1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የዋጋ ግሽበት በመንግሥት ሰራተኛው ላይ በርትቷል

ረቡዕ፣ ጥቅምት 15 2010

በኢትዮጵያ ገበያ የግንባታ እቃዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ አልባሳት እና የምግብ ሸቀጦች ጭምር የዋጋ ጭማሪ እያሳዩ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት የዋጋ ጭማሪውን በአስተዳደራዊ እርምጃዎች እቆጣጠራለሁ ቢልም ዘላቂ መፍትሔ መሆኑ ግን ያጠራጥራል።

https://p.dw.com/p/2mSQN
Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

የዋጋ ጭማሪ የግብይት ሥምምነቶች አፍርሷል

የኢትዮጵያ መንግሥት ብር ከዶላር አኳያ የነበረውን የምንዛሪ ተመን ባዳከመ ማግሥት የመሰረታዊ ሸቀጦች፣ የግንባታ ግብዓቶች እና ተሽከርካሪዎች ዋጋ ላይ ልዩነት ተፈጥሯል። ልዩነቱ ቀደም ብለው ቀብድ የተከፈለባቸውን የግብይት ሥምምነቶች አፍርሷል። የግብይት ሥምምነታቸው ከፈረሰባቸው መካከል የአዲስ አበባው ነጋዴ አቶ ሞሐመድ ኢብራሒም ይገኙበታል።

"ኮሮላ ልንገዛ ፈልገን 410 ሺሕ ብር ልንገዛ ተስማምተን ልክ በሁለተኛው ቀን ዶላር ጭማሪ ሲያደርግ አፈረሱት። የሰጠናቸውንም ቀብድ መለሱ። ለምንድነው ስንላቸው ዶላር ስለጨመረ የመኪና ሻጮች እንዳንሸጠው ከልክለውናል፤ይጨምራል ብለውናል ነበር ያሉን። 420 ሺሕ ብር ሁሉ ብንሰጣቸው እምቢ አሉ።"

አቶ ሞሐመድ ኢብራሒም እንደሚሉት በኢትዮጵያ ገበያ ላይ የዋጋ ጭማሪ የተከሰተው ባገለገሉ መኪኖች ላይ ብቻ አይደለም። የአዳዲሶቹም ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።

"አዳዲስ የሚገቡ መኪኖችን አሁን አብዛኞቹ ነጋዴዎች መሸጥ አይፈልጉም። ወደ ፊት ያለውን ገበያ አይተው ነው መሸጥ የሚፈልጉት። ቀብድ ተቀብለው የነበሩት አንዳንዶቹ አፍርሰዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ ቢያንስ 30 እና 40 ሺህ ብር ዋጋ ጨምረዋል።"

Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

ቀብድ ተቀብለው ለተዋዋሉት ሥራ የሚጠቀሙባቸው ግብዓቶች ዋጋ በድንገት ቢያሻቅብም ምን ያደርጋሉ? የወረዒሉው የእንጨት እና ብረታ ብረት ባለሙያ አቶ ሰዒድ የሆኑት እንዲያ ነው።

"ሳይጨምር በፊት ቀብድ እንቀበልና ይጨምራል ብለን ስላላሰብን እቃ ሳንገዛ ቀረን።" የሚሉት አቶ ሲዒድ በር እና መስኮቶች፣ የእቃ መደርደሪያ ቁም ሳጥኖች እና አልጋዎች ከእንጨት እና ከብረት ይሰራሉ። ብር ከዶላር አኳያ የነበረው የምንዛሪ ተመን ከተዳከመ በኋላ ግን ለሥራቸው በግብዓትነት የሚገለገሉባቸው እንጨቶች እና ብረቶች ዋጋ ጨምሯል። ከደንበኞቻቸው የተቀበሏቸውን ትዕዛዞች በዋጋ ጭማሪው ምክንያት መመለስ ባለመቻላቸው በኪሳራ ለመስራት መገደዳቸውን የሚናገሩት ባለሙያው "እኔ በምኖርበት አካባቢ የጨመረው ሁሉም ነው። አንድ ላሜራ 250 ብር ነበር የምንገዛው። አሁን ግን በአንድ ጊዜ የ100 ብር ጭማሪ አሳይቶ በ350 ብር ነው የምንገዛው። ባለ 18፣ ባለ 12 እና ባለ 3 የሚባል ኤም ዲ ኤፍ ጣውላ አለ። ባለ 3 የሚባለው 160 ብር ነበር የምንገዛው አሁን 200 ብር ገብቷል። ያው ዶላር ጨመረ ብለው ነው እንግዲህ ዋጋ የጨመሩት።" ሲሉ ያክላሉ።

