1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ፤ የዕድገት ስልትና የግል መዋዕለ-ነዋይ

ሐሙስ፣ ሰኔ 1 1998

የአፍሪቃን ልማት ለማፋጠን፤ በዓለም ሕብረተሰብ ድርጅት የሚሌኒየም ግብ መሠረትም ድህነትን ለመቀነስ የተጣለውን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ መንግሥታዊ ዕርዳታ ብቻውን አይበቃም የሚለው አስተሳሰብ በወቅቱ በጠበብት ዘንድ የተስፋፋ ጉዳይ ነው። በአብዛኞቹ አመለካከት የግሉ ኤኮኖሚ ዘርፍ ተሳትፎ ወሣኝነት አለው፤ መጠናከርም ይኖርበታል።

https://p.dw.com/p/E0di
የአፍሪቃ የልማት ዕጦት ገጽታ
የአፍሪቃ የልማት ዕጦት ገጽታምስል dpa

የ 37 የአፍሪቃ መንግሥታት ሚኒስትሮችና የአሜሪካ ተጠሪዎች በዚሁ መንፈስ ሰሞኑን ዋሺንግተን ላይ ተሰብስበው ሲነጋገሩ ሰንብተዋል። የስብሰባው ዓላማ የግሉን ዘርፍ መዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት ማዳበር የሚረዳ ስልትን ገቢር ማድረግና ንግድን ማጠናከር ነው። ዛሬ የሚጠናቀቀው ስብሰባ ርዕስ ያደረገው የአፍሪቃን ልማት በግሉ ዘርፍ መዋዕለ-ነዋይ ማሳደጉንና ንግድን ማፋጠኑን ነው። በአስተናጋጅነት ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮንዶሌሣ ራይስ ናቸው።

በአሕጽሮት AGOA በመባል የሚታወቀው የአሜሪካና ከሣሃራ በስተደቡብ ያለው የአፍሪቃ ክፍል የንግድና የኤኮኖሚ ትብብር መድረክ ዘንድሮ ዓመታዊ ጉባዔውን ሲያካሂድ ለአምሥተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት የአፍሪቃ ጉዳይ ምክትል ባለሥልጣን ሊንዳ ግሪንፊልድ እንዳስረዱት ንግድና የኤኮኖሚ ልማትን ለማዳበር አዳዲስ ፖሊሲዎችን ለማስፈን በሚኒስትሮች ደረጃ ከሚደረገው ንግግር ባሻገር አንድ የግሉ ዘርፍ መድረክም ኩባንያዎች አዳዲስ ገበዮችና ሸሪኮች የሚያገኙበትንና ትርፋቸውን ማሳደግ የሚችሉበትን ሁኔታ ለማውጣጣት ይሞክራል።

በመድረኩ ላይ ከሚሳተፉት አገሮች መካከል ደቡብ አፍሪቃን፣ ኢትዮጵያን፣ ጋናን፣ ኬንያንና ሞዛምቢክን፤ እንዲሁም ናይጄሪያን፣ ሤኔጋልን፣ ታንዛኒያንና ኡጋንዳን የመሳሰሉት ይገኙበታል። መድረኩ የተከፈተው “ The Africa Growth and Opportunity Act” የተሰኘውን የአሜሪካ ብሄራዊ ሸንጎ በ 2000 ዓ.ም. አጽድቆት የነበረውን አፍሪቃን የልማት ዕድል ለመስጠት የተወጠነ ሕግ ተከትሎ ነው። ውጥኑ አፍሪቃን ከተረጂነት ባሻገር ኤኮኖሚዋን ከዓለም የንግድ ሥርዓት ጋር በማስተሳሰሩም ያልማል።
ሊንዳ ግሪንፊልድ ለጋዜጠኞች እንዳስረዱት መድረኩ በአፍሪቃና በአሜሪካ መካከል ያለውን የሁለት ወገን ንግድ ለማሳደግና የምርቶቹንም ዓይነት ለማበራከት በጣሙን ነው የረዳው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የሁለት ወገኑ የንግድ ልውውጥ ባለፈው 2005 ዓ.ም. ቀደም ካለው ሲነጻጸር 37 በመቶ በመጨመር ወደ 61 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ከፍ ብሎ ነበር። የ AGOA መድረክ አሁን ወደ አሜሪካ ገበዮች የሚዘልቁትን ምርቶች ከ 6,400 በላይ አሳድጎ ነው የሚገኘው። የአሜሪካን ቴክኒካዊ ዕርዳታም አብሮ ያራምዳል።

