1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ኢትዮጵያ ሳተላይት አመጥቃለሁ ማለቷ

ረቡዕ፣ ጥር 10 2009

ኢትዮጵያ ከ3 እስከ 5 ዓመታት ድረስ ሳተላይት አመጥቃለሁ ብላለች። የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ከተቋቋመ ገና ጥቂት ወራትን ነው ያስቆጠረው። ለመሆኑ ሳተላይት ለማምጠቅ ምን አይነት አቅም ይጠይቃል?

https://p.dw.com/p/2VxKC
Indien Start Rakete PSLV-C35
ምስል picture-alliance/dpa

ኢትዮጵያ ሳተላይት አመጥቃለሁ ማለቷ

የኢትዮጵያ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር መሥሪያ ቤት ሰሞኑን አሶሺየትድ ፕሬስ ለተሰኘው የዜና ምንጭ እንዳስታወቀው ከሆነ ኢትዮጵያ እስከሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ድረስ የሲቪል ሳተላይት ወደ ኅዋ ልታመጥቅ አቅዳለች።  ላለፉት 55 ዓመታት በኅዋ ሳይንስ ዘርፍ የቴክኒክ ማማከር ድጋፍ የሚሰጠው የዩናይትድ ስቴትሱ ኤሮስፔስ የተሰኘው ተቋም የኢንተርኔት ሰነድ እንደሚጠቁመው ከሆነ ግን መንግሥታት ወደ ኅዋ የሚልኳቸው ሳተላይቶችን ገንብቶ እስከ ማምጠቁ ድረስ በአማካይ 7 ዓመት ከመንፈቅ  ጊዜያትን ይፈጃል። ኢትዮጵያ ከ3 እስከ 5 ዓመታት ድረስ ሳተላይት አመጥቃለሁ ብላለች። የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ከተቋቋመ ገና ጥቂት ወራትን ነው ያስቆጠረው። ለመሆኑ ሳተላይት ለማምጠቅ ምን አይነት አቅም ይጠይቃል?

«ኢትዮጵያ ከ3 እስከ 5 ዓመታት ድረስ ሳተላይት ወደ ኅዋ አስወነጭፋለው ትላለች» ሲል ማክሰኞ ጥር 2 ቀን፤ 2009 ዓ.ም. የዘገበው አሶሺየትድ ፕሬስ የተሰኘው የዜና ምንጭ ነው። የዜና አውታሩ የኢትዮጵያ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር መሥሪያ ቤትን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ ኢትዮጵያ ሳተላይቱን ልታመጥቅ ያቀደችው ቻይና ውስጥ ከሚገኝ ተቋም ነው።

ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች እና ሳይንቲስቶች ከቻይና በሚመጥቀው ሳተላይት ላይ ሚናቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት ወደ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንሥትር መሥሪያ ቤት ደወልን። የኅዋ ሳይንስን የሚመለከተው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋም እንደሆነ ተነገረን። ወደ ተቋሙ ደወልን።  የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ይባላሉ። እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጣ፦ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋም በመንግሥት አዋጅ የተቋቋመው ዘንድሮ መስከረም ወር ላይ ነው።

«ተቋማችን አዲስ ነው። አቅምን መገንባት፤ ሰው ኃይል ማደራጀት፤ ምርምር ማኪያሄድ  እነዚህ ሥራዎችን ነው የሚያከናውነው።  ከዚያ ደግሞ የምርምር ውጤቱ ጥሩ እየሆነ  ሲሄድ ወደሚፈልገው አቅጣጫ በየ እድገት ደረጃዎች  ምርምር እና አቅም ሲጎለብት  እንደዚያ አይነት ነገር ነው የሚደረገው።»

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋም የተቋቋመው ገና በዚህ ዓመት ቢሆንም፤ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ግን አንዲት አነስተኛ ሳተላይት በዚህ ዓመት ወደ ኅዋ የማምጠቅ አቅም እንደገነባ መግለጡ ይታወሳል። ሳተላይት የማምጠቅ ሙከራው የሚከናወነውም በተማሪዎች እና አስተማሪዎች እንደሆነ ተነግሮ ነበር። ሙከራው ይደረጋል ተብሎ የነበረውም «የመለስ ኤሮስፔስ ሳይንስና ኢንጂነሪንግ ዳይናሚክስ» በሚል ፕሮጀክት ስር ነው።  በዕቅዱ መሰረት ከሆነ ሳተላይት ወደ ኅዋ ለማምጠቅ በኢትዮጵያ ትግራይ የሚገኘው መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ብቸኛው ይሆናል።   

USA Start der Space-X Falcon 9
ምስል picture-alliance/Zumapress/Xinhua

ዶክተር ያብባል በአውሮጳ የኅዋ ተቋም የጠፈር አፈጣጠር ምሥጢርን ለመፍታት አሠሣ በሚያደርገው ሳተላይት የሚሰበሰቡ መረጃዎችን መተንተን ዋነኛ ተግባራቸው የሆነ ሣይንቲስት ናቸው።

