1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢራቅ፤ ከዉድመት ወደ ዉድመት

ሰኞ፣ ሰኔ 16 2006

የዛሬዎቹ አሸባሪዎች እስላማዊ መንግሥት የመመስረት ቅዠታቸዉ ነቅተዉ ከድሮዎቹ አሸባሪዎች ከኩርዶች ተምረዉ ማዕከላዊና ምዕራባዊ ኢራቅ ላይ «ሱኒስታን» ወይም ሌላ መንግሥት ቢያቆሙስ?

https://p.dw.com/p/1COcK
ምስል picture-alliance/abaca

የኢራቅ ኩርዶች ሰሜናዊ ኢራቅ ላይ «የኩርዲስታን አካባቢ መንግሥት» ያሉትን መስተዳድር ከመሠረቱ ከ1992 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ወዲሕ ኢራቅ ከካርታ-ወረቀት ባለፍ በገቢር አንድ ሆና አታዉቅም።ጥንታዊቱን፤ ታሪካዊቱን፤ ሥልጡኒቱን ሐብታሚቱን ሐገር አንድም-ሁለትንም እንዳትሆን ቅጥ ያሳጧት የዋሽግተን፤ ለንደን ሐያላን በሁለት ሺ ሰወስት ሲወሯት የበረገዱት የእልቅት እቶን አንድዶ አንዶ ሰሞኑን ከአንድም-ሰወስትምነቷም ጥፋት ጠርዝ ላይ አድርሷታል።የጎሳ፤ የሥልጣን፤ ከሁሉም በላይ የሐይማኖት ሐራጥቃ ልዩነት የገፋዉ ጥፋት ለአካባቢዉም እንደሚተርፍ ስጋቱን ያልገለጠ የሐያል፤ሐብታም ሐገር፤የትልቅ ማሕበር መሪ ዲፕሎማት የለም።ሁሉም ግን ጥፋት-ሥጋቱን የሚያስወግድ ሠላማዊ ብልሕት ከመሻት ይልቅ ጠላት የሚለዉን ለማጥፋት፤ አሰላለፉን ማሳመሩ እንጂ የጥፋቱ-ጥፋት።የጥፋት ሥጋቱ ሰበብ-ምክንያት መነሻ፤ ዳራዉ ማጣቃሻ፤ የሐይል አሰላለፉ እንዴትነት መድረሻችን ነዉ-ላፍት አብራችሁኝ ቆዩ።

የኢራቅ እና የሻም ወይም የሌቫንት እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ወይም ISIL የተሰኘዉ ቡድን እስላማዊ መንግሥት የመመሥረት አላማዉ ከግብ መድረሱ አጠራጣሪ ነዉ።ሥሙ በሚያጠቃልላቸዉ ከኢራቅ እስከ ፍልስጤም፤ከሶሪያ እስከ ሊባኖስ በሚገኙት ሐገራት ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል ብሎ የሚያስብ ታዛቢ፤ፖለቲከኛ ቀርቶ የራሱ የቡድኑ አባል እንኳ ካለ፤ እሱ ሲበዛ ወፈፌ-ሲያንስ ቅዥታም ነዉ።

ቡድኑ ብዙዎች እንደተስማሙበት አሸባሪ፤ ጥቂቶች እንደሚሉት ደፈጣ ተዋጊ፤ደጋፊዎቹ እንደሚያምኑት ለሱኒ ሐራጥቃ አማኞች መብት የሚታገል ይሆን ይሆናል።ተዋጊዎቹ ግን አንድም አሜሪካ መራሹን ወረራና ጥፋቱ ያስቆጣቸዉ ሁለትም የሺዓ መራሹ መንግሥት ግፍ-በደል ያስመረራቸዉ ሱኒ አረቦች መሆናቸዉ ግን እርግጥ ነዉ።

