1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢቦላ ዳግም በምዕራብ አፍሪቃ

ዓርብ፣ ሐምሌ 24 2007

ፍጥነቱ ጋብ አለ እንጂ በምዕራብ አፍሪቃ ሙሉ ለሙሉ አልተወገደም፤ኢቦላ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 መገባደጃ ላይ ተቀስቅሶ ከ11 ሺህ በላይ አፍሪቃውያንን ቀጥፏል። ህፃናትን ከወላጆች፣ ዘመድን ከዘመድ አለያይቶ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስም ፈጥሯል ይኸው የኢቦላ ተሐዋሲ።

https://p.dw.com/p/1G88Q
Ebola-Impfung in Liberia 02.02.2015
ምስል John Moore/Getty Images

[No title]

ጠፋ ሲሉት ብቅ እያለ ላለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ27,800 በላይ ሰዎችን ተሐዋሲው አጥቅቷል። የምዕራብ አፍሪቃዋ ላይቤሪያ በቅርቡ ከኢቦላ ተሐዋሲ ነፃ መኾኗን ማወጇ ከተሰማ በኋላ ከዛሬ ሁለት ሣምንት በፊት ስድስት ሰዎች በተሐዋሲው መጠቃታቸው ተመዝግቧል። ጎረቤት ጊኒ እና ሴራሊዮን ውስጥ ደግሞ ባለፈው ሣምንት በእያንዳንዳቸው ወደ አምስት የሚጠጉ ሰዎች በኢቦላ ተሐዋሲ መያዛቸው ተሰምቷል።

ኒኮላስ አሾፍ ሌአፔል ጀርመን ለተሰኘው ማኅበር ሰሜን ሴራሊዮን ቦምባሊ አውራጃ ውስጥ በሚገኝ አንድ ጤና ጣቢያ ውስጥ ያገለግላሉ። እንደ መገናኛ አውታሮቹ ሁሉ እሳቸውም ኢቦላ ሙሉ ለሙሉ አለመጥፋቱን ይናገራሉ።

«በአካባቢው በየቀኑ የሚሆነውን እንከታተላለን። እናም እዚያ አሁንም ድረስ በኢቦላ ተሐዋሲ የሚያዙ ሰዎች እንዳሉ እንሰማለን። ሆኖም እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን እኛ ያለንበት ቦምባሊ አውራጃ ከኢቦላ ነፃ ነው።»

Sierra Leone Ebola Hilfe
ምስል L'Appell Deutschland

ሴራሊዮን ውስጥ ኾነው አፍሪቃውያኑን በማገልገል ላይ ያሉት ኒኮላስ አሾፍ በቪተን ሔርዴከ ዩኒቨርሲቲ የስምንተኛ ወሰነ-ትምኅርት የህክምና ተማሪም ናቸው። የኢቦላ ተሐዋሲ በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ተቀስቅሶ በርካቶችን ሲቀጥፍ ብዙዎቹ የውጭ ሃገራት የህክምና ባለሙያዎች ጓዛቸውን በፍጥነት ሸክፈው ከአፍሪቃ ወጥተዋል። እሳቸው ግን ከአንዲት ጠና ያሉ ሜክሲኮያዊት ሐኪም ጋር በመሆን ተሐዋሲውን ሲዋጉ ቆይተዋል። አሁን በኢቦላ ተሐዋሲ የተጠቁ ሰዎች መኖራቸው በሦስቱ ምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ውስጥ በተሰማበት ወቅት የምዕራቡ ዓለም መገናኛ አውታር ትኩረት ያለመስጠቱ ነገር እንደሚያሳዝናቸው ገልጠዋል።

«በኢቦላ ተሐዋሲ የተጠቁ ሰዎች እንዳሉ እንሰማለን። የሚያሳዝነው ነገር ግን በጀርመን እና በአውሮጳ የሚገኙ የመገናኛ አውታሮቻችን እንደቀድሞው ትኩረት ሰጥተው ሲዘግቡበት አይታይም። ምናልባትም በኢቦላ የተያዘ ሰው ከእንግዲህ በጀርመን፣ በዩናይትድ ስቴትስ ወይንም ደግሞ በአጠቃላይ በአውሮጳ ስለሌለ ይኾናል፤ ብቻ ያ መኾኑ ያሳዝናል። »

የኢቦላ ተሐዋሲ በምዕራብ አፍሪቃ ሄድ መለስ በሚልበት በአሁኑ ወቅት የዓለም ጤና ድርጅት የኢቦላ ክትባት ሙከራ ስኬታማ መኾኑን ዓርብ ሐምሌ 24 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. ከጄኔቫ ይፋ አድርጓል። እንደ ጤና ድርጅቱ ከኾነ ጊኒ ውስጥ በ4,000 ሰዎች ላይ የተሞከረው የካናዳ ክትባት መቶ በመቶ ውጤታማ ነው። VSV-EBOV ወይንም VSV-ZEBOV የተሰኘው ክትባት ስኬታማ መኾኑን የጤና ድርጅቱ ቢያበስርም በርካታ ተቺዎች ግን ተሐዋሲው በምዕራብ አፍሪቃ ተቀስቅሶ በርካቶችን ሲቀጥፍ የዓለም ጤና ድርጅቱ ፈጣን ምላሽ አልሰጠም ሲሉ ይወቅሳሉ።

Ebola Liberia
ምስል picture-alliance/dpa/A. Jallanzo

ከዚህ ቀደም የኢቦላ ተሐዋሲ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በሱዳን አካባቢዎች ሲከሰት ብዙም ሳይስፋፋ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር። ይኸው ተሐዋሲ በምዕራብ አፍሪቃ ዳግም ከተከሰተ ከዓመት በላይ ቢያስቆጥርም እስካሁን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር አልዋለም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