቡት ገንዘብ ብዙ ቀዳዳዎችን የሚሸፍን ነው።

ግን ችግሩ ዕርዳታው በወቅቱ በአስካሁኑ መጠን መቀጠል በሚችልበት ሁኔታ ላይ አይገኘም። ሤኔጋልን በተመለከተ በዓለምአቀፉ የምንዛሪ ድርጅት በአይ.ኤፍ.ኤም. ስሌት ከውጭ የሚላከው ገንዘብ በዚህ በያዝነው ዓመት ሲሶ ያህል መቀነሱ የማይቀር ነው። ለዚህም ምክንያቱ ወደ ምዕራቡ ዓለም የፈለሱት ገንዘብ ላኪዎች ራሳቸው ሥራ-አጥ እየሆኑ መሄዳቸው ነው። ከውጭ የሚላከው ገንዘብና የመንግሥት ገቢ እየቀነሰ መሄድ፣ የመዋዕለ-ነዋይ ማቆልቆልና የኑሮ ውድነት መክፋት በሤኔጋል ብቻ ሣይሆን በርከት ባሉ የአፍሪቃ አገሮች የወደፊቱን ዕድገት የመነመነ ያደርገዋል።
የኤኮኖሚ ጠበብት በሚያስቀምጡት መስፈርት መሠረት በአፍሪቃ ዕርምጃ ታይቷል ለማለት ቢያንስ 5 ከመቶ ዓመታዊ ዕድገት ያስፈልጋል። ከዚህ በታች ያለው ሁሉ ግን ድህነትን በመታገሉ ረገድ የረባ ለውጥ ሊያስከትል አይችልም። የወቅቱ ግምት ደግሞ እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ የአይ,ኤም.ኤፍ. አስተዳዳሪ ዶሚኒክ-ሽትራውስ ካን እንዳሉት የሚከተለው የድሃ-ድሃ የሚባለው ሕዝብ ቁጥር መጨመር ነው።

“አፍሪቃ ውስጥ ባለፉት ዓመታት አንዳንድ ስኬቶች መመዝገባቸው አልቀረም። የኤኮኖሚው ዕድገት ቀደም ካሉት ዓመታት ሲነጻጸር በጣሙን ከፍተኛ ነበር። ግን ይህ ዕርምጃ በቀውሱ፤ አፍሪቃ ሃላፊነት በሌለባት ቀውስ የተነሣ ከንቱ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ባለፉት ዓመታት አፍሪቃ ውስጥ በከባድ ጥረት የተገኘው ስኬት ቀጣይ እንዲሆን ማድረጉ የሃብታም መንግሥታት ሃላፊነት ነው”

ለማንኛውም የወቅቱን የፊናንስ ቀውስ በመታገሉ ረገድ የአፍሪቃ መንግሥታት ይበልጡን በዋሺንግተኑ ዓለምአቀፍ የምንዛሪ ድርጅት በ አይ.ኤም.ኤፍ. ላይ ማተኮራቸው ግድ የሚሆን ነው የሚመስለው። በድን-ሃያ በሚል ስብሰብ በቅርቡ በለንደን የዓለም የፊናንስ ጉባዔ ያካሄዱት በኢንዱስትሪ ልማት የተራመዱ መንግሥታት ብሄራዊ ኤኮኖሚያቸው በመዋዠቅ ላይ ላሉ አገሮች ዕርዳታቸውን ከፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ይህም የሚቀናበረው በዋሺንግተኑ የምንዛሪ ድርጅት ነው። ለግንዛቤ ታዳጊዎቹ አገሮች ብድር ለማግኘት ብቁ ይባሉ አይባሉ የዚሁ ድርጅት ዕይታ ወሣኝነት አለው።

እርግጥ አይ.ኤም.ኤፍ. ለዕርዳታው ጥብቅ የጥገና ለውጦችን ቅድመ-ግዴታ ሲያደርግ በመቆየቱ ውሣኔዎቹ በብዙዎቹ የአፍሪቃ አገሮች ተወዳጅ እንዳላደረጉት ግልጽ ነው። አሁን በፊናንሱ ቀውስ ወቅት ደግሞ ሁኔታው ብሶ እንደሆን እንጂ ዓመኔታ እየሰፈነ ነው ለማለት አያስደፍርም። ብዙዎች አፍሪቃውያን መንግሥታት በድርጅቱ ለዓመታት የበጀት ቁጠባ ዲሲፕሊን እንዲያሳዩ ሲገፉ ከቆዩ በኋላ በአንጻሩ የበለጸጉት መንግሥታት ለራሳቸው ኤኮኖሚ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲያፈሱ መመልከቱ አልተዋጠላቸውም። አፍሪቃ በፊናንሱ ቀውስ ተጎጂ ሆና መቀጠሏ የማይቀር ነገር ነው። ብዙዎቹ አገሮች ዛሬም በዓለም ገበያ ዋጋ ላይ ጥገኞች ናቸው፤ ብሄራዊ ኤኮኖሚያቸውም ለቀውስ የተጋለጠ ሆኖ ይቀጥላል።
በአጠቃላይ የብዙዎች ታዳጊ፤ በተለይም ከሣሃራ በሰደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ አገሮች ሁኔታ በጣሙን የሚያሳስብ ነው። ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ለመንስዔው ተጠያቂ ባይሆኑም የወደፊት የዕድገት ዕድላቸውን መጫን ይዟል። ከዚህ አንጻር ድሀነትና ረሃብን መቀነሱን የሚጠቀልሉት የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ልማት ግቦች ያለ ውጭ ዕርዳታ ጨርሶ የሚደረስባቸው ሊሆኑ አይችሉም። ለነገሩ የሚሌኒየሙ ዕቅድ ገቢርነት ወይም ስኬት የፊናንሱ ቀውስ ሳይከሰትም በብዙዎች የአፍሪቃ አገሮች አጠያያቂ ሆኖ የቆየ ጉዳይ ነው። አንዳንድ ታዛቢዎች እንዲያውም ዕቅዱ ከመደበኛ ጊዜው አሥር ዓመት ያህል ተጨምሮለት እንኳ ቢሳካ ትልቅ ነገር ነው ማለት ጀምረዋል።

DW/RTR

መስፍን መኮንን/ሂሩት መለሰ