ሰሜን ሸዋ መኮይ ከተባለች አነስተኛ ገበያ ቀድሞ የመንግሥት ሰራተኛ የነበሩት አቶ ሮቤል ከበደ የአልባሳት ነጋዴ ከሆኑ ከራረሙ። በሱቃቸው ለገበያ የቀረቡ አልባሳት ከ50-70 ብር ጭማሪ እንዳሳዩ የሚናገሩት አቶ ሮቤል ከደንበኞቻቸው "ለምን" የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ አርቦላቸዋል።

"በቅርብ ልብስ ላመጣ ደሴ ሔጄ ነበር። ዋጋ ጨምሮ ነው ያገኘሁት። ስጠይቃቸው ምንዛሪ ስለጨመረ እኛ ልብሶችን የምናመጣበት ዋጋ ጨምሯል ነው ያሉኝ። ቦዲ ለምሳሌ 150 እና 160 ይሸጡ የነበሩትን ከደሴ ያመጣሁት በ200 ብር ነው። እኔ የምሸጠው 230 እና ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል። 350 ብር የነበሩ ሱሪዎች ደግሞ ወደ 400 ከፍ ብለዋል።"

ከብረት እስከ እንጨት ከሚስማር እስከ ቆርቆሮ የዋጋ ጭማሪ ያስከተለው የኢትዮጵያ መንግሥት ብር ከዶላር አኳያ የነበረውን የምንዛሪ ተመን ለማዳከም ያሳለፈው ሳኔ ነው። ሰሜን ወሎ ዞን ጋዞ ወረዳ 140 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ቅጠል ቆርቆሮ ወደ  170 ብር አሻቅቧል። የባትሪ ድንጋይ ከ8 ብር ወደ 10 ብር ከፍ ብሏል። ጤፍ፣ ዘይት እና ስኳርም መሰረታዊ የዋጋ ለውጥ ታይቶባቸዋል። የዋጋ ጭማሪው ክርን የበረታው ደግሞ በገጠር ነዋሪ እና የመንግሥት ሰራተኛው ላይ ነው።

Straßenszene in Harar, Äthiopien
ምስል Z. Abubeker/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ የፖሊሲ አውጪዎች እና የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች የብር የምንዛሪ ተመን መዳከም የዋጋ ግሽበት ያስከትላል አያስከትልም በሚለው ጉዳይ ላይ ያላቸው ሐሳብ የተለያየ ነው። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለ ማርያም "ከብሔራዊ ባንክ ፖሊሲ አውጪዎች እንደተሰማው የዋጋ ጭማሪ ሊያስከስት የሚችል ማክሮ ኤኮኖሚያዊ ምክንያት አሁን ላይ የለም። ስለዚህ የዋጋ ጭማሪ አንጠብቅም ሲባል ነበር። ሌሎች የኤኮኖሚ ተንታኞች ደግሞ አሁን ካለው የማክሮ ኤኮኖሚ ሁኔታ፤ ዓለም አቀፍ የገበያ ሁኔታ እና አገሪቷ ገቢ ምርቶች ላይ ጥገኛ ከመሆኗ አንፃር አንድም የዋጋ ውድነትን ይመጣል ብሎ የመጠበቅ አዝማሚያ እና እውነተኛ በገበያ ላይ የሚንጸባረቅ የዋጋ ጭማሪ ሊኖር ይችላል የሚል አንድምታ  ሲሰማ ቆይቷል። አሁን እንደምናየው ግን የዋጋ ጭማሪ ሊኖር ይችላል የሚለው መላምት ወደ እውነታ እየተቀየረ ያለ ነው የሚመስለው።" ሲሉ ይናገራሉ። አቶ ጌታቸው እንደሚሉት የምንዛሪ ተመን ለውጡ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ምን ያክል የዋጋ ለውጥ ያስከትላል የሚለውን ማስላት እንኳ አዳጋች ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን በአስተዳደራዊ እርምጃዎች ለመቆጣጠር ማቀዱን አስታውቋል። የንግድ ሚኒሥቴር ምኒሥትር ድዔታ አቶ አሰድ ዚያድ አዲስ አበባ ላይ "ይሔን አጋጣሚ ተጠቅሞ አለአግባብ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ዋጋ መቆለል አይቻልም።" ሲሉ አስጠንቅቀዋል። "ይኼንን ሕገ-ወጥ ድርጊት የሚከተል አካል ካለ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ይቀጥላሉ። እሸጋው ስረዛው ይቀጥላል። ስለዚህ በዲቫልዌሽኑ ምክንያት ኢንፍሌሽን መፈጠር የለበትም።"