«ይሕን ነጥብ አፅንኦት ልሰጠዉ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም በዚሕ ዉጊያ የሚሳተፉት ነዉጠኞች ብቻ አይደሉም።በማዕከላዊ መንግሥት (አገዛዝ) የተንገፈገፉ፤ማዕከላዊ መንግሥት በሚያደርሰዉ ግፍ የተጠቁ የሱኒ አማፂያን ጭምር-እንጂ።ለዚሕም ነዉ እነዚሕ ታጋዮች በየአካባቢዉ ሕዝብና ነዋሪ ድጋፍ ይሕን ያሕል አካባቢ ባጭር ጊዜ የተቆጣጠሩት።»

ይላሉ-የክርዲስታን ርዕሠ-ከተማ የኤርቢል ከተባ። ኒሐድ ሳሊም ቆጃ።እዚሕ ቦን የኖሩ-እና የተማሩ ናቸዉ።ርዕሠ-ከተማዉን ኤርቢል ያደረገዉ የኩርዲስታን አካባቢ መንግሥት ሰሜናዊ ኢራቅን ከ1992 ጀምሮ-ይገዛል።ኩርዲስታን የራስዋ ፕሬዝዳንት አላት። መስዑድ ባርዛኒ ይባላሉ።ካቢኔ፤ በሕዝብ የሚመረጥ ምክር ቤት አላት።ጦር ሠራዊት አላት።ፔሽመሬርጋ ነዉ-ሥሙ።ፖሊሥ ሠራዊት፤ ባንዲራ፤ ብሔራዊ መዝሙር፤ ቋንቋ ብቻ አንድ መንግስት ሊኖረዉ የሚችለዉ ሁሉ አላት።

ሁሉም ያለዉን-ሁሉንም የሚያደርገዉን መስተዳድር በ1992 ከመሠረቱት ሁለት ዋናኛ የኩርድ የነፃነት ታጋዮች አንዱ ካርታ-ወረቀት ላይ አንድ የምትባለዉ የኢራቅ ፕሬዝዳንት ናቸዉ።ጀላል ጠላባኒ።

ፕሬዝዳንት ሳዳም-ሁሴን የአንግሎ-አሜሪካኖች ወዳጅ በነበሩበት ዘመን-በአንግሎ-አሜሪካኖቹ ጠላት በኢራን ይደገፉ የነበሩት ጠለባኒ፤ባርዛኒና ሌሎቹ የኢራቅ ኩርድ የነፃነት ታጋዮች፤ ለባግዳድ፤ ለአንካራ፤ለደማስቆ እና ለምዕራብ ደጋፊዎቻቸዉ አሸባሪዎች ነበሩ።

ሳዳም ለዋሽግተን-ለንደኖች፤ወራሪ፤ ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ አምራች፤ አሸባሪዎችን ደጋፊ ቀንደኛ ጠላት ሲሆኑ ግን የኩርድ መሪዎች ጠላታቸዉን ወዳጅ-ወዳጃቸዉን ጠላት የማደረጉን መገለባበጥ ከሐያላኑ ለመማር ጊዜ አላጠፉም።

Irak Schiiten-Miliz in Bagdad
ምስል ALI AL-SAADI/AFP/Getty Images

ኩርዶች ሠልፋቸዉን ባሳመሩ ማግሥት ዋሽግተን-ለንደኞች ባደረጉባቸዉ ግፊት ጠለባኒ እና ባርዛኒ የሚመሯቸዉ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች የኩርዲስታን የአርበኞች ሕብረት PUK እና የኩርዲስታን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ KDP ከሌሎች ትናንሽ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመቆም ተስማሙ።ዋሽንግተን ለንደኖች በሰጧቸዉ የገንዘብ፤ የዲፕሎማሲ ከሁሉም በላይ «ዘመቻ ምቾት ፈጣሪ-ባሉት ወታደራዊ ከለላ ተጠልለዉ ኤርቢል ላይ ነፃ አከል መንግሥት መሠረቱም።

የዛሬዎቹ አሸባሪዎች እስላማዊ መንግሥት የመመስረት ቅዠታቸዉ ነቅተዉ ከድሮዎቹ አሸባሪዎች ከኩርዶች ተምረዉ ማዕከላዊና ምዕራባዊ ኢራቅ ላይ «ሱኒስታን» ወይም ሌላ መንግሥት ቢያቆሙስ?

