1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤልኒኞ እና አፍሪቃን የጎዳዉ ድርቅ

ማክሰኞ፣ የካቲት 15 2008

በአፍሪቃ ቀንድ እና በደቡባዊ አፍሪቃ አካባቢ በሚገኙ ሃገራት የዝናብ መታጣት ያስከተለዉ ድርቅ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ለምግብ እጥረት እና ረሀብ ዳርጓል። የአየር ጠባይ ለዉጡ ኤልኒኞ በተሰኘዉ ክስተት መባባሱ ነዉ የሚነገረዉ።

https://p.dw.com/p/1I0Nl
Simbabwe Dürre Maisfeld
ምስል picture alliance/Photoshot

ኤልኒኞ እና አፍሪቃን የጎዳዉ ድርቅ

ይህ ክስተት ዓመታት እያሰለሰ የሚመጣ፤ የሚያስከትለዉ ተፅዕኖም ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። አስቀድሞ አለመዘጋጀት በርካታ ሃገራትን አሁን ለምግብ ርዳታ ልመና አብቅቷል።

በአሁኑ ወቅት ዚምባብዌ፣ ማላዊ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ ሞዛምቢክ፣ ኢትዮጵያ ባጠቃላይ በደቡባዊ አፍሪቃ እና በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ የሚታየዉ ድርቅ ከፍተኛ ችግር እንደሚያስከትል ይታሰባል። በርካቶች ቀደም ሲል ያመረቱትን የምግብ እህል በመጨረሳቸዉ አሁን ቤተሰባቸዉን የሚመግቡትን ለመሸመት ዶሮዎች እና ከብቶቻቸዉን ለመሸጥ እንደተገደዱ ሞዛቢክ ዉስጥ የሚገኘዉ ኬር የተሰኘዉ የርዳታ ድርጅት ዳይሬክተር ማርክ ኖስባህ ይናገራሉ።

«ሌላዉ የተመለከትኩት በርካታ ሰዎች ከገጠማቸዉ የምግብ እጥረት የተነሳ ቤተሰቦቻቸዉን ለመመገብ ሲሉ አሁን ዶሮዎች፣ ፍየሎች እና ላሞችን እየሸጡ ነዉ። አብዛኛቾዉ ቤተሰቦችም አሁን ከሞላ ጎደል በቀን አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ ነዉ ለመብላት የሚችሉት።»

Simbabwe Geier Esel
በዚምባቡዌ ኤሊኞ ያስከተለዉ ድርቅምስል Reuters/P. Bulawayo

ኖስባህ እንደሚሉት 170 ሺህ ሞዛቢካዉያን የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። እንደ ድርጅቱ መረጃም በደቡባዊ አፍሪቃ ሃገራት ባጠቃላይ ወደ14 ሚሊየን ህዝብ ለከፋ የረሀብ አደጋ ተጋልጧል። በደቡብ አፍሪቃ አካባቢ ሃገራት ከሰላሳ ዓመታት በላይ በተደረገዉ ክትትል መሠረት ከጥቅምት እስከ ታኅሳስ ባለዉ ጊዜ እንዳለፉት ሁለት ዓመታት አነስተኛ ዝናብ የታየበት ወቅት እንደሌለ የተመ የዓለም የምግብ መርሃግብር ይገልጻል። ለዚህ ደግሞ ኤልኒኞ የተሰኘዉ የአየር ጠባይ ክስተት ተጠያቂ ነዉ። ይህ የአየር ጠባይ ክስተት ከሁለት እስከ ሰባት ባሉ ዓመታት ዉስጥ ተደጋግሞ የሚታይ እንደሆነ ነዉ የሚገለፀዉ። በዘንድሮዉ የክረምት ወራት የታየዉ ግን ካለፉት 35 ዓመታት ካጋጠመዉ የከፋና የተራዘመ እንደሆነ ተነግሯል። ኤሊኞ በተለያየ አካባቢ የተለያየ ተፅዕኖ ነዉ የሚያስከትለዉ። በአንድ ወገን ከደቡብ ፓስፊክ የመጣዉ የሙቀት ማዕበል በበርካታ አካባቢዎች የተጠናከረ ዝናብ እና ጎርፍን አስከትሏል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ እና ኬንያ አንዳንድ አካባቢዎች ይህ ይታያል። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ጭራሽ ዝናብ የሚባል የለም። ኢትዮጵያ ዉስጥ ድርቁና የጎርፍ መጥለቅለቁ በአንድነት ነዉ የተከሰቱት። ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ እስካሁን አስር ሚሊዮን የሚሆኑ ወገኖች የርዳታ ምግብ ጠባቂዎች ሆነዋል። በቀጣይ ወራትም ቁጥራቸዉ ወደ18 ሚሊየን ከፍ ሊል እንደሚችል የርዳታ ድርጅቶች ከወዲሁ ስጋታቸዉን ገልጸዋል። ኤሊኞ ሲከሰት አስቀድሞ ይታወቃል። ተደጋግሞ ሲያጋጥምም ታይቷል። የሚያስከትለዉን መዘዘዝ ካለፈዉ በማገናዘብ አስቀድሞ በመዘጋጀት መቀነስ አይቻልም ወይ? በካናዳ ካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ የሚያተኩረዉ ዘርፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ጌታቸዉ አሰፋ ያብራራሉ። ዝርዝሩን ከድምፅ ዘገባዉ ይከታተሉ።

Infografik El Niño Erklärgrafik Englisch
የኤሊኞ ክስተት ሥዕላዊ ገለፃ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