1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን የተፈራረሙት ስምምነት

ረቡዕ፣ መጋቢት 23 2007

ኢትዮጵያ፤ግብጽና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የተፈራረሙት ስምምነት የመወደሱን ያክል ዛሬም ድረስ እያወያየና እያከራከረ ነው ። የግብጽ ጋዜጦች የስምምነቱን መፈረም በደስታ የመቀበላቸውን ያህል ትችቶችም እየሰነዘሩ ነው።

https://p.dw.com/p/1F1VL
Ägypten Äthiopien Damm am Nil
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

በጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር 2013 የኢትዮጵያ እና ግብጽ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሻከረበት ጊዜ ነበር። የቀድሞው የግብጽ ፕሬዝዳንት መሀመድ ሙርሲ ከከፍተኛ ሹማምንቶቻቸው ጋር በተገኙበትና በበቴሌቭዥን የቀጥታ ስርጭት በተላለፈ ውይይት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በ4.2 ቢሊዮን ዶላር የምትገነባውን ግድብ ለማስተጓጎል የሃይል እርምጃን እንደ አማራጭ ያነሱበት ውይይት ደግሞ ዋንኛው ምክንያት ነበር። በዚያን ወቅት የዛሬው የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ የአገሪቱ የጦር አዛዥ ነበሩ። ምን አልባት የፕሬዝዳንት ሙርሲ ከፍተኛ ሹማምንት በአማራጭነት ያቀረቡት የሃይል እርምጃ ተግባራዊ ሊሆን ቢችል በበላይነት የሚያስፈጽሙት የቀድሞው ፊልድ ማርሻል የዛሬው ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ነበሩ።

ፕሬዝዳንት ሲሲ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ አገራቸው በአባይ የውሃ አጠቃቀምና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበትን እሰጥ አገባ ማርገብ ችለዋል። ፕሬዝዳንቱ መጋቢት 14/2007 ዓ.ም. በሱዳን ካርቱም የተፈራረሙት ቅድመ ስምምነት ሊጠቀስ ይችላል። በጀርመን የልማት ማዕከል ተጋባዥ ተመራማሪ የሆኑት ራውያ ቶፊቅ «ስምምነቱ አለመግባባቶቹን ሙሉ በሙሉ የሚፈታ ፈር ቀዳጅ ወይም በቅኝ አገዛዝ ዘመን በናይል ውሃ አጠቃቀም ላይ እንደተፈረሙት ስምምነቶች ሌላ ኢ-ፍትሃዊ ስምምነት ነው ማለት አይቻልም።ማመቻመች ማለት ነው። በሁለቱ መካከል ያለ ነው። በዚህ መርህ ላይ ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ስለምትገነባው ግድብ ስለሚደረጉ ትብብሮች የሚያወሱ አንቀጾች አሉት።»ሲሉ ይናገራሉ።

Karte Nil Verlauf und Renaissance-Staudamm Englisch

አሁን ሁለቱ አገሮች የተፈራረሙት ሰነድ አገሮቹ ተቀራርበው ልዩነታቸውን መፍታት የሚችሉበት እድል ፈጥሯል እንጂ ሙሉ በሙሉ አልፈታም። ለዚህም ይመስላል የግብጽም ይሁን የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በያሉበት የሰነዱን አዎንታዊ እና አሉታዊ መልክ እንደ የአገሮቻቸው ጥቅም ሊተነትኑ የሚሞክሩት። ራውያ ቶፊቅ አሁን በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባውን ግድብ አስመልክቶ የተፈረመው ቅድመ ስምምነት ወደ ጥልቅ ቴክኒካዊ ስምምነቶች ማደግ እንደሚኖርበት ይናገራሉ።

«ይ ያሁኑ ቅድመ ስምምነት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ለምትገነባው የህዳሴ ግድብና ወደፊትም ለምትገነባቸው ሌሎች ግድቦች ጥልቅ ቴክኒካዊ ትንታኔና ስምምነት መተርጎም ይኖርበታል። በዚህም ኢትዮጵያ የምትገነባቸው ግድቦች ሶስቱን የምስራቅ ናይል አገሮች እኩል ተጠቃሚ ያደርጋሉ? ወይስ በሌሎቹን አገሮች በተለይም ግብጽን ወደ ጎን በመተው ለኢትዮጵያ ልማት ብቻ ያገለግላሉ የሚለውን ለማወቅ እንችላለን።»

ኢትዮጵያ፤ሱዳንና ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የተፈራረሙት ስምምነት አስር መርሆዎች አሉት። ራውያ ቶፊቅ ስምምነቱን አስመልክቶ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ያሏቸው ሁለት ነጥቦች አሉ።

Ägypten Nil Gizeh Pyramide Kairo
ምስል AP

«የመጀመሪያው ነገር ይህ ስምምነት የሶስቱን አገሮች መልካም ፈቃድ የሚያሳይ እጅግ ሰፊ ስምምነት ነው። አስገዳጅ ነገር የለውም።ሶስቱ አገሮች ግድቡ በመጀመሪያው አመት ውሃ የሚሞላበትን ሁኔታ እና አጠቃላይ ግድቡን በተመለከተ በሚሰሩት ጥናቶች ላይ ለመተባበር ተስማምተዋል።። ሌላው ኢትዮጵያ ጥናቶቹ በሙሉ ከመጠናቀቃቸው በፊት የመገንባቱን ሂደት እያከናወነች ነው። ጥናቶቹ ከመጠናቀቃቸው እና አማካሪ ተቋማቱ የሚያቀርቡት ቴክኒካዊ ምክረ ሃሳብ ላይ የሶስቱ አገሮች ባለሙያዎች ወደ ፊት እንዴት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ሳይስማሙ በፊት ምንም አይነት አስገዳጅ ስምምነቶች ሊኖሩ አይችሉም።»

ኢትዮጵያ ለግብጽ ያደላል የሚባለውና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1929 በታላቋ ብሪታኒያ የተፈረመው የናይል የውሃ ክፍፍል ስምምነት እንዲቀየር ትፈልጋለች። ኢትዮጵያ በ3.1 ቢሊዮን ዩሮ የምትገነባው የታላቁ ህዳሴ ግድብ 6,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል ተብሏል። የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ለግድቡ ግንባታ የወንዙ ፍሰት በተቀየረበት ወቅት መካረር መጀመሩ አይዘነጋም። አሁን የተፈረመው ስምምነት ለሻከረው ግንኙነት መሻሻል በር ቢከፍትም በአባይ ወንዝ የውሃ ክፍፍል፤ ግድቡን ለመሙላት በሚወስደው ጊዜና ከተፈጥሯዊ ፍሰቱ የሚቀንሰው የውሃ መጠን ላይ ከስምምነት አልተደረሰም።

እሸቴ በቀለ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