1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢጋድ ደቡብ ሱዳንን አስጠነቀቀ

ሰኞ፣ ኅዳር 1 2007

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት ባለሥልጣን በምህጻሩ ኢጋድ እንደሚቀጣቸው በድጋሚ አስጠነቀቀ። አስፈላጊ ከሆነም ኢጋድ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል ዝቷል። የደቡብ ሱዳን አማፂያን በበኩላቸው የደቡብ ሱዳን መንግስት ስምምነቱን ጥሶ ውጊያ ከፍቶብናል ሲሉ ከሰዋል።

https://p.dw.com/p/1Dkui
Südsudan - Abkommen
ምስል Reuters
የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት አዲስ አበባ ውስጥ ቅዳሜ ዕለት ያደረጉትን ስምምነት ካላከበሩ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ማዕቀብ እንደሚጥልና ጣልቃ እንደሚገባ አስጠነቀቀ። የኢጋድ አባል ሃገራት መሪዎች ማስጠንቀቂያውን ያስተላለፉት ሐሙስ፣ጥቅምት 27 እና በነጋታው አርብ አዲስ አበባ ውስጥ ያካሄዱትን 28ኛው የመሪዎች ልዩ ስብሰባ ተከትሎ ነው። ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘው የዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች ተንታኝ አንድሪው አታ አሳሞሃ ኢጋድ ውሳኔው ካልተከበረ ከማስጠንቀቂያ ባለፈ ሊንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።
«የሚፈፀመው ነገር ላይ ጣልቃ ለመግባት ማዕቀብ ወሳኝ ነው። ደቡብ ሱዳንን አስመልክቶ የአካባቢው ሃገራት ማዕቀብ ተመራጭ ነው። ኢጋድ ጠረጴዛ ላይ ያቀረባቸው አማራጮች ተግባራዊ ካልሆኑ የተፋላሚው ኃይላት ንብረቶች እንዲታገዱ፣ የጉዞ ማዕቀብ እንዲጣል፣ እንዲሁም የጦር መሣሪያ አቅርቦት እንዲቋረጥ መወሰን ይኖርበታል፤ ከእዛም ባሻገር ውሳኔው ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ መግፋት አለበት»
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪርምስል Reuters
የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የጦር መሣሪያ እና ሌሎች ለጦርነት የሚውሉ ቁሳቁሶችን እንዳያገኙ፣ የንብረት ዝውውራቸው እንዲታገድ፣ የጉዞ ማዕቀብ እንዲጣልባቸው ሊያደርግ እንደሚችል ኢጋድ ዝቷል። ተፋላሚ ኃይላቱ
ነፍጥ አንስተው እርስ በእርስ መገዳደል ከጀመሩ ድፍን አንድ ዓመት ሊሞላቸው አንድ ወር ቢቀራቸው ነው። ተፋላሚዎቹ ተኩስ ለማቆም በተደጋጋሚ ስምምነት ቢያደርጉም ቃላቸውን ሲጠብቁ ግን አልታዩም።«እስካሁን እንደተመለከትነው ከሆነ ቀደም ሲል የተደረጉ ስምምነቶች እውን አልሆኑም። እንደውም ጥሰቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ 11 ወራትን አስቆጥሯል። አሁንም የምናወራው ግን ከጠብ አጫሪነት ስለመቆጠብ ስምምነት ነው። በእዚህ መልኩ ከቀጠለ ጠበኝነትን ለማስቀረት ያደረጉት ስምምነት ይከበራል ብሎ አመኔታ መጣል እጅግ አስቸጋሪ ነው።»
የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ከ11 ወራት በፊት በጀመሩት ውጊያ እስካሁን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አልቀዋል፤ ኹለት ሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል። የደቡብ ሱዳን መንግስት እና ተፋላሚ ኃይላቱ ዛሬም ግን ዛሬም ይወቃቀሳሉ። የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር እና የአማፂያኑ መሪ ሪክ ማቻር ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ተገናኝተው ቢስማሙም፤ ከሠዓታት በኋላ የደቡብ ሱዳን አማፂያን የመንግስት ጦር ጥቃት አደረሰብን ሲሉ ወቅሰዋል። የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚንስትር ጦርነቱን ለማቆም መንግስት ቁርጠኛ ነው ብለዋል። ሆኖም ይኽ ፈጣን መወቃቀስ የኢጋድ ውሳኔ ወደፊት ተግባራዊ ስለመሆኑ ጥርጣሬ አጭሯል።
የደቡብ ሱዳን የአማፂያኑ መሪ ሪክ ማቻር
የደቡብ ሱዳን የአማፂያኑ መሪ ሪክ ማቻርምስል Reuters
«ቃላቸውን መጠበቃቸውን በተመለከተ ከፍተኛ ጥርጣሬ ካጫሩት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ግጭቱ በተፈጠረበት ቦታ ላይ የሚገኙ ተፋላሚዎች በርካታ መሆናቸው ነው። ምንም እንኳን መሰረታዊ መርኆዎችን ለማክበር አዲስ አበባ ላይ ቁርጠኝነቱ ቢገለጥ፤ ለተግባራዊነቱም መግለጫ ቢሰጥ የምር ለማስተግበር ግን ኢጋድ ይቸግረዋል። ምክንያቱም የተፋላሚዎቹ በርካታ ወኪሎች እና ወታደሮች በቦታው የሚያደርጉትን የቀን ተቀን እንቅስቃሴ አይከታተሉም። ያ አስቸጋሪ ያደርገዋል።»
የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት በ28ኛው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት (ኢጋድ)የመሪዎች ልዩ ስብሰባ የተስማሙባቸው አጀንዳዎችን ለማማከሪያ በጠየቁት መሰረት የ15 ቀናት የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸዋል። ተፋላሚ ኃይላቱ በተሰጣቸው ቀነ-ገደብ ሁሉን አቀፍ የሥልጣን ክፍፍል ሽግግር እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት ጠቅሷል። በቃላቸው ይፀኑ እንደኾን ግን የሚታወቅ ነገር የለም።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