የጨርቃ-ጨርቅ ምርትን በተመለከተ ከ 37ቱ በመድረኩ የታቀፉ የአፍሪቃ መንግሥታት ባሻገር ተጨማሪ 25 አገሮችም ከአሜሪካ በኩል የተለየ የቀረጥ አስተያየት ይደረግላቸዋል። ዋሺንግተን ይህን የምታደርገው ሕገ-ወጥ ንግድን ለመቋቋም ነው። በዚሁ ውጥ’ን መሠረት የተጠቀሱት 25 አገሮች በተወሰነ መጠን ወይም ኮታ ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ ሆነው ወደ አሜሪካ እንዲያስገቡ ይፈቀድላቸዋል።

የዘንድሮው መድረክ በተለይ ለአፍሪቃ ዕድገት የውጭ መንግሥታት ዕርዳታ ብቻውን የሚበቃ አለመሆኑን ያስረገጠ ነው። የአፍሪቃ ልማት ዕውነተኛ መንኮራኩር፤ ክፍለ-ዓለሚቱ ሙሉ ሃይሏን ለመጠቀም የምትበቃውም ራሷ የግሉን ዘርፍ በማጠናከር የበኩሏን ጥረት ስታደርግ ብቻ መሆኑ ከመቼውም በላይ ነው የታመነበት። የአሜሪካ የአፍሪቃ ጉዳይ ባለሥልጣን ሊንዳ ግሪንፊልድ በጉዳዩ ሲናገሩ አፍሪቃ ከተቀረው ዓለም ወደ ኋላ የቀረችበት ቁልፍ ዘርፍ የንግድ ይዞታዋ ነው ብለዋል።

አብዛኞቹ የአፍሪቃ አገሮች ዛሬ ወደ አሜሪካ ለሚሸጧቸው በርከት ያሉ ምርቶቻቸው የሚያገኙት ክፍያ እጅግ ዝቅተኛ ነው። ስለዚህም ለአፍሪቃ ዕድገት ቁልፉ በመጀመሪያ ደረጃ የራሳቸው አምራቾች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በውስጣቸው አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ ይሆናል። አሜሪካ በ 2005 ከ 37ቱ የ AGOA አገሮች ያስገባችው ምርት 38.1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ነበር።
ይህም ቀደም ካለው ዓመት 44 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ባለሥልጣን ጄንዳይ ፍሬዘር ይህ በነዳጅ ዘይት ብቻ ሣይወሰን ብዙ ምርቶችን የጠቀለለው ንግድ አስደናቂ ዕርምጃ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩልም አሜሪካ በዚያው ዓመት ያሻገረችው ምርት በጨርቃ-ጨርቅ ደረጃ ዝቅ ቢልም በዕርሻ ውጤቶች፣ በምርት መኪናዎችና በኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች በኩል ዕድገት የታየበት ነበር።

