1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ እና የፀጥታው ምክር ቤት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 21 2008

ኢትዮጵያ በአብላጫ ድምፅ የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የተለዋጭ አባልነት መቀመጫ አገኘች። ዛሬ ኒውዮርክ ውስጥ በተከፈተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በተካሄደው የድምጽ አሰጣጥ ስርዓት ላይ ኢትዮጵያ አፍሪቃን ወክላ የቀረበች ብቸኛ እጩ ነበረች ።

https://p.dw.com/p/1JF8Q
USA UN Vollversammlung in New York
ምስል Getty Images/K. Betancur

[No title]

ይሁንና፣ ኢትዮጵያ ተለዋጭ አባል ለመሆን ከጠቅላላ ጉባኤው ሦስት አራተኛውን ድምጽ ማግኘት ነበረባት፣ በዛሬው ጠቅላላ ጉባዔ ኢትዮጵያ ከ193 አባል ሀገራት የ185 ን ድጋፍ አግኝታ ነው የተለዋጭ አባልነት መንበር የፀደቀላት። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዛሬ ኒውዮርክ ውስጥ በጀመረው ጠቅላላ ጉባኤ ድምፅ የሚሰጠው በፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አምስት የተለዋጭ አባላት መቀመጫዎችን ለመያዝ በእጩነት በቀረቡ ሃገራት ላይ ነው ። በዙር የሚደርሰውን ይህን መቀመጫ ለመያዝ ኢትዮጵያ አፍሪቃን ወክላ በብቸኛ እጩነት ቀርባለች ። ሦስት የአውሮፓ እና ሁለት የእስያ ሃገራትም የተለዋጭ አባልነት መቀመጫ ለማግኘት እየተፎካከሩ ነው ። የተመድ መሥራች አባል የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፉት 70 ዓመታት ሁለት ጊዜ ብቻ የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባል ሆኖ አገልግላለች ። ይህም በአፄ ኃይለ ሥላሴ እና በደርግ ዘመነ መንግሥታት ነው ። አቶ አበበ አይነቴ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ስልታዊ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ ይህን ቦታ ዛሬ ካገኘት ለሃገሪቱ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል ይላሉ ። ይህንንም በሦሶት ይከፍሉታል ።
በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ በምክር ቤቱ ውስጥ ያገለገለችው ከዛሬ 26 ዓመት በፊት ነው ። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊው 2013/2014 ራስዋን ለዚህ ቦታ በእጩነት የማቅረብ ፍላጎት የነበራት ቢሆንም ያኔ ቦታውን ለሩዋንዳ ሪፐብሊክ ለቃለች ። የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የተለዋጭ አባልነት መቀመጫ ለማግኘት የምትጠባበቀው ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በፕሬስ ነፃነት አፈና በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት እና የፕሬስ ነፃነት ተሟጋች ድርጅቶች ተደጋጋሚ ወቀሳ የሚቀርብባት ሃገር ናት ።በዚህ የተነሳም ሃገሪቱ በምክር ቤቱ የሚጠበቅባትን ሃላፊነት መወጣቷን የሚጠራጠሩ እና ቦታውም አይገባትም ሲሉ የሚከራከሩ ወገኖች አሉ ። የአፍሪቃ ህብረት ኢትዮጵያ ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት በእጩነት እንድትቀርብ ያጸደቀው በዚህ ዓመት በጥር ወር በተካሄደው 26 ተኛው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነበር ።

UN Hauptquartier New York
ምስል Getty Images

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