1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤርትራውያን ስደተኞች እና የስዊስ መንግሥት ውሳኔ

ረቡዕ፣ የካቲት 4 2007

አንድ ለውሁዳን ጎሳዎች የሚሟገት የጀርመናውያን ድርጅት የስዊትዘርላንድ መንግሥት የተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘላቸውን ኤርትራውያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ወስዶት የነበረውን ውሳኔ ሰሞኑን የሻረበትን ድርጊት አሞገሰ።

https://p.dw.com/p/1EZgb
Italien Flüchtlingsdrama vor Lampedusa
ምስል picture alliance/ROPI

« ገዜልሻፍት ፊውር በድሮተ ፈልከር » የተባለው ድርጅት እንዳመለከተው፣ ስደተኞቹ ይመለሱ በሚባልባት ኤርትራ ውስጥ አሁንም ግዙፍ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ይታያል። በመሆኑም፣ አውሮጳውያን መንግሥታት በኤርትራ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳርፉ እና ከዚችው ሀገር በሚመጡ ስደተኞች አኳያ የሚከተሉትንም ተገን አሰጣጥ መርሕ እንዲያስተካክሉ ድርጅቱ ጠይቋል።

Gesellschaft für bedrohte Völker Logo Grafik

በስዊትዘርላንድ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥት በሀገሪቱ የሚገኙትን ኤርትራውያን ስደተኞችን በተመለከተ የሚከተለውን መርሕ እንዲያጠናክር ባለፉት የመፀው ወራት በመጠየቅ ያካሄዱትን ክርክር ተከትሎ መንግሥት የተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘላቸውን ስደተኞች ወደ ትውልድ ሀገራቸው ለመላክ ወስኖ ነበር። ግን፣ ይኸው ውሳኔው የስደተኞቹን ሕይወት ስጋት ላይ መጣል ማለት መሆኑን ብዙ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በማመልከት ጠንካራ ተቃውሞ ካሳረፉበት በኋላ ርምጃውን እንደገና ማጤን መገደዱን ነበር « ገዜልሻፍት ፊውር በድሮተ ፈልከር » የተባለው ድርጅት ኃላፊ ኡልሪኽ ዴልዩስ ያስታወቁት።

« ክርክሩን ተከትሎ የስዊትዘርላንድ ብሔራዊው የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት አንድ የልዑካን ቡድን ወደ ኤርትራ በመላክ ከሀገሪቱ መንግሥት እና ከሌሎች ተቋማት ጋ ስለ ሰብዓዊ መብቱ ይዞታ ተነጋግሮዋል። ቡድኑ በኤርትራ በድብቅ ያካሄደውን ተልዕኮ አብቅቶ እንደተመለሰ እና በሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ አንዳችም መሻሻል አለመታየቱን ካረጋገጠ በኋላ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት እና የፍትሕ ሚንስቴር የተገን ማመልከቻቸው ውድቅ የሆነባቸውን ስደተኞች ወደ ኤርትራ ላለመላክ ይከተሉት በነበረው መርሓቸው ለመፅናት ወሰኑ። »

Bundesplatz in Bern, Schweiz
ምስል picture alliance/dpa
Ulrich Delius
ምስል Gesellschaft für bedrohte Völker

የስዊስ መንግሥት ይህን ውሳኔ የደረሰው ኤርትራውያን ከሀገራቸው የሚሰደዱበትን መንሥዔ የተመለከተው ጉዳይ በሌሎች አውሮጳውያት ሀገራትም ውስጥ በጣም ማነጋገር በያዘበት ጊዜ በመሆኑ፣ ኤርትራውያን በግዳጅ መመለስ የሌባቸውም በሚል የመብት ተሟጋቾች የሚያሰሙትን አቋም ያጠናከረ አዎንታዊ ሂደት ነው ሲሉ ዴልዩስ አሞግሰዋል። እንደሚታወሰው፣ የዴንማርክ መንግሥት የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት የኤርትራ ሰብዓዊ መብት ይዞታ ተሻሽሎዋል ሲል ባለፈው ታህሳስ ወር ያወጣው ዘገባ ሀገሪቱ ስደተኞችን ላለመቀበል የምታደርገው በኤርትራ ያለውን ገሀዱን የማያንፀባርቅ ጥረት ነው በሚል ብርቱ ወቀሳ ነበር የተፈራረቀበት። እንደ ዴልዩስ አስተያየት፣ የአውሮጳ መንግሥታት በአዳጋቹ የባህር እና የየብስ ጉዞ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል ተገን ፍለጋ የሚመጡትን ስደተኞችን ላለመቀበል የማከላከል ርምጃ በመውሰድ ፈንታ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እና በኤርትራ መንግሥት ላይ ጫና ማሳረፍ ይገባቸዋል።

« የአውሮጳ ህብረት የኤርትራን ጉዳይ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውይይቶች ላይ በማንሳት ሊመክርበት ይገባል፣ ከዚህ በተጨማሪም የኤርትራ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ይዞታውን እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚተክልበትን ሁኔታ እንዲያሻሽል ማሳሰብ ይጠበቅበታል ብለን እናስባለን። እስካሁን እንደምናየው ግን ኤርትራውያኑ ስለሚሰደዱበት ምክንያት ውይይት አይደረግም። በኤርትራ ለምን ባለፉት 30 ዓመታት ሁኔታው አልተሻሻለም? ለምን የሰብዓዊ መብት ይረገጣል? የአውሮጳ ህብረት ሁኔታውን በመመርመር ፈንታ ለምንድን ነው አንዳንድ ጥሪ በማቅረቡ ላይ ብቻ ራሱን የሚገድበው? በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለውን ግንኙነት አይመለከቱም። በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ባለው ውዝግብ ላይ አዘውትረው የኢትዮጵያ መንግሥትን አቋም ነው የሚወስዱት። እና የኤርትራ መንግሥት አመራር ራሱን ያገለለበትን ርምጃ እየደገፉ ነው። ይህ ደግሞ በጣም ያሳዝናል። ለዚህ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ለቀጠለው መጥፎ ውዝግብ ከኤርትራ አመራር ጋር የይስሙላ ያልሆነ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ከማሳሰብ አልቦዘንም። በመሆኑም፣ በውዝግቡ መንሥዔ ላይ በማትኮር መፍትሔ መሻቱ ትርጉም ይኖረዋል። »

እና፣ የስዊስ መንግሥት ተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘላቸውን ኤርትራውያን ወደ ሀገራቸው ላለመመለስ አሁን የወሰደው ርምጃ በሌሎች የአውሮጳ ሀገራት የተገን አሰጣጥ ፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ይችል እንደሆን ለቀረበላቸው ጥያቄ ዴልዩስ ሲመልሱ እንዲህ ነበር ያሉት።

« አዎ፣ ምክንያቱም ፣ በእጃችን ያሉትን መረጃዎች ስንመለከት፣የዴንማርክ የስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት ተሻሽሎዋል በሚል ያወጣው ዘገባ መሠረተ ቢስ ነው። ውሳኔው ስደተኞችን ወደሀገራቸው መመለስ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩን የሚያሳይ ነው። ስደተኞች የመቀበል አለመቀበል ጉዳይ ለአውሮጳ በጠቅላላ ችግር በመሆኑ፣ በዜርትራ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ለሚሻሻልበት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባዋል። »

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