1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤቦላን ለመግታት የሚደረግ ትግልና የአፍሪቃ መንግሥታት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 2007

በምዕራብ አፍሪቃዉያኑ ሃገራት ማለትም በሴራሊዮን በጊኒና ላይቤርያ የኤቦላ ወረርሽኝ ስርጭት አሁንም አልተገታም። ናይጀርያዊዉ የተዋሐሲ ጉዳዮች ጥናት ባለሞያ ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በምዕራብ አፍሪቃ የኤቦላ ተዋሐሲ ጨርሶ አለመጥፋት ዋና ምክንያት የአፍሪቃዉያኑ ዉሳኔ ሰጭዎች የአሠራር ጉዳይ ነዉ፤

https://p.dw.com/p/1E5OH
Oyewale Tomori
ምስል Privat

አፍሪቃዉያኑ ባለስልጣናት ለህዝባቸዉ ከማሰብ ይልቅ ለግል ህይወታቸዉ ይጨነቃሉ ፤ በቂ እንቅስቃሴም አላደረጉም ሲሉ ተናግረዋል።

«የጤና ክብካቤ በአፍሪቃ» በሚል ርዕስ ፣ ዳሬሰላም ታንዛንያ ላይ ኅዳር 9 እና 10 በተካሄደዉ ጉባኤ የመንግሥታት ተጠሪዎች እና የኤኮኖሚ ባለሞያዎች ተገኝተዋል። በጉባኤዉ ላይ «በአህጉር አፍሪቃ የኤቦላ ተዋሐሲ ያስከተለዉን ከፍተኛ ጉዳት በተመለከተ ምን ዓይነት ትምህርትን መዉሰድ ይኖርባታል» «በጤና ክብካቤ ረገድ አፍሪቃ ያላትን አቅም እንዴት መገንባትስ ትችላለች?» በሚለዉ ነጥብ ላይ ተወያይቷል። በሀገሪቱ ያሉት የግል የጤና ተቋማት የኤቦላ ተዋሐሲ መዛመትን ለመግታት ምን ሚና መጫወት ይችሉ ይሆን? ለሚለዉ ጥያቄ ናይጀርያዊዉ የተዋሐሲ ጉዳዮች ባለሞያዉ ኦይዋሌ ቶሞሪ ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ መንግሥት ራሱ የተዋሐሲዉን መከላከያ መርፌ መሥራት አይችልም ነዉ ያሉት

Ebola Freetown Christos Stylianides Vytenis Andriukaitis European Union Helfer
ምስል European Union

«ዋናዉ ነገር እዚህ ላይ መንግሥታት በራሳቸዉ መከላከያ መርፌን መስራት አይችሉም። አዉሮጳ ዉስጥ ይህ ጉዳይ እንዴት እንደሚሰራበት አይተናል። የቫይረስ መከላከያ መርፊ ምርትን አቅራቢዉ አምራች ኢንዱስትሪዉ ነዉ። መንግሥት መስራት ያለበት ህጋዊ የሆኑ ጉዳዮችን ብቻ መሟላታቸዉን መከታተል ነዉ፤ ለምሳሌ መርፊ ዉስጥ ያለዉ የመድሃኒት በትክክለኛ ሁኔታ መሟላቱንና መመሩትን እና ለተጠቃሚ በህጋዊ ሁኔታ መልቀቁን በመሳሰሉት ጉዳዮች፤ ግን በርካታ የአፍሪቃ መንግሥታት በመድሃኒት መርፌዉ ምርት ላይ ሁሉ እጃቸዉን አስገብተዉ መሳተፍ ይፈልጋሉ። ምልክንያቱም ከምርቱ በስተጀርባ ከመድኃኒቱ ንግድ እኛም ገንዘብ እናገኛለን የሚል ተስፋን ይሰንቃሉ። ከዚህ ነገር ሁሉ ግን እጃቸዉን ማንሳት ይኖርባቸዋል። ለዚህም ነዉ፤ አምራች ኢንዱስትሪዉን ማምረት ትችላለህ ብሎ ለማሳየት ፤ እንዲህ አይነቱ ጉባኤ መደረጉ አስፈላጊ የሚሆነዉ»

