1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢራቅ፤ የጦርነት ማግስት ጦርነት ምድር

ሰኞ፣ ሰኔ 6 2008

ዘመቻዉ ግራ የገባዉን ዓለም ግራ-አጋቢ ሥልት በትንሹ ግን በግልፅ የሚያሳይ ትርዒት ይመስላልም። ኢራንና ዩናይትድ ስቴትስ «ጠላቶች» ናቸዉ። በአሜሪካኖች የሠለጠነ፤ የአሜሪካኖች ጦር መሳሪያ የታጠቀ፤ በአሜሪካ አማካሪዎች፤ በአሜሪካ የጦር ጄቶች የሚረዳዉን የኢራቅን ጦር፤ ኢራኖችም ያግዙ፤ ያማክሩ፤ የኢራን ሚሊሺያዎችም ከጎኑ ተሰልፈዉ ይዋጉለታል።

https://p.dw.com/p/1J5sv
ምስል Reuters/A. Al-Marjani

ኢራቅ፤ የጦርነት ማግስት ጦርነት ምድር

ኢራቅን የወረረዉ የአሜሪካ ጦር አዛዦች ድል፤ ገድል፤ ሽንፈት ዉድቀታቸዉን ሲተርኩ ብዙዎቹ የፋላጁሑን ዉጊያ ማለፍ አይችሉም። በተለይ በ2004 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) «ሁለተኛዉ የፋሉጃሕ ዘመቻ» በተባለዉ ዉጊያ የተካፈለዉ የአሜሪካ፤ የብሪታንያ እና የኢራቅ ጦር አዛዦች እንደሚሉት ጦራቸዉ የገጠመዉ አፀፋ የአሜሪካ ጦር በ1968 ሆይ በተባለችዉ የቬትናም ከተማ ከገጠመዉ ፈተና ጋር ተመሳሳይ ነዉ። ዘንድሮ ፋሉጃሕን ለመያዝና ላለማስያዝ የሚፋለሙት ኃይላት ማንነት፤ ስምና ብዛት በርግጥ ከቀዳሚዎቻቸዉ የተለዩ ናቸዉ። የሚያደርሱት ጥፋት፤ ዓላማ፤ ሥልታቸዉ ግን ከዛሬ 48 ዓመቱም፤ ከዛሬ 12 ዓመቱም ብዙም የተለየ አይደለም። የተዋጊዎቹ ማንነት፤ የዉጊያዉ ጥፋት እና የዉጤቱ እንዴትነት የቅኝታችን ትኩረት ነዉ ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ባለፈዉ ታሕሳስ እንዳሉት እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS ወይም ISIL) ብሎ የሚጠራዉን አሸባሪ ቡድን ለማጥፋት መንግሥታቸዉ የከፈተዉን ዓለም አቀፍ ሁለንተናዊ ዘመቻ አጠናክሮ ይቀጥላል። ፕሬዝደንቱ እንዳሉት ዩናይትድ ስቴትስ እና የቅርብ ተባባሪዎችዋ ቡድኑን ለማጥፋት ከቀየሱት ሥልት ቀዳሚዉ ኢራቅና ሶሪያ የሚገኙ የቡድኑን ጠንካራ ይዞታዎች መቀማት ነዉ። በተለይ ኅዳር ላይ የፈረንሳይዋ ርዕሠ-ከተማ ፓሪስ በአሸባሪዎች መጠቃትዋ አሜሪካ መራሹ ዓለም በአሸባሪዉ ቡድን ላይ የከፈተዉን ዘመቻ ማጠናከር እና ማጣደፍ ይገባዋል፤ ፕሬዝደንቱ ያኔ እንዳሉት።

«ISILን የሚዋጉ በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ የኢራቅና የሶሪያ ኃይላትን ማሠልጠንና ማስታጠቃችንን እንቀጥላለን። ይሕን በማድረግ (ቡድኑን) መሸሸጊያ እናሳጣዋለን። ጥቃቱን የሚያፋጥን ልዩ ጦር በሁለቱም ሃገራት እያሰፈርን ነዉ። ፓሪስ ከተጠቃች ወዲሕ ይሕን እርምጃችንን እያጣደፍን ነዉ። እስፍራዉ ዉጤታማ እርምጃዎንም እየወሰድን ነዉ።»