ይህን በዚሁ ተወት አድርገን በሁለተኛው የልማት ርዕሳችን እናተኩርና የአውሮፓ ሕብረት በ 77 የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሢፊክ አካባቢ አገሮች የሚካሄዱ የልማት ፕሮዤዎችን ወደፊት በ 22 ሚሊያርድ ኤውሮ ዕርዳታ ለመደገፍ ወስኗል። የሕብረቱ ኮሚሢዮን ሰሞኑን ብራስልስ ላይ እንዳስታወቀው ዕርዳታው ከ 2008 እስከ 2013 በሚዘልቁት አምሥት ዓመታት ውስጥ የሚቀርብ ነው። ገንዘቡንም ሆነ ይሄው በሥራ ላይ የሚውልበትን ሁኔታ በተመለከተ የሕብረቱና የ ACP ሃገራት ተጠሪዎች ባለፈው ሣምንት ፓፑዋ-ኒውጊኔያ ላይ ተገናኝተው ተነጋግረዋል።

በዓመታዊው የአውሮፓ ሕብረትና የአፍሪቃ፣ ካራይብ ፓሢፊክ አገሮች ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የተሳተፉት የታዳጊው ዓለም ሚኒስትሮች በሰፊው የገንዘብ አቅርቦት እጅግ መደሰታችው አልቀረም። የሕብረቱ ኮሚሢዮን አፈ-ቀላጤ አማዴዉ አልታፋይ እንደገለጹት ብራስልስ ለአፍሪቃ፣ ካራይብና ፓሢፊክ አገሮች፤ እንዲሁም ለዛሬዎቹ የባሕር ማዶ ግዛቶቿ የመደበችውን ዕርዳታ በሚቀጥሉት ዓመታት ለአሥር የአውሮፓ የልማት ገንዘብ ተቋማት ለማቅረብ ተዘጋጅታለች። ከዚሁ አብዛኛውን ገንዘብ፤ ሃያ ሚሊያርዱን ኤውሮ የሚያገኙት ደግሞ 77ቱ የ ACP ማለት የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሢፊክ አካባቢ አገሮች ናቸው።

ሃያ ሚሊያርዱ ለ ACP አገሮች የተወጠነ ዕርዳታ ቀድሞ ለዘጠኝ የልማት ዕርምጃዎች ይሰጥ ከነበረው 35 በመቶ ከፍ ያለ መሆኑ ነው። አሃዙ ለታዳጊዎቹ አገሮች ከዚህ ቀደም ያልነበረ የፖለቲካ ተሳትፎን ስለሚያስከትል ታላቅ ክብደት ይኖረዋል አልታፋይ እንደተናገሩት።

የአውሮፓ ሕብረት ወደፊት ለ ACP አገሮች የሚሰጠውን ዓመታዊ የልማት ዕርዳታው እስካሁን ከነበረው 2,7 ወደ 3,6 ሚሊያርድ ኤውሮ ከፍ ለማድረግ ይፈልጋል። ይሄው ለልማት ፕሮዤዎች የሚቀርበው ገንዘብ ከመደበኛው የአውሮፓ ሕብረት በጀት ውጭ መሆኑ ነው። ዘጠነኛው የልማት ፕሮዤ ዕርዳታ በሚቀጥለው 2007 ዓ.ም. መጨረሻ የሚያበቃ ሲሆን የሕብረቱ ዓባል መንግሥታት በአሥረኛው የልማት ፕሮዤ የፊናንስ አቅርቦት ለመስማማት ረጅም ጊዜ ወስዶባቸዋል።

የአውሮፓው የልማት ዕርዳታ ኮሜሣር ሉዊስ ሚሼል እንዳስረዱት አሁን በታቀደው አሥረኛ በጀት ሕብረቱና ACP የቀድሞዎቹ የአውሮፓ ቅኝ-ግዛቶች ካስቀመጡት የዕድገት ግብ ለመድረስ ሁኔታው ተመቻችቶላቸዋል። ከጥረቱ ዋነኛውም በተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ መሠረት ድህነትን መታገል፣ በጎ አስተዳደርን ማስፈንና የአካባቢ ተራድኦን ማሻሻል ነው። የሕብረቱ ኮሚሢዮን አፈ-ቀላጤ አማዴዉ አልታፋይ እንደሚሉት የዕርዳታው ገንዘብ ለ 77ቱ የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሢፊክ አካባቢ መንግሥታት አቅድ ባለውና ጠቃሚ በሆነ መንገድ መከፋፈል ይኖርበታል። የገንዘብ ክፍፍሉ በያንዳንዱ አገርና አካባቢ የወደፊት ጭብት ዕቅድ ላይ በመመስረት መከናወኑ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ኮሜሣር ሚሼል ዕቅዶቹን ለማዳበር የተለያዩ የአካባቢ አውደ-ጥናቶችን እንደሚያካሂዱ ነው የተነገረው።