የጉባኤዉ ተሳታፊዎች የኤቦላ ተዋሐሲን በተመለከተ፤ በአፍሪቃ መንግሥታት ላይ ከፍተኛ ወቀሳን አሰምተዋል፤ ይህ ለምን ይሆን? ለሚለዉ የዶቼ ቬለ ጥያቄ የናይጀርያዊዉ የተዋሐሲ ጉዳዮች ባለሞያዉ ኦይዋሌ ቶሞሪ እንዲህ ይላሉ፤ « በጊኒ ዉስጥ የመጀመርያዉ የኤቦላ ተዋሐሲ አደጋ የታየዉ በታህሳስ ወር በጎርጎረሳዊዉ 2013 ዓ,ም ነዉ። ግን ዓለም ይህን ጉዳይ ያወቀዉ ሶስት ወር ዘግይቶ ነዉ። አንድ ጥሩ የቅድምያ ማስጠንቀቅያ አሰራር ቢኖረን ኖሩ ጉዳዩን ቶሎ መፍትሄዉን ቶሎ እንደርስበት ነበር። ይህን ጉዳይ ደግሞ በብዙ መንግሥታት ናቸዉ ችላ ያሉት። ወረርሽኙ የኤቦላ ተኅዋሲ መሆኑ ታዉቆ እንኳ መንግሥታት ኤቦላ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል። አልያም ይህ የኛ ችግር አይደለም ችግሩ የጊኒ ወይም የሴራሊዮን ነዉ ብለዉ ተናግረዋል። አሁን ተዋሐሲዉ በየቦታዉ ከተሰራጨ በኋላ ታድያ ሥርጭቱን ለመግታትና ለመቆጣጠር አልተቻለም። ይህ የአሁኑ ሁኔታ ሊከሠት የቻለዉ ደግሞ በወቅቱ ምንም መከላከያ አለማድረግና የዝግጅት ጉድለት ጥምረት ዉጤት ነዉ።» የኤቦላ ተዋሐሲ ከተዛመተባቸዉ ሃገራት መካከል፤ በከፋ ድህነት ላይ እንዲሁም ከሃገራቱ መካከል ለዓመታት በጦርነት ዉስጥ የነበሩ ይገኙበታል። ምናልባት ይህ አደገኛ ተዋሐሲ በከፍተኛ ፍጥነት ሊዛመት የቻለዉ በነዚህ ሁለት ነጥቦች ይሆን? የናይጀርያዊዉ የተዋሐሲ ጉዳዮች ባለሞያዉ ኦይዋሌ ቶሞሪ መልስ አላቸዉ፤

«እኔ ሁልጊዜ የማቀርበዉ ጥያቄ ሃገራቱ እንዴት እንዲህ ድሆች ለመሆን በቁ ስል ነዉ። እንደ ሴራልዮንና ላይቤርያ ያሉት ሃገራት ለምን ጦርነት አካሄዱ? ለሆነ ኅብረተሰብ ጥቅም ወይስ ለአልማዝ ጥሬ ሃብት ነዉ የተዋጉት! በአፍሪቃ ስለ ድህነት ሲታሰብ ይህንን ጉዳይ ማሰብም ያስፈልጋል። የአፍሪቃ ዉስጥ ድህነት ምክንያት ቅድምያ የሚሰጣቸዉን ነገሮች እና ጉዳዮች ለይቶ አለማወቅ ነዉ። አንድ መንግስት ለነዋሪዉ ማቅረብ ያለበት የመጨረሻ ነገር አለ ለምሳሌ የህክምና ጣቢያን የመሳሰለ ነገር። ወይም የኤቦላ ተዋሐሲ በታየባቸዉ ሃገራት ህሙማንን ለሚረዱ ያለክፍያ የላስቲክ የእጅ ጓንቲ ማቅረብ» ግን በዚህ ግዜ የመንግስት ተጠሪዎች የተመድ ስብሰባን ለመካፈል በሚል በኒዮርክ በሚገኝ ምርጥ ሆቴል ይቀመጣሉ። ታድያ እዚህ ላይ ጥቃቄዉ የድህነት ሳይሆን ፤ ገንዘብ ወጪ የሚሆነዉ በምን ላይ ነዉ የሚለዉ ይሆናል። ይህን ችግር እስካ ላስወገድን ድረስ፤ እንደተለመደዉ ማማረራችንን እንቀጥላለን። አፍሪቃ ደሃ ናት፤ እኛ ግን ደሃ አይደለንም። በአፍሪቃ ዉስጥ ቅድምያ የምንሰጠዉ ትክክለኛ ላልሆነ ነገር ነዉ »