«ኢትዮጵያ ውስጥም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሞከሩት ትንሽ ሳተላይት አለ። አልፋ መለስ የሚሉት 30 ኪሎ ሜትር  ለመጓዝ የሠሩት ሮኬት  የፈጀባቸው አቅደው፣ ሠርተው  እስኪያስወነጭፉት ድረስ  2,3 ሚሊዮን ዶላር  ነው የፈጀባቸው።  ይሄ እንግዲህ የተማሪዎች ፕሮጀክት ነው። ያው አስተማሪዎቻቸውም አብረው ሠርተዋል። ግን ለምንም የምትገለገልበት አይደለም።  ምክንያቱም ቢያንስ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት [መወንጨፍ አለበት] ከመሬት [ምኅዋር] ለመውጣት።»

ኢትዮጵያ በጥቂት ዓመታት ከቻይና ተቋም አመጥቀዋለሁ ያለችው ሳተላይት የአየር ሁኔታን በተሻለ ለመተንበይ ብሎም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ከርቀት ለመቃኘት ያስችላል ተብሎለታል። ዝርዝር መረጃ ገን አልተሰጠም።

ኢትዮጵያ ሳተላይት ለማምጠቅ ማቀዷን ያስታወቀችው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ በተከሰተው ከባድ ድርቅ የተነሳ 10 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሀብ ከተጋለጠ እና  በሺህዎች የሚቆጠሩ እንስሳት ከሞቱ በኋላ ነው ሲል አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። ሳተላይቱ ምን ያህል ወጪ እንደሚደረግለት እና ለወታደራዊ አገልግሎት ይውል እንደሆነም  ግልጽ የሆነ ነገር የለም ብሏል አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል በዘገባው።

«የሳተላይትን ጥቅም በደምሳሳው ብንመለከት፦ ሳተላይት [ወደ ኅዋ]የምትልከው መሬትን ለመቃኘት ከሆነ ከላይ ሆኖ ሲሽከረከር  ነገሮቹን ሁሉ በደንብ ለመመልከት ነው። ስለዚህ ሳተላይቱ ላይ የተለያዩ ነገሮችን ልታስቀምጥ ትችላለህ።  ካሜራዎች ልታስቀምጥበት ትችላለህ። እነዚያ ካሜራዎች የሚነግሩህ ምንድን ነው? የተለያዩ አይነት ካሜራዎች አሉ። ለምሳሌ፦ በዐይን የሚታየውን ብርሃን ብቻ ሳይሆን በዐይን የማይታዩትን እነ ኢንፍራሬድ፣ ማይክሮዌቭን የመሳሰሉ፤ የተለያዩ  ሬዲዮ ከምትለው ከረዥም ሞገድ ጀምረህ በጣም አጭር እስከምትለው እስከ ጋማ ሬይ ድረስ  የተለያዩ መረጃዎችን ከመሬትም ሊሆን ይችላል  ወይንም ደግሞ ነጥብህን ወደ ላይ ካደረግኸው ከመሬት ውጪ  የሚመጡትን ለመቀበያ ማለት ነው።»

ሳተላይት ላይ የሚገጠሙ ረቂቅ ካሜራዎች የሚጠቀሙት ጨረር በምድር ላይ የሚርመሰመሱ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን፥ ከምድር ውስጥ የመሸጉ ማናቸውንም አካላት ለመቃኘት ያስችላል። ወደ ኅዋ የሚመጥቁ ሳተላይቶች እንደየግባቸው ወጪያቸው የተለያየ ነው። ግዙፍ የሚባሉት ሳተላይቶች በአማካይ አጠቃላይ ወጪያቸው ከ100 እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር እንደሚፈጁ ዶክተር ያብባል ተናግረዋል።

ወደ ኅዋ የሚወነጨፉ ሳተላይቶችን መጠን የሚወስነው በሳተላይቱ ሊታሠሥ የተፈለገው ጉዳይ ዕቅድ እና ዓላማ ነው። ሳተላይት የማምጠቁ ዓላማ በርካታ ነገሮችን ለማሠሥ ከሆነ ሳተላይቱ ላይ ብዙ ቁሶችን መጫን  ያስፈልጋል። ብዙ መሣሪያዎች ለመጫን ደግሞ  ትልቅ ሳተላይት ያስፈልጋል። በዛው መጠን ሳተላይቱ ወጪውም መጠኑም ከፍ ይላል።

ዶክተር ያብባል የሚሠሩበት የአውሮጳው የፕላንክ ሳተላይት ከነቁሳቁሶቹ ወደ 1 ሺህ ኪሎ ግራም ይመዝናል። ኢትዮጵያ ልታስወነጭፍ ያቀደችው እስከ 500 ኪሎ ግራም የሚደርስ መካከለኛ ሳተላይት እንደሆነ ዶክተር ያብባል አክለዋል። 

