1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤርትራና RSF፧

ሐሙስ፣ ኅዳር 26 2000

ዋና ጽህፈት ቤቱ፧ ፓሪስ፧ ፈረንሳይ የሚገኘው በዓለም ዙሪያ ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው፧ ድንበር አያግዴው የጋዜጠኞች ድርጅት (RSF) የአውሮፓው ኅብረትና የአፍሪቃ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ጉባዔ የፊታችን ቅዳሜ፧ ሊዝበን፧ ፖርቱጋል ውስጥ ከመጀመሩ በፊት፧ የኤርትራ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ አፈ-ወርቂና ረዳቶቻቸው፧ ወደአውሮፓ ኅብረት አገሮች እንዳይገቡ የሚል ጥሪ ዛሬ ማስተላለፉ ተገለጠ።

https://p.dw.com/p/E0a8
ምስል picture-alliance /dpa
ድርጅቱ፧ ለዚህ የሰጠው ምክንያት እ ጎ አ ከ 2001 ዓ ም አንስቶ፧ በኤርትራ የሰብአዊ መብትና የፕረስ ነጻነት ይዞታ፧ አሳሳቢ ነው የሚል ነው። ከዚህም ሌላ ድርጅቱ፧ በትናንቱ ዕለት፧ የ 54 ዓመቱን ጎልማሣ ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ሥዩም ፀሐዬን፧ የዓመቱ ጋዜጠኛ ሲል ዕውቅና ሰጥቶታል። ተክሌ የኋላ ዝርዝሩን አጠናቅሯል።
ጋዜጠኛ ሥዩም ፀሐዬ፧ (RSF) እንደዘገበው፧ ኤርትራ ውስጥ በዱር በገደል ውጊያ ይካሄድ በነበረበት ወቅት አብሮ የተሳተፈ ተዋጊ ነበረ። ያኔም ነበር፧ ከጋዜጠኛነት ሙያ ጋር የተዋወቀው። ስለተዋጊዎች፧ አጫጭር ፊልሞችና ፎቶግራፎች በማንሳት ከሠራና፧ ኤርትራ ራሷን የቻለች ነጻ አገር ሆና ከቆመች በኋላም፧ የቴልቭዥንና ራዲዮ ክፍል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ነብ። እ ጎ አ ከመስከረም 2001 ዓ ም በፊት፧ የቀድሞ ታጣቂ ወንድሞቹን፧ «አምባገነናዊ አገዛዝ አመጣችሁ« እያለ ይነቅፍ ስለነበረ፧ በቀላሉ ዒላማ ለመሆን ቻለ። ዘንድሮ፧ የዓመቱ ጋዜጠኛ ለመባል የበቃውም፧ በዚህ ሳቢያ ነው ሲሉ፧ የዶቸ ቨለ የሃውሳው ክፍል ባልደረባ ራቢ ግዋንዱ ያነጋገረቻቸው የ RSF የአፍሪቃ ክፍል ኀላፊ Leonard Vincent አስረድተዋል። Vincent 15 ኤርትራውያን ጋዜጠኞች፧ ሥዩም ፀሐዬ ጭምር፧ ዘመድ-ወዳጅ፧ ማንም እንዳይጎበኛቸው ተደርጎ እንደታሠሩ ናቸው ሲሉ የገለጡ ሲሆን፧ በህይወት ይኑር-አይኑር የሚያውቁት እንደሌለም ተናግረዋል።
«በህይወት ይኑር-አይኑር፧ የምናውቀው የለም፧ ማብራሪያም አላገኘንም። ዬት እንዳለ፧ ዬት እንደታሠረ፧ ጤንነቱ፧ እንዴት እንደሆነ(በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ) አናውቅም። ይህ ሲጠየቅ፧ የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት አንዳች ማብራሪያ መሥጠት አይፈልጉም።«
በድንበር አያግዴው የጋዜጠኞች ድርጅት (RSF)፧ የእርሱ የዓመቱ ጋዜጠኛ መባል እርሱ፧ በሚገኝበት ሁኔታ ለሚገኙ ያለው ትርጉም ምንድን ነው? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ፧
«እንደሚመስለኝ፧ በመጀመሪያ በኤርትራ ውስጥ ያለውን ይህን መሰል አሳዛኝ ሁኔታ እንዲተኮርበት ያደረጋል። እኛም ጠቃሚ አድርገን የምናየው ይህን ነው። የጋዜጠኞቹ ሁኔታ፧ የተረሱ አለመሆናቸውንም እንዲያውቁ ለማድረግ ነው። ይህ በኤርትራ ለሚኖሩ ብቻ ሳይሆን ስለሚወዷቸው ዘመዶቻቸው ምንም ዓይነት ዜና ለሌላቸው የቤተሰብ አባላትም ይጠቅማል።«
ድንበር አያግዴው የጋዜጠኞች ድርጅት፧ ቀደም ሲል በመግቢያችን ላይ እንደጠቀስነው፧ በእሥራት ላይ የሚገኘውን ኤርትራዊ ጋዜጠኛ፧ ሥዩም ፀሐዬን የዓመቱ ጋዜተኛ ተብሎ እንዲታወስ መምረጥ ብቻ ሳይሆን፧ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂና ረዳቶቻቸው፧ ወደ አውሮፓው ኅብረት አገሮች እንዳይገቡ፧ እንዲከለከሉ ሲል፧ ጥሪ አቅርቧል። በዚህ ጉዳይ ላይ የኤርትራ መንግሥት አስተያየት ምን እንደሆነ የማስታወቂያ ሚንስትሩን አቶ አሊ አብዱን ጠይቀናቸው ነበር።
«እኛ በህዝብ ግንኙነት ሥራ እንካ-ስላንትያ ውስጥ ለመግባት ዝግጁ አይደለንም። ደረጃችንን ዝቅ አድርገን፧ እነርሱ እንደሚያደርጉት ነገር ማካረር ተግባራችን አይደለም፧ ምክንያቱም ለእንዲህ ዓይነቱ ኀላፊነት ለጎደለው አፍራሽ መግለጫ ያን ያህል ትርጉም አንሰጥምና!
በየወሩ ይህን መሰል መግለጫ ካላወጡም፧ ገንዘብ አይከፈላቸውም።ስለዚህ፧ ምቹ ወንበር ላይ ተቀምጠው በሚሠነዝሩት የጉዳዮች ትንተና የሚረኩ ከሆነ፧ ይርኩ፧ ነው ፧ የምንለው። እነዚህ ሰዎች፧ እንዲሁ የስለላ ሠራተኞች ሲሆኑ፧ በጋዜጠኛነት ሽፋን በማሠረግ፧ በሌላ ሉዓላዊ አገር ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ ናቸው።«