1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞች በሮም የተፈፀመባቸው በደል

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 16 2009

ቁጥራቸው ወደ 800 ይጠጋል የተባለ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ሮም ኢጣልያ ውስጥ ለዓመታት ከኖሩበት ህንጻ በኃይል እንዲወጡ ከተደረገ ዛሬ ሦስተኛ ቀናቸውን አስቆጥረዋል። የኢጣልያ መንግሥት ከወሰደው ከዚህ ድንገተኛ እርምጃ በኋላ አብዛኛዎቹ በአቅራቢያው ከሚገኝ ጎዳና ላይ እንደፈሰሱ ነው። ድርጊቱን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ኮንነዋል።

https://p.dw.com/p/2iemt
Italien Demonstration in Rome
ምስል picture-alliance/Pacific Press/P. Cortellessa

ስደተኞች በሮም የተፈፀመባቸው በደል

ባለፈው ቅዳሜ ማለዳ ነበር ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከጎርጎሮሳዊው 2013 ዓም አንስቶ የሚኖሩበትን መሀል ሮማ ተርሚኒ ከተባለው ዋና ባቡር ጣቢያ አቅራቢያ የሚገኘውን ህንፃ ፖሊስ በማለዳ ጥሶ በመግባት በኃይል ያስወጣቸው። 500 የኢጣልያ ህግ አስከባሪዎች ከአየር እና ከምድር ህንጻውን ወረው በወሰዱት በዚህ ድንገተኛ እርምጃ 725 እንደሚሆኑ የተነገረ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ስደተኞች ጎዳና ላይ ተበትነዋል። ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው ድንገት ከህንጻው እንዲወጡ ከተደረጉት ስደተኞች አብዛኛዎቹ ንብረታቸውን ይዘው የሚወጡበት ጊዜ እንኳን አላገኙም። የሮሙ ወኪላችን ተክለ እዝጊ ገብረ እየሱስ በተበተኑበት ሜዳ ላይ ትናንት አግኝቶ ያነጋገራቸው ስደተኞች ለልዩ ልዩ ችግሮች መዳረጋቸውን ገልጸዋል። ከህንጻው ነዋሪዎች አብዛኛዎቹ  ኢጣልያ በስደተኝነት የተቀበለቻቸው እና ተገን ጠያቂዎች ናቸው።አቶ ዳኛቸው ሁንዴ ጡሬ የመኖሪያ ሰነድ ያገኙ እና በዚህ ህንጻ ውስጥ ለ3 ዓመት ያህል የኖሩ ስደተኛ ናቸው። ባለፈው ቅዳሜ ፖሊስ ህንጻውን ሰብሮ ሲገባ ቤታቸው አልነበሩም። እርሳቸው ከጠዋቱ 11 ሰዓት ነበር ወደ ሥራ የሄዱት አገር ሰላም ነበር ያኔ። ዱብ እዳው የደረሰው ከጠዋቱ 12 ሰዓት ነበር። በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች በስልክ ደውለው ከነገሯቸው በኋላ ሥራቸውን አቋርጠው ወደ ህንጻው ተመለሱ ።አቶ ዳኛቸው ወደ መኖሪያቸው ተመልሰው የመግባት እድል ባገኙበት አጋጣሚ ያዩት በህልምም በውንም ያልጠበቁት ነበር ።
የዛሬ 6 ዓመት በሊቢያው ጦርነት ወቅት ኢጣልያ የገቡት አቶ ዳኛቸው እንደሚሉት ስደተኞቹ ህንጻው ውስጥ መኖር የጀመሩት የኢጣልያን የስደተኞች አያያዝ በሚቃወሙ እና ለስደተኞች መብት በሚሟገቱ ኢጣልያውያን እና የኢጣልያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ድጋፍ ነው። የሮሙ ወኪላችን ተክለ እዝጊ ገብረ እየሱስ እንደሚለው ይህን መሰሉን ድጋፍ የሚሰጡት ግራ ዘመም ፓርቲዎች ናቸው። 
አቶ ዳኛቸው ስደተኞቹ ህንጻው ውስጥ መኖር እንደጀመሩ ፖሊስ ሊያስወጣቸው መሞከሩን በኋላም የፖለቲካ ስደተኞች መቆያ ይሁን ተብሎ ከተዉት በኋላ ለ4 ዓመታት ያህል ሊቆዩበት እንደቻሉ ተናግረዋል። ከሁለት ዓመት በፊት ህንጻው ውስጥ የሚኖሩት እንዲባረሩ ፍርድ ቤት ወስኖ ነበር የሚሉ ዘገባዎችም አሉ። የተመ የስደተኞች ጉዳይ መርጃ ድርጅት በምህጻሩ ዩ ኤን ኤች ሲ አር የኢጣልያ መንግሥት ስደተኞች በይፋ ሳይሰጣቸው ይኖሩበት ከነበረው ህንጻ እንዲወጡ መደረጉን በጥብቅ ተቃውሟል። በኢጣልያ የዩ ኤንኤች ሲ አር ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባልደረባ ባርባራ ሞሊኖርዮ ለበርካታ ዓመታት ኢጣልያ የኖሩትን እነዚህ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች የተፈጸመባቸው አግባብ አይደለም ብለዋል።