China Raumlabor Tiangong 2
ምስል picture alliance/dpa/A. Xin

በእርግጥም የኅዋ ሳይንስ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ዘርፍ ነው። ለአብነት ያህል በርካታ ሳተላይቶችን ወደ ኅዋ ያስወነጨፈችው ህንድ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 ለኅዋ ምርምር ተቋሟ ያወጣችው ገንዘብ 1,1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ሳይንሳዊ ዘገባዎችን የሚያቀርበው ሳይንስ አለርት የተሰኘው ድረ-ገጽ ይጠቁማል። 

የኅዋ ሳይንስ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ ዘርፍ ብቻም አይደል። በዘርፉ ጥልቅ ዕውቀት ያካበቱ የበርካታ ሳይንቲስቶችን ያላሰለ ክትትል የሚሻ ጭምር እንጂ። በኅዋ ሳይንስ ዘርፍ የቴክኒክ ማማከር ድጋፍ የሚሰጠው የዩናይትድ ስቴትሱ ኤሮስፔስ ወደ 3,500 ግድም ሠራተኞች አሉት። ከግማሽ በላይ ሠራተኞቹ (70%) በኅዋ ሳይንስ ዘርፍ የቴክኒክ ባለሙያዎች ናቸው።  700 ያህሉ የተቋሙ ሠራተኞች የፒኤች ዲ ዲግሪ አላቸው። የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን።

የሰው አቅም እንግዲህ እንጦጦ ኦቭዘርቫቶሪ ምርምር ማዕከል የሚባለው አለ፤ የእነሱ ሠራተኞችም በስሩ አንድ ላይ ስለሆኑ  ገና ትንሽ ወደ 26 ሰው ነው ያለን።  ቅጥሩ ምናምኑ ገና የሰው ኃይል የማደራጀት  ሥራ ላይ ነው ያለው አሁን።»

አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና አውታር በሰሞኑ ዘገባው፦ የኢትዮጵያ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ቃል አቀባይ አቶ ወንድወሰን አንዱዓለም ኢትዮጵያን የኅዋ ሳይንስ ማዕከል ለማድረግ መንግሥታቸው እንዳቀደ ተናግረዋል ብሏል።

«የአጭር ጊዜ ዕቅዳችን ምርምር ማከናወን፤ የምርምር ሥርዓት መዘርጋት፤ የሰው ኃይል ማጠናከር፤  መዋቅራችንን ማደራጀት፤ ሰውን ማሰባሰብ እና ሰውን ማጠናከር ነው። ይኼ ነው በጣም አጭሩ።»

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚንሥትሩ የሚመራ የኅዋ ሳይንስ ምክር ቤት አለኝ ማለቷን አሶሺየትድ ፕሬስ በዘገባው አትቷል። በኅዋ ሳይንስ የሳተላይት ማምጠቅ ሙከራ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ተግባር ነው። ትንሽ ስህተት ሮኬቱን ገና ከመነሻው ሊያፈነዳው ይችላል።  ያም በመሆኑ ነው በርካታ ሃገራት ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ በስተመጨረሻ የሚሳካላቸው። ዶክተር ሰለሞን።  

«ምን ችግር አለ የረዥምማ አቅም የሚፈቅደውን ያህል እንሄዳለን። የረዥም አይደል ከመሬት ተነስተው እስከ ጥልቁ ኅዋ ድረስ የሚሄዱት ሰዎቹ?  ስለዚህ አቅሙ በፈቀደው ሁሉ  ረዥሙ፦ የኢኮኖሚውን፤ የሰው ኃይልን፤ ሁሉንም አቅምን እየጠበቀ  የሚሄድ ነው የረዥም ጊዜ ዕቅዳችን። ለነገሩ የረዥም ጊዜ ዕቅድ የዐሥር ዓመት፤  የሃያ ዓመት ገና  እየተዘጋጀ እንጂ  በመንግሥት ጸድቆ ይሄ የሀገራችን  የረዥም ጊዜ [የኅዋ ሳይንስ መርሐ-ግብራችን] ዕቅድ ነው ብሎ አልተሠጠም ገና ነው።»

የኅዋ ሳይንስ በአፍሪቃ ጥቂት በሚባሉ ሃገራት ብቻ ተግባራዊ የሆነ ዘርፍ ነው። ደቡብ አፍሪቃ፣ ግብጽ እና ናይጀሪያ በኅዋ ሳይንስ ከአፍሪቃ የሚጠቀሱ ሃገራት ናቸው። የኢትዮጵያ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንሥቴር መሥሪያ ቤት በዕቅዱ መሰረት ከ3 እስከ አምስት ዓመታት ሳተላይት ማምጠቅ ይሳካላት ይሆን? ጊዜ የሚፈታው ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