የኤርቢሉ ከንቲባ እንደሚሉትእማ ኢራቅ-እኮ አሁንም ሰወስት ናት።

«ኢራቅ በሰወስት ትላልቅ-መስተዳድሮች መተዳደር አለባት።የኩርዲስታን ግዛት፤ ከከምዕራብ የሱኒዎች፤ ከደቡብ የሺዓዎች። የወቅቱ እዉነታ ይኽ ነዉ።ኢራቅ በሰወስት የተከፈለች ናት።አነዚሕ አካባቢዎች ባግዳድ ላይ በቆመ አንድ ማዕከላዊ መንግሥት መንግድ እንዲገዙ ወይም እንዲያስተዳድሩ የምንፈልገዉ ለምድነዉ ነዉ?»

የዚያች ታሪካዊት ሐገር ካንድነተ ይልቅ ሰወስትነቷ መድመቁ ባንድነቱ ለሚያምነዉ ሕዝቧ ታላቅ-ድቀት፤ለሩቁ ታዛቢ አሳዛኝ ክስተት ነዉ።ቱርክን፤ ሶሪያን፤ ኢራንን፤ ሊባኖስን፤ ባሕሬንን ለመሳሳሉ የአካባቢዉ ሐገራት፤ ለአብዛኛዉ አፍሪቃና ለሌሎችም የተለያየ ጎሳ፤ የተለያየ ሐይማኖት፤ የሚከተል ሕዝብ ተሰባጥሮ ለሚኖርባቸዉ ሐገራት ደግሞ መጥፎ አብነት።

ያም ሆኖ የኢራቅ ሰወስትነት ከ2003 ጀምሮ መዓልት-ወሌት የሚያልቀዉን መከረኛ ሕዝብ ከተጨማሪ እልቂት የማዳኑ ምልክት ከሆነ፤ ሐቁን መቀበሉ መራር ግን ምርጫ ሲጠፋ-የሚመረጥ ምርጫ መሆኑ ግድ ነዉ። ታላቁን ድቀት፤ አሳዛኝ መጥፎዉን አብነት ለማስቀረትም ሆነ ምርጫ-የሌለዉ ምርጫን ለመቀበሉ ሒደት ሠላማዊ ብልሐት እንዲፈለግለት ብዙ የፖለቲካ ተንታኝ ታዛቢዎች ብዙ ማለታቸዉ አልቀረም።

Irak kurdischer Soldat Stadtrand Kirkuk ISIS
ምስል picture-alliance/dpa

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙንም እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ በቀደም ደግመዉታል።

«የተለያዩ (ጎሳ ወይም ሐይማኖቶች) ከፍተኛ እልቂት የመቀጠሉ አደጋ በጣም ሠፊ ነዉ።ይሕ ሁላችንም በጣም አሳሳቢ ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ማሊክን ጨምሮ የኢራቅ መንግሥት መሪዎች ይሕን ጉዳይ ሁሉም ወገኖች በሚሳተፉበት ድርድር እንዲፈቱት ሳሳብ ነበር።ባለፈዉ ሳምት ከጠቅላይ ሚንስትር ማሊኪ፤ ከአካባቢዉ ሐገራት መሪዎች ከቱርክ፤ከኢራን እና ከሌሎችም ጋር በሥልክ ተነጋግሬያለሁ።»

የዓለም አድራጊ ፈጣሪዎች ግን የኤርቤል ከንቲባን አባባል፤ የፓንን ምክር፤ እዉነታዉንም ቢያንስ እስካሁን አልተቀበሉትም።እንዲያዉም የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ትናንት እንዳሉት ማዕከላዊና እና ምዕራባዊ ኢራቅን-የሚቆጣጠረዉን ቡድን (ISIS ISIL ነዉ የሚሉት እሳቸዉ) ለመነጠል ሌሎች የፖለቲካ ሐይላት በጋራ መቆም አለባቸዉ።