Irak Falludscha Kämpfe IS
ምስል picture-alliance/AP Photo/K. Mohammed

በርግጥም ኦባማ እንዳሉት ከፓሪሱ ጥቃት በኋላ አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅና ሶሪያ የሚገኙ የISIS ይዞታዎችን በጦር ጄት፤ በሰዉ አልባ አዉሮፕላን (ድሮን) እና ሚሳዬል መደብደቡን አጠናክሯል። የኢራቅ መንግሥት ጦር፤ የኩርድ ወታደሮች፤ ለዘብተኛ የሚባሉት የሶሪያ አማፂ ቡድናት አልፎ ተርፎ የኢራንና የሊባኖስ ሚሊሺያዎች የአሸባሪዉን ቡድን ይዞታዎች ለመማረክ በየአካባቢዉ እየተፍጨረጨሩ ነዉ።

የኢራቅ መንግሥት ሥልታዊዉን የአንባር ግዛትን በተለይም ፋሉጃሕን ከአሸባሪዉ ቡድን ለመማረክ መጠነ-ሰፊ ዘመቻ የከፈተዉም ከፕሬዝደንት ኦባማ መግለጫ በኋላ ነዉ። የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ጄቶች፤ ሔሊኮብተሮችና ድሮኖች ካየር፤ የጦር አማካሪዎችና ልዩ ኮማንዶዎች ከምድር ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚሰጡት የኢራቅ መንግሥት ጦር በርግጥ ብቻዉን አይደለም።

ከመደበኛዉ ጦር በተጨማሪ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ እና የሺዓ ሚሊሺያዎች ዘምተዋል። ዘመቻዉ ግራ የገባዉን ዓለም ግራ-አጋቢ ሥልት በትንሹ ግን በግልፅ የሚያሳይ ትርዒት ይመስላልም። ኢራንና ዩናይትድ ስቴትስ «ጠላቶች» ናቸዉ። በአሜሪካኖች የሠለጠነ፤ የአሜሪካኖች ጦር መሳሪያ የታጠቀ፤ በአሜሪካ አማካሪዎች፤ በአሜሪካ የጦር ጄቶች የሚረዳዉን የኢራቅን ጦር፤ ኢራኖችም ያግዙ፤ ያማክሩ፤ የኢራን ሚሊሺያዎችም ከጎኑ ተሰልፈዉ ይዋጉለታል።

በሁለቱ ጠላቶች ግራ-ቀኝ የሚደገፈዉ የኢራቅ ጦር ባለፈዉ መጋቢት በከፈተዉ ዘመቻ እስካሁን ለዉጤት የበቃዉ ረመዲ የተባለችዉን ከተማ መቆጣጠሩ ብቻ ነዉ። ረመዲ በመንግሥት ጦር ቁጥጥር ብትዉልም ከአይ ሲ ስ ሰርጎ-ገብ ደፈጣ ተዋጊዎችና አጥፍቶ ጠፊዎች የዕለት ከዕለት ጥቃት አላመለጠችም። ዘገቦች እንደሚጠቁሙት የመንግሥት ጦር ረመዲን ከተቆጣጠረ ካለፈዉ ሚያዚያ ወዲህ በሳምንት ባማካይ አራቴ በቦምብ ፍንዳታ ትሸበራለች።

Irak Falludscha Flüchtlinge vor Kämpfen
ምስል Reuters/T. Al-Sudani

የአጠቃላይ ዘመቻዉ ዋና ኢላማ የሆነችዉ ፋሉጃሕ ግን አሁንም በአሸባሪዉ ቡድን ቁጥጥር ሥር ናት። ከተማይቱን ለቀዉ የሚወጡ ነዋሪዎች እንደሚሉት የመንግሥት ጦር ፋሉጃሕን ማጥቃት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የሚላስ የሚቀመስ ማግኘት ሲበዛ ከባድ ነዉ። አማፂያኑ በነዋሪዎቹ ላይ የሚያደርሱት በደልም እየከፋ ነዉ።

«ሠላሳ-አምስት ሆነን በጠፍ ጨረቃ ከከተማይቱ ሸሸን። አክስቴም አብራን ጉዞ ጀምራ ነበር።መሐል ላይ ተጠፋፋን።እዚያ ጀሐነብ ነዉ። ምንም ነገር የለም። ምግብ የለም። ዉኃ የለም። ሰዉ ለመኖር የሚያስፈልገዉ ምንም ነገር የለም። ይሕ ልቤን ይሰብረዋል።»

