1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኖርዌይ

ሐሙስ፣ መጋቢት 15 2008

የኖርዌይ መንግስት 800 ኢትዮጵያውያንን በግዳጅ ወደ አገራቸው ለመመለስ በመዘጋጀቱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን አስታወቁ። ከእነዚህ መካከል ስልሳዎቹ ህጻናት ናቸው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/1IJZk
Äthiopische Asylbewerber in Norwegen
ምስል Ethiopian asylum seekers Association in Norway

[No title]

ወ/ሮ የሺሐረግ በቀለ ከስምንት አመታት በፊት ከኖርዌይ ሲደርሱ ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ስላልነበራቸው ለአስራ አምስት ያክል ቀናት ለእስር ተዳርገዋል። የእስር ጊዜያቸው ሲጠናቀቅ ጊዜያዊ ጥገኝነት ፈቃድ አግኝተው ሥራ ሲሰሩ ቆይተዋል። አሁን በአባልነት የሚያገለግሉበት የኢትዮጵያ ስደት ጠያቂዎች ማህበር በኖርዌይ ያለ ፍላጎታቸው ወደ አገራቸው የመመለስ እጣ ፈንታ የገጠማቸውን 800 ስደተኞች ለመታደግ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

የኖርዌይ ተገን ጠያቂዎች ድርጅት ቃል አቀባይ ዮን ኦለ ማርቲንሰን ውሳኔው በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እና ኖርዌይ የተፈራረሙት ስምምነት አንድ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

Äthiopische Asylbewerber in Norwegen
ምስል Ethiopian asylum seekers Association in Norway

«ወደ አገራቸው የሚመለሱት የተገን ጥያቂያቸው ውድቅ የተደረገባቸው እና በኖርዌይ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው። የኖርዌይ መንግስት ህጋዊ የጉዞ ሰነድ የሌላቸውን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ሳይችል ቆይቷል። ስለዚህ በ2012 ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት ተፈረመ። ይህ በፈቃደኝነት የሚመለሱትን እና የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ይጨምራል። የኖርዌይ መንግስት እስካሁን ፈቀደኛ የሆኑትን እንዲሁም ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ያላቸውን ብቻ ነበር የሚመልሰው።»

የኢትዮጵያ ስደት ጠያቂዎች ማህበር በኖርዌይ አባላቱን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጋር በመተባበር በኦስሎ እና መሰል ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች አካሂዷል። ወ/ሮ የሺሐረግ እንደሚናገሩት ኢትዮጵያውያኑ በፖለቲካ አመለካከታቸውና ተሳትፏቸው ምክንያት ችግር ይገጥመናል የሚል ስጋት አላቸው።

ተገን ጠያቂ ኢትዮጵያውያኑን በግዳጅ የመመለሱ ተግባር በትክክል መቼ እንደሚጀመር በእርግጠኝነት አይታወቅም ያሉት ዮን ኦለ ማርቲንሰን የኢትዮጵያውያኑን ስጋት ይጋራሉ። ኢትዮጵያውያኑ ያለ ፈቃዳቸው ወደ አገራቸው ቢመለሱ ሊገጥማቸው የሚችለው አደጋ ያሳስበናል ሲሉም አክለዋል።

Äthiopische Asylbewerber in Norwegen
ምስል Ethiopian asylum seekers Association in Norway

«ስምንት መቶዎቹ አሊያም ከፊሉ ቢመለሱ በኢትዮጵያ ሳሉ አሊያም በኖርዌይ ባላቸው የፖለቲካ ተሳትፎ ምክንያት እንግልት ሊገጥማቸው ይችላል የሚል ስጋት አለን። እናም ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሌላቸው በኢትዮጵያ በሰላም መኖር የሚችሉት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ቢመለሱ ችግር ይኖረዋል ብለን አናምንም። ነገር ግን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያላቸው በኢትዮጵያ መንግስት ሊከሰሱ ይችላሉ የሚል ስጋት አለን።

ኖርዌይ ጥብቅ የተገን አሰጣጥ ፖሊሲ ያጸደቀችው ባለፈው አመት ሲሆን በርካታ ስደተኞችን በግዳጅ ወደ መጡበት ለመመለስ የምታደርገው ጥረት የ.ተ.መ.ድ. ጨምሮ ከበርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ነቀፋ ገጥሞታል።

እሸቴ በቀለ

ሒሩት መለሰ