«ከፈለጉ ሁሉንም ኢራቅን በሙሉ የሚወክል፤ሕዝቡን የሚያስተባብር እና በISIL ላይ የሚያተኩር አመራር የመመመሥረት ዕድሉ አላቸዉ።»

ባሁኑ ወቅት ገሚስ ኢራቅን የሚቆጣጠረዉን ሐይል ) ያገለለ-ግን ሁሉንም ወገኖች ያቀፈ መንግሥት የሚመሠረት ብልሐት-መኖሩ በርግጥ ግራ-አጋቢ ነዉ። ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ ከምርጫ ዘመቻቸ ኖቤል የሠላም ሽልማት እስከ ተሸለሙበት ጊዜ ድረስ ለዓለም ሠላም ከገቡት ቃል- የተሳካላቸዉም አንድ ነገር ነዉ። ኢራቅ ሠፍሮ የነበረዉን የአሜሪካ ጦር ማስወጣቱ።

U.S. Außenminister John Kerry und Nuri Al Maliki Premierminster Irak 23.06.2014 Bagdad
ምስል REUTERS

ኦባማ ከኢራቅ ለተመለሱ ወታደሮች ታሕሳስ 2011 ባደረጉት የምሥጋና ንግግር ጦራቸዉ የወጣዉ «ሉዓላዊት፤ የተረጋጋች እና ራስዋን የቻለች» ኢራቅን መሥርቶ ነዉ ብለዉ ነበር።በቦምብ አረር የምትነደዉን የኢራቅን መረጋጋት፤እስካሁን እሁለት አሁን ደግሞ እሰወስት ከመቆረስ ጠርዝ የደረሰችዉን-የኢራቅን ሉዓላዊነት የሚዉቁት በርግጥ ኦባማ፤መስተዳድራቸዉና ተከታዮቹ ናቸዉ።

ብቻ ኦባማ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት ገሚስ ኢራቅን የሚቆጣጠረዉ ISIS አሸባሪ ነዉ።አሸባሪዉን ቡድን ለማጥፋት ኦባማ ከሁለት ዓመት በፊት «እራሷን የቻለች» ላሏት ለኢራቅ መንግሥት የጦር መሳሪያና የወታደር ዕርዳታ ዳግም ልከዋል።

«ዩናይትድ ስቴትስ ለኢራቅ ፀጥታ አስከባሪ የምንሰጠዉን ድጋፍ እንቀጥላለን።ባግዳድና ሰሜናዊ ኢራቅ ዉስጥ የISILን የሽብር ሥጋት ለመቋቋም የሚረዳ የጋራ የዘመቻ ማዕከላት ለመመሥረት ተዘጋጅተናል።በአዲሱ የፀረ-ሽብር ወዳጅነት ድርጅት መሠረት ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎችን ለመስጠት ከምክር ቤቶቹ ጋር እየሰራን ነዉ።ኢራቅ በኤምባሲያችን ዉስጥ አማካሪዎች ወትሮም አሉን።አሁን ደግሞ ሰወስት መቶ ያሕል ተጨማሪ ወታደራዊ አማካሪዎችን ለማዝመት ተዘጋጅተናል።»

ዩናይትድ ስቴትስ ከሳዳም ሁሴይን የቀማችዉን የባግዳድ ቤተ-መንግስት ለታማኞችዋ ስታከፋፍል ሥነ-ሥርዓታዊዉ ግን የተከበረዉ ሥልጣን የደረሳቸዉ ሱኒዉ ግን ኩርዱ ጠላባኒም፤ የጠቅላይ ሚንስትርነቱ ዋና ሥልጣን የተሰጣቸዉ ሺዓዉ፤ግን አረቡ ኑሪ አል መሊኪም፤ አሜሪካ ካለች ምንገዷቸዉ። ያን እንደ-ኩርዶች ሱኒ፤ እንደ ሺዓዎች አረቦች የተሰባሰቡበትን ቡድን አወገዙ።አሸባሪ-እያሉ።

