1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍ በፈቱበት ቋንቋ ስደተኞች መረጃ ሲያገኙ

ዓርብ፣ ጥቅምት 21 2007

ኢትዮ -ኮሎኝ የተባለው የስፖርት እና የባህል ማህበር በኮሎኝ ከተማ ከአንድ የስደተኞች ምክር መስጫ ማዕከል ጋር በመተባበር የብዙ ስደተኞችን ጥያቄ የሚመልስ ድረ ገፅ በአማርኛ ተርጉሞ ለስደተኞች አቅርቧል። ስለዚሁ ድረ ገፅ በዛሬው የወጣቶች ዓለም እናወራለን።

https://p.dw.com/p/1Dedl
Verein - Ethio-Cologne Sport und Kultur e.V.
ምስል Ethio-Cologne Sport und Kultur e.V.

በሺ የሚቆጠሩ የአፍሪቃ ስደተኞች ከአፍሪቃ በስተ ሰሜን ወደምትገኘው አህጉር አውሮፓ፤ ለተሻለ እድልና ህይወት ሲሉ ተሰደዋል። በተለይ በዚህ በመገባደድ ላይ ባለው የጎርጎሮሲያኑ 2014 ዓ ም ከመቼውም በላይ ስደተኞች አውሮፓ ገብተዋል። በጀርመን ብቻ በ9 ወር ጊዜ ውስጥ 136 000 ስደተኞች ተገን ጠይቀዋል። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ስደተኞች ከሶርያ ቢሆኑም ቁጥራቸው አናሳ የማይባል አፍሪቃውያን ስደተኞች በተለይም ከኤርትራ እና ናይጄሪያ ጀርመን ገብተዋል። በርካታ ስደተኞች አደገኛውን እና ፈተና የተሞላበትን ጉዞ አልፈው ጀርመን ሲደርሱ ፤ ጉዞዋቸው የተጠናቀቀ ቢመስልም፤ ጥገኝነት መጠየቅ እና ከጥገኝነት አሰራሩ ጋር የተያያዘ ረዥም ጉዞ ይጠብቃቸዋል። እያንዳንዱ ስደተኛ ተገን ለመጠየቅ ለቃለ መጠይቅ በሚቀርብበት ጊዜ በአስተርጓሚ የመመለስ መብት አለው። ነገር ግን አዲስ ስደተኞች፤ በተለይም ከኢትዮጵያ ወደ ጀርመን ሲመጡ ስለ መብት እና ግዴታዎች የሚረዱት በከተማው የሚኖሩ ኢትዮጵያንን ጠይቀው ነው። ከቅርብ ጊዜ አንስቶ ግን ቢያንስ በኮሎኝ ከተማ እና አካባቢዋ የሚገኙ ስደተኞች የምክር አገልግሎቱን ወይንም ቅድመ ጥያቄያቸውን በአማርኛ ቋንቋ የሚያገኙበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ኢትዮ -ኮሎኝ የተባለው የስፖርት እና የባህል ማህበር በኮሎኝ ከተማ ከአንድ የስደተኞች ምክር መስጫ ማዕከል ጋር በመተባበር በአማርኛ ቋንቋ ተርጉም ስላቀረበው ድረ ገፅ የማህበሩ ሊቀመንበር ተስፋዬ አበበ ገልፆልናል።

ዘመድ እና የሚያውቁት ሰው የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ጀርመን ሲመጡ በመጀመሪያ ሰው ለመተዋወቅ የሚሞክሩት ወደ ሀይማኖት ተቋማት እና ሌሎች የሀገራቸው ማሕበራትን በማፈላለግ ነው። ስለሆነም ወደ ኢትዮ- ኮሎኝ ማህበር ያመሩ ኢትዮጵያውያንም አልጠፉም። ከቅርብ ጊዜ አንስቶ የዚህ ማህበር አባል የሆነው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ አቤል ታደሰ ይባላል። ተገን ጠይቆ የሚኖረው አቤል ከ 18 ዓመት በታች በነበረበት ጊዜ ጉዳዩን በተመለከተ የሚያግዘው ሰው ተመድቦለት ነበር። አሁን 19 ዓመት ስለሞላው ኃላፊነቱን በግሉ መወጣት አለበት። በአሁኑ ሰዓት በሳምንት 3 ቀን ጋራዥ ውስጥ ይሠራል። 2 ቀን ደግሞ ከስራው ጋር የተያያዘ ትምህርት ይወስዳል። ምንም እንኳን አቤል አሁን ኑሮውን ቢለምድም፤ መጀመሪያ ላይ የነበረውን እንግዳነት ያስታውሳል። ይህ ድረ ገፅ በምን መልኩ እንደጠቀመው አካፍሎናል።

Flüchtlinge in Rosenheim
በርካታ ስደተኞች በደቡብ ጀርመን አድርገው ወደ ጀርመን ትላልቅ ከተሞች ለመጓዝ ሲሞክሩ ባቡር ላይ ይያዛሉ።ምስል Bundespolizei Rosenheim

ጀርመን የሚገቡት ተገን ጠያቂዎች ቁጥር በመብዛቱ በአሁኑ ሰዓት 100 000 የሚሆን የስደተኞች ጥያቄ ተቀባይነት የሚያገኝበት ወይም ውድቅ የሚሆንበትን ምላሽ ገና አላገኘም። አቤልም ምላሹን እየተጠባበቀ ይገኛል። እንደ የስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ተመልካች መሥሪያ ቤት ምላሽ የሚሰጥበት ጊዜ ይለያያል። የሶርያ ስደተኞች በአምስት ወር ገደማ ምላሽ ሲያገኙ ከፍጋኒስታን የመጡ ለምሳሌ ምላሽ እስኪያገኙ እስከ 13 ወር ሊፈጅ ይችላል። ለስደተኞች መብት እንደሚቆረቆረው ድርጅት ፕሮ አዙል ደግሞ ጀርመን ውስጥ ከ ሁለት አንድ ተገን ጠያቂ ተቀባይነት ያገኛል። የተገን ጠያቂዎች ተቀባይነት እንደ ምክንያቱ ቢለያይም ፤ መጀመሪያ ላይ የሁሉም ስደተኞች ጥያቄ ተመሳሳይ ነው። እንዴት ስደተኝነት መጠየቅ እችላለሁ? የሚል።

ኮሎኝ ከተማ የሚገኘው ኢትዮ -ኮሎኝ የስፖርት እና የባህል ማህበር ከአንድ የጀርመን የስደተኞች ምክር መስጫ ማዕከል ጋር በመተባበር ለስደተኞች ስላዘጋጀው ድረ ገፅ የድምፅ ዘገባውን በመክፈት ያገኛሉ።

ልደት አበበ

ተክሌ የኋላ