ይላሉ አአሪፍ። በሩቁ ዘመን፤- የባቢሎኖች ሥልጣኔ ያንቆጠቆጣት፤ የአይሁድ ትምሕርት ቤቶች የፈሉባት፤ ትንሽ ከተማ ነበረች። በመሐሉ የቱርክ ነጋዴዎች የሚያርፉባት፤ በርካታ መሳጂዶች የታነፁባት ትንሽ ግን ሥልታዊ ከተማ ሆነች። በኋለኛ ዘመንዋ ፋብሪካዎች የሞሉባት፤ ንግድ የሚቀለጣጠፍባት፤ በመንገድ-ድልድይ ያሸበረቀችr ትልቅ ከተማ ሆነች። ከሁሉም በላይ የኤፍራጥስ ወንዝ ለሁለት የሚገመስባት ፤ ዘመናይ ትልቅ ከተማ ነበረች። ፋሉጃሕ።

በ1991 በከፊል፤ ከ2004 ወዲሕ ደግሞ በአብዛኛዉ ወድማለች።ዛሬም እየወደመች ነዉ።

በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ማብቂያ የኦስማን ቱርክ ተሸንፎ ብሪታንያ አካባቢዉን በተቆጣጠረች ማግሥት በ1920፤ ሌትናንት ኮሎኔል ጀራልድ ሌችማን የተባሉ ብሪታንያዊ ሐገር አሳሽ የጦር መኮንን ከተማይቱን የሚያስተዳድሩትን ሼኽ እንዲያነጋግሩ ተላኩ። የሼኹ ልጆች ኮሎኔሉን ገደሏቸዉ። በሃያ-አንደኛ ዓመቱ በ1941 ፋሉጃሕ አጠገብ የነበሩ የኢራቅ ወታደሮች በብሪታንያ ቅኝ ገዢ ጦር ላይ አምፀዉ ብዙ የብሪታንያ ወታደሮችን ገደሉ። የብሪታንያ ጦር ግን አመፀኞቹን ባጭር ጊዜ ደፈለቃቸዉ።

ኩዌትን ከኢራቅ ወረራ ነፃ ለማዉጣት የዘመተዉ አሜሪካ መራሽ ጦር ኢራቅን ሲያጠፋ ብሪታንያዎች በሐምሳ አመታቸዉ ያችን ከተማ እንደገና አገኟት። 1991። ኤፍራጥስ ወንዝ ላይ የሚገኘዉን ድልድይ እንዲያፈርስ ዘመተ-የተባለ የብሪታንያ የጦር ጄት የታቀፈዉን ቦምብ ሕዝብ በተሰበሰበት የገበያ ሥፍራ ለቀቀዉ። በትንሽ ግምት አንድ መቶ ሐምሳ ሰዉ አለቀ።

Irak Falludscha Flüchtlinge vor Kämpfen
ምስል Reuters/T. Al-Sudani

ከጥቂት ቀናት በኋላ ሌሎች ጄቶች የጣሉት ቦምብ ሌላ የገበያን ሥፍራ አወደመ። ሌላ ሕዝብ ፈጀ። ኩዌትን ነፃ ለማዉጣት የዘመተ ጦር ከሰባት መቶ ኪሎ ሜትር በላይ የምትርቀዉን ከተማ፤ ያዉም ሰላማዊ ነዋሪዎችን በቦምብ የፈጀበትን ምክንያት የጠየቀ የለም። አሁንም፤ ምናልባት ከእንግዲሕም የሚጠየቅ የለም። እልቂት፤ ጥፋት፤ የጦርነት ማግስት፤ ጦርነቱ ግን ከ1920 በፊትም፤ በ1920ም፤ በ1941፤ በ1991፤ በ2003፤ ዘንድሮም እንደቀጠለ ነዉ።

ልዩነቱ እስከ 1991 የነበሩት ጦርነቶች በአብዛኛዉ በወታደሮች መካከል የሚደረጉ፤ አሸናፊ-ተሸናፊ የሚለይባቸዉ፤ አስታራቂ ሽማግሌ መሐል የሚገባባቸዉ ነበሩ። ዓለም የጅምላ ግድያን መጥፎነት፤ የሰላማዊ ሰዎች መጠቃትን ወንጀልነት፤ የጦር ወንጀልን አስከፊነት በሚያወግዝ፤ በሚኮንነበት ዘመን የሚደረገዉ ዉጊያ ግን ሕፃን ካዋቂ፤ ሴት ከወንድ፤ ወታደር ከሲቢል ሳይለይ መፍጀቱ ነዉ ሰቀቀኑ።