መሊኪ ከዉግዘትም አልፈዉ የሺዓ ወጣት ሱኒ-ወገናቸዉ ላይ እንዲዘምት ሰበኩት፤ ቀሰቀሱት። ወጣቱም-ወገኑን ሊወጋ ከተተ።ባደባባይ ሠልፍ ዛተ-ፎከረም።እሱ-አንዱ ነዉ።

Obama Pressekonferenz US Politik Irak 19.06.2014
ምስል Reuters

«የዚሕ ሠልፍ ዓላማ ለኢራቅ ሕዝብ ጠላቶች፤ ለፅንፈኞችና ለአሸባሪዎች መልዕክት ለማስተላለፍ ነዉ።እኛ የኢማም አል-መሕዲ አባላት መሆናችን የሕዋዝ-(የሺዓ መንፈሳዊ ትምሕርት ቤት) ልጆን መሆናችንን፤ ቀዉስን ለማስወገድ በጣም የተራቀቀ ከባድና ቀላል መሳሪያ የታጠቅን መሆናችንን እንዲያዉቁት ለማድረግ ነዉ።»

ጠለባኒንም፤ መሊኪንም ለረጅም ጊዜ ሲረዱ ለነበሩት ለሺዓ-ፋርሶቹ አያቱላሆችም፤ለደማስቆ ባአዚዝስት-አላዊት አረቦችም፤ ደማስቆ-ቴሕራኖችን ባሸባሪነት ለሚወነጅሉት፤ ለጥፋታቸዉ ለሚታገሉት ለዋሽግተን-ቴል አቪቭ-ብራስልስ መሪዎችም የሰሞኑ ዋና ጠላት፤ አደገኛ አሸባሪ ISIS ወይም ISIL ነዉ።

ሶሪያ፤ ኢራቅን እና እስራኤል አቃርጠዉ የያዝዋት ትንሺቱ፤ ደሐይቱ ዮርዳኖስ ሳትቀር አሸባሪዉን ቡድን ለመዉጋት ጦሯን በተጠንቀቅ አቁማለች።የዩናይትድ ስቴትስ ከሠላሳ ዓመታት በላይ በአክራሪ፤ አሸባሪነት ከምትወነጅላት ኢራን ጋር ያን ቡድን በጋራ ለማጥፋት ንግግር ጀምራለች።

ዋሽግተኖች ቴሕራኖችን ጠጋ ጠጋ ማድረጋቸዉን ያልወደዱት የሪያድ ነገሥታት «በኢራቅ የዉስጥ ጉዳይ ማንም ጣልቃ ባይገባ ጥሩ» ነዉ ማለት ይዘዋል።

በዋሽግተን ቴሕራኖች የሚደገፉት ጠቅላይ ሚንስትር መሊኪ ባንፃሩ ሳዑዲ አረቢያ ሱኒ አማፂያንን ትደግፋለች በማለት ሪያዶችን ወንጅለዋል።«መጀመሪያ ቤታቸዉን ያፅዱ» መለሱ የሪያድ ነገስታት-ለመሊኪ ወንጀላ።

Irak Flüchtlinge 16.06.2014
ምስል picture alliance/AA

ኢራኖች በኣካባቢዉ የበላይነትን ለመያዝ ባንድ በኩል ከሳዑዲ አረቢያ ጋር እተሻኮቱ-በሌላ በኩል እንደ አሜሪካኖች ሁሉ የሱኒዎችን አማፂ ቡድን እያወገዙ፤ከአሜሪካኖች ጋር እተወያዩ ግን ደግሞ የአሜሪካኖችን ጣልቃ ገብነት በግልፅ ይቃወማሉ።