የአውሮፓ ሕብረት ከዚሁ ከልማት ፕሮዤው ሌላ ከ 77ቱ ታዳጊ አገሮች ጋር የሽርክና ውል ለማስፈንም ይደራደራል። ዓላማው በተለይም ለታዳጊዎቹ አገሮች የንግድ ሁኔታዎችን ማቃለል፣ ወደ ሕብረቱ ገበዮች በቀላሉ የሚዘልቁበትን ሁኔታ ማሻሻልና የውስጣቸውንም የንግድ ግንኙነት ማጠናከር ነው። ሕብረቱ ከአፍሪቃ መንግሥታት ጋር ወደ አውሮፓ በሚደረገው ፈለሣ ጉዳይ ላይም ይነጋገራል። በወቅቱ በስፓኝና በኢጣሊያ በኩል ወደ አውሮፓ ለመዝለቅ የሚፈልጉት አፍሪቃውያን ፈለሣ እየተጠናከረ መምጣቱ የሚታወቅ ነው። በረጅም ጊዜ በኤኮኖሚ ምክንያቶች የሚደረገውን ስደት በታዳጊዎቹ አገሮች ያለውን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል የማያጓጓ ለማድረግ ይታሰባል።

የሆነው ሆኖ የአውሮፓ ሕብረት በቀድሞ ቅኝ-ግዛቶችም ሆነ ሌሎች ታዳጊ አገሮች ልማትን ለማዳበር የያዘው ውጥን ፍቱን እንዲሆን በነዚሁ አካባቢዎች ድህነትን በእርግጥ ለመቀነስ የሚያበቃ የኤኮኖሚ ሥርዓት፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ በጎ አስተዳደር ዕውን መሆኑ ወሣኝ ነው። በዚህ በኩል ተገቢው ግፊት ይደረጋል ወይ? ዋናው ጥያቄ ይህ ነው። ባለፈው ዓመት በስኮትላንድ ግሌንኢግልስ ስምንቱ ሃያላን መንግሥታት የ G-8 መሪዎች ባደረጉት የዕዳ ምሕረት መስፈርት፤ ከዓለም ባን’ክ ፓሊሲ አንጻርም ቃል ገቢር ሲሆን አይታይም። መስፈርቱ በራስ ጥቅም ላይ ተመስርቶ የሚተረጎም ነው የሚመስለው።

ይህ አንዱ ችግር ሲሆን በዓለም ንግድ ላይም ታዳጊ አገሮች በሚገባ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ለውጥ እንዲሰፍን ተሃድሶ ለማድረግ አልተቻለም። አሁን ያለው ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ሥርዓት ለአንድ ወገን ጥቅም ያደላ፤ ፍትሃዊነት የጎደለው ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ታዳጊ አገሮች በዓለም ገበዮች ላይ ተገቢ ድርሻቸውን ማግኘት እስካልቻሉና በሌላ በኩልም በበለጸጉት መንግሥታት የልማት ፖሊሲ አኳያ የድሆች ሕዝቦችን መብትና የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽል በጎ አስተዳደር መስፈኑ የማያወላውል የዕርዳታ ቅድመ-ግዴታ እስካልሆነ ድረስ ድህነትን ለመቀነስ ይቻላል ብሎ ማሰቡ ዘበት ነው።