የአሪፍና የብጤዎቹ የፋሉጃሕ ነዋሪዎች ልብ የመሰበሩ ምክንያትም ሌላ አይደለም። በኢራቅ የተባበሩት መንግሥታት የርዳታ አስተባባሪ ሊሰ ግራንዴ ልብም እንደነአሪፍ ሳይሰበር አይቀርም። ቢቀር እንኳ ዓለም መልስ ያላገኘለትን ጥያቄ እንደገና ይጠይቃሉ። ለጦርነት ቢሊዮነ-ቢሊዮናት የሚከሰክሰዉ ሐያል ዓለም የጦርነቱ ጉዳተኞችን ለመርዳት ለምን ይሰስታል እያሉ።

«የሰብአዊ ርዳታ ድርጅቶች ገንዘብ ጨርሰዋል። ያለን በሙሉ እዚሕ ለፋሉጃሕ ችግረኞች ዉሏል። የተረፈን የለም። ተጨማሪ ዘጠና ሺሕ ሕዝብ ወደኛ ለመምጣት እየሞከረ እንደሆነ እናዉቃለን። እነሱን የመርዳት አቅማችን በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ደግነት ላይ የተመሠረተ ነዉ። ዳአሽ ወይም አይስልን ለማሸነፍ ለጦር መሳሪያ ያን ያሕል ገንዘብ እየወጣ፤ የአይስል ሰለባ የሆነዉን ሕዝብ እርዳታ መንፈጉ ለኛ ትርጉም የለዉም።»

አሜሪካ መራሹ ጦር ኢራቅን በወረረበት በ2003 ብዙ ጉዳት ካልደረሰባቸዉ የኢራቅ ትላልቅ ከተሞች አንዷ ነበረች። ዓመት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ግን ወረራዉን የሚቃወሙ ደፈጣ ተዋጊዎች፤ የቀድሞዉ የኢራቅ መንግሥት ባልደረቦችና ደጋፊዎች፤ የአልቃኢዳ እና የሌሎች አሸባሪ ቡድናት መከማቻ ሆነች።

የዩናይትድ ስቴትስ፤ የብሪታንያና የኢራቅ ወታደሮች ከተማይቱን ለመቆጣጠር ግንቦት 2004 የከፈቱት ዘመቻ በአማፂያኑ አፀፋ ከሸፈ። ሕዳር 2004። ሁለተኛ ዘመቻ። በዘመቻዉ ከስድስት ሺሕ በላይ የአሜሪካ፤ ከአንድ ሺሕ በላይ የብሪታንያ፤ ሁለት ሺሕ የኢራቅ ወታደሮች ተካፍለዋል። በአማፂያኑ በኩል ሰወስት ሺሕ ተዋጊዎች መሰለፋቸዉ ተዘግቧል።

ከተማይቱን ለመቆጣጠር በተደረገዉ የቤት ለቤት ዉጊያ በሁለቱም ላይ የደረሰዉ ጉዳት ሲበዛ ከባድ ነዉ። የአሜሪካ ጦር ከ1968 የሆይ( ቬትናም) ከ ወጊያ ወዲሕ ከባድ ወጊያ ሲገጥመዉ የያኔዉ የመጀመሪያዉ ነዉ። በ2005 አሜሪካኖች በብዙ መስዋዕትነት የተቆጣጠሯት ከተማ በ2014 ከሌላ አማፂ እጅ ወደቀች። አይሲስ። አሁንም ከተማይቱን ለመያዝ ከአስር ሺሕ በላይ ጦር ዘምቶባታል። ጦርነቱን የሚከታተሉ እንደሚሉት የኢራቅ መንግሥትና ተባባሪዎቹ ፋሉጃሕ መቆጣጠራቸዉ አይቀርም። በ1941፤ በ1991፤ በ2004ም እንዲሁ ተብሎ-እንዲሁ ሆኖ ነበር።

Irak US-General Joseph Votel
ምስል picture-alliance/AP Photo/R. Burns

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