«በኢራቅ የዉስጥ ጉዳይ ዩናይትድ ስቴትስም ሆነች ሌሎች ወገኖች ጣልቃ መግባታቸዉን እንቃወማለን።አንቀበለዉም።ምክንያቱም የኢራቅ መንግሥት፤ ሕዝብና የሐይማኖት ባለሥልጣናት ይሕን ቀዉስ ያስወግዱታል ብለን እናምናለንና።በፈጣሪ ፍቃድ ይወገዳልም።»

አሉ የኢራኑ ላዕላይ መሪ አያቱላሕ ኻሚኒ-ትናንት። ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ግን ዛሬ ባግዳድ ዉስጥ ጠቅላይ ሚንስትር መሊኪን አነጋግረዋል።የኬሪ መልዕክት በአመራራቸዉ ብዙዎች የተከፉባቸዉ መሊኪ ሥልጣን እንዲለቁ መጠየቅ ይሁን-ISIS የሚጠፋበትን ሥልት ማማከር ይሁን በዉል አለየም።

ሁለቱም ቢሆን የኢራቅ ኩርዶች ነፃ መንግሥት ካወጁ መዘዙ የማይቀርላት ቱርክ የISIS አማፂያን ዜጎቿን በማገታቸዉ በጣም ተበሳጭታ ነበር።ይሁንና እንደ ቱርክ ሁሉ የኩርዶች መዘዝ ከሚያሰጋቸዉ ከቴሕራኖች ወይም ከምታስወጋቸዉ ደማስቆዎች ጋር ለመወዳጀት አልቸኮለችም።እንዲያዉም ሺዓዎች በሚበዙበት ባስራ የሚገኝ ቆንስላዋን ዘግታ-በባግዳዱ የሺዓዎች መንግሥት ላይ ያላትን ጥርጣሬ ግልፅ አድርጋለች።

አዉሮጶች እንደ አሜሪካኖች ሁሉ ISISን በአሸባሪነት ለማዉገዝ-መወንጀል አላመነቱም።ቡድኑን በጦር ሐይል ለማጥፋት መዛቱን ግን ቀዝቀዝፖለቲካዊ መፍትሔ» ማለቱን ሞቅ-ደመቅ አድርገዉት-አዲሱ የበጋ ሳምንት-አንድ አለ።የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ዛሬም ደገሙት።

Irak 21.06.2014
ምስል Getty Images/Afp

«ባለፉት ሳምንታት በተደጋጋሚ ለመገናኛ ዘዴዎች እንደነገርኩት አሁን የሚያስፈገዉ የISISን ግስጋሴ ለመግታትና የሱኒ ሕዝብን ድጋፍ እንዳያገኝ ለማድረግ ሁሉኑንም አካባቢዎችና ሐይማኖችን ያቀፈ ሁሉን አቀፍ መንግሥት መመሥረት ነዉ።ይኽ በተቻለ ፍጥነት መመሥረት ያለበት አንዱ ጉዳይ ነዉ።»

ISIS ደፈጣ ተዋጊዎች ሞሱሉን ከተቆጣጠሩ ወዲሕ ምዕራባዉያን በጣሙን አሜሪካኖች ፊት የነሷቸዉ የጠቅላይ ሚንስትር መሊኪ ዘመነ-ሥልጣን በጣት የሚቆጠር ነዉ።መሊኪን የሚተካዉ መሪ ሳዳምን ወይም መሊኪን ላለመሆኑ ግን ምንም ማረጋገጪያ የለም።መሊኪ ከISIS ጋር እንዲደራደሩ ከመገፋፋት ይልቅ ሥልጣናቸዉን መስዋዕት አድርገዉ-ISIS የሚያጠፋ ሌላ ፖለቲከኛ እንዲሾም ግፊት በሚደረግባቸዉ ባሁኑ ወቅት ያቡድን ተጨማሪ ግዛቶችን መቆጣጠሩ ጉድ-አጃኢብ እያሰኘ፤ የኢራቅም ጥፋት-እንደቀጠለ ነዉ።ለዛሬ ይብቃን።ነጋሽ መሐመድ

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