«ምንም ማስጠንቀቂያ አልተሰጣቸውም። ከተወሰኑ ችግር ላይ ካሉ እና ልጆች ካሏቸዉ ቤተሰቦች በስተቀር አብዛኛዎቹ አማራጭ አልተሰጣቸውም። ከህንጻው እንዲወጡ ነው የተደረገው። አማራጭ ቤት ግን አልተሰጣቸውም። ከህንጻው እንዲባረሩ ከተደረገ ከአንድ ቀን በኋላ ወዴት እንደሚሄዱ ያላወቁ ሰዎች ከህንጻው ፊት ለፊት በሚገኝ ጎዳና ላይ ነበር የፈሰሱት። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ባለሥልጣናት ለዚህ ችግር መፍትሄ ፍለጋ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው። ከመካከላቸው ቢያንስ 50 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን ከግምት ውስጥ ማስገባት ነበረባቸው። እነርሱም ጎዳና ላይ ነው የሚያድሩት። ከህንጻው ከተባረሩ ከሁለት ቀናት በኋላ ሁኔታው አሁንም አልተለወጠም።» 
UNHCR እንደሚለው ስደተኞቹ ባዶ የነበረው ህንፃ ውስጥ የገቡት በይፋ ታውቆ አይደለም። ይህን ያደረጉትም መኖሪያ ቤት ስላጡ እና መፍትሄ ስላልተፈለገላቸው ነው። በዚህ ዓይነት መንገድ ሮም ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ህንፃዎች የሚኖሩ ሰዎች ጉዳይም ከወዲሁ ሊታሰብብበት እንደሚገባ ሞሊናርዮ አሳስበዋል።
«ቀድሞ ባዶ የነበረ ስደተኞች እና ተገን ጠያቂዎች ገብተው የሚኖሩበት ህንፃ ይህ ብቻ አይደለም በሮም ከተማ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የተገፉ እና የተረሱ ናቸው። ስለዚህ እኛ የምንለው የኢጣልያ መንግሥት ጉዳዩን እንዳለ ይተወው ሳይሆን ከዚያ ይልቅ የተሻለ አማራጭ ያቅርብላቸው ነው የምንለው። እናም ስደተኞች ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህደው መኖራቸውን የሚደግፉ ፖሊሲዎች ሥራ ላይ እንዲውሉውሉ ነው የምንጠይቀው።»
በትናንትናው እለት ፖሊስ ሴቶች እና ህፃናት ወደ አንደኛ ፎቅ እንዲገቡ እንተደፈቀደላቸው ተዘግቧል። ትናንት የስደተኞቹ ተወካዮች የሮም ከተማን ባለሥልጣናት ካነጋገሩ በኋላ ባለሥልጣናቱ ባወጡት መግለጫ ቤተሰብ ያላቸውን አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞችን ቅድሚያ ሰጥተው ለመርዳት እንደሚሞክሩ አስታውቀዋል። ሌላ ምትክ መኖሪያ ለመስጠት ቃል ባይገቡላቸውም ስለ ወደፊቱ እርምጃ እንደሚያሳውቋቸው እንደነገሯቸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። አቶ ጌታቸው ቅዳሜ ጠዋት ወደ ከጡበት ቤታቸው እስካሁን መመለስ አልቻሉም። በዚያኑ እለትአስፈቅደው ከወጡበት  ሥራቸውም አልተመለሱም።

Polizei räumt von fast 1000 Migranten besetztes Haus in Rom
ምስል picture alliance/P. Cortellessa/Pacific Press via ZUMA Wire/dpa
Italien ausgeräumter Palast am Unabhängigkeitsplatz
ምስል picture-alliance/ZUMAPRESS.com/P. Cortellessa
Italien ausgeräumter Palast am Unabhängigkeitsplatz
ምስል picture-alliance/ZUMAPRESS.com/P. Cortellessa

ኂሩት መለሰ 

ነጋሽ መሐመድ