 የኢትዮጵያ መንግሥት በአስተዳደራዊ ቅጣት ሊቆጣጠር የሚሻው ያለ አግባብ ዋጋ የጨመሩበትን ብቻ አይደለም።  ከርሞ ከሚመጣ የዋጋ ለውጥ ትርፍ ለማግኘት የቋመጡትን ጭምር እንጂ። የዋጋ ግሽበት ይለመዳል?

በተመን ለውጡ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ እቃዎች ዋጋ መጨመር የማያከራክር ጉዳይ ቢሆንም ቀድመው በገቡት ላይ የታየው ግሽበት ግን ነጋዴዎችን የሚያስወቅስ ድርጊት ሆኖ ይታያል። አቶ ሞሐመድ ኢብራሒም የኢትዮጵያ መንግሥት እወስዳለሁ የሚለው አስተዳደራዊ እርምጃ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ተሰምቷቸዋል።

Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

"ከዚህ በፊት በነበረው ልምድ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ዋጋ ይጨምራል እንጂ ቀንሶ አያውቅም። ሲጨምር አንዴ እንጮኻለን፤ ከጮኽን በኋላ እንለምደዋለን ዝም እንላለን። ወደ ፊትም ይጨምራል እንጂ ይቀንሳል የሚል ሐሳብ የለኝም።"

መሰረታዊ የኤኮኖሚ አላባውያን ግሽበት የመፍጠር እድል ስላላቸው አሁን የሚወሰዱ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ዘላቂ መፍትሔ ሊሆኑ እንደማይችሉ የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ይናገራሉ። አጋጣሚዎች ሲገኙ ብዙ ትርፍ ለማትረፍ ያለውን ባሕሪ በመቀነስ ረገድ ግን የተወሰነ አስተዋፅዖ ሊኖራቸው እንደሚችል እምነታቸው ነው። እርሳቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሰውም ሆነ በግዙፍ የመዋዕለ ንዋይ ሥራዎች ላይ የተሰማራው መንግሥት በመሆኑ የበጀት አስተዳደር ፖሊሲ ግሽበትን ለመቆጣጠር ቁልፍ ሚና ይኖረዋል።

"የበጀት ፖሊሲው የተመጠነ በኤኮኖሚው ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ ላያሟሙቅ በሚችል መልኩ ከተገደበ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ተገቢ ያልሆኑ፤መጠቀም ላይ መሰረት ያደረጉ ኢንቨስትመንቶችን በመቀነስ በአጠቃላይ በበጀት ፖሊሲ አወጣጥ ሥርዓት ውስጥ መቆጠብን ግምት ውስጥ ያስገባ የገንዘብ ፖሊሲ መከተል የምንችል ከሆነ ብቻ ነው የግሽበት ተፅዕኖውን መቋቋም የሚቻለው።"

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