Ebola Conakry European Union Helfer
ምስል European Union/Kenzo Tribouillard

በአካባቢዉ ላይ የሚገኙት የዓለም የጤና ድርጅት ሰራተኞች የኤቦላ ተዋሐሲን ለመግታት እየሰሩ መሆናቸዉ ነዉ የተገለፀዉ። ይህ ድርጅት ምን ያህል እየሰራ ይሆን? እንደ ናይጀርያዊዉ የተዋሐሲ ጉዳዮች ባለሞያዉ ኦይዋሌ ቶሞሪ ድርጅቱ በትጋት የሚንቀሳቀስ ቢሆን ኖሮ አሁን ያለንበት ደረጃ ባልደረስን ነበር ባይ ናቸዉ።

« ድርጅቱ በብርቱ ቢንቀሳቀስ ኖሮ ፤ አሁን የሚታየዉ ሁኔታ ባልተከሰተም ነበር። በ90ዎቹ ዓመታት የኤቦላ ተኀዋሲ በኮንጎ መዛመት ሲጀምር ፤ በአፍሪቃ ሃገራት ሁሉ ተግባራዊ የሚደረግ አንድ ፀረ- ተዋሐሲዉን እንቅስቃሴ ለማድረግ መረሃ-ግብርን አወጣን። እንደ ተዋሐሲ ጉዳዮች ባለሞያ እኔም በመረሃ-ግብሩ ላይ ተሳታፊ ነበርኩ። የዛን ጊዜ እንደተናገርኩት ታድያ ይህ ስኬታማ የቅድመ ማስጠንቀቅያ መረሃ-ግብር ሊኖረን የሚችለዉ ከነዚህ ነገሮች ሳናስገባ ስንቀር ነዉ። ይህ ደግሞ የስልጣን ሽኩቻ ፤ የፖለቲካ ልዩነቶችን ሁሉ ያካትታል። »

እዚህ ላይ ኦይዋሌ ቶሞሪ የፖለቲካ አቋም ትልቅ ሚና አለዉ ማለታቸዉ ይሆን ?

«እንደኔ እምነት ትልቁ ችግር መንግስት ለሁሉም ነገር ነፃና - ግልፅ ትንታኔን መስጠት ባለመፈለጉ እና የቅድሚያ ማስጠንቀቅያ መረሃ-ግብር ላይ በቂ ገንዘብ ባለመመደቡ ነዉ። በቅድሚያ ማስጠንቀቅያ መረሃ ግብር ላይ የሚፈስዉ ወጭ ወረርሽኙን ለማጥፋት ወይም ለመዋጋት ከሚወጣዉ ወጭ በጣም ዝቅ መሆኑ እሙን ነዉ»

በኤቦላ ተዋሐሲ የተጎዱ ሃገሮች መንግሥታት ከዚህ የኤቦላ ተዋሐሲ መዛመት ችግር ምን ሊማሩ ይችላሉ፤ ለሚለዉ ጥያቄ ናይጀርያዊዉ የተዋሐሲ ጉዳዮች ባለሞያዉ ኦይዋሌ ቶሞሪ፤ « ይህ የጎላ ችግር በመከሰቱ ምክንያት አንድ ትልቅ ለዉጥ ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ። ትክክል የሚያስብ እያንዳንዱ ፖለቲከኛ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ከዚህ በኋላ ፈፅሞ ሊከሰት አይገባዉም ብሎ በቁርጠኝነት መናገር መቻል አለበት። በርግጥ ይህ ሊሆን የሚችለዉ ደግሞ ችግሩን ለመቅረፍ ገንዘብ ወጭ ለማድረግ ዝግጁ ሲኮን ብቻ ነዉ። የሰዎችን መሠረታዊ ጤና ለመጠበቅ ገንዘብ ወጭ መሆን አለበት፤ ወጭ የሆነበት የጤና ሁኔታ ደግሞ ስኬታማ መሆን ይኖርበታል። ይህ ደግሞ ለሁሉም ግልፅ ነዉ »

የኤቦላ ተዋሐሲ ሥርጭትን ለመግታት በሚደረገዉ ጥረት ከአደጉት ሃገራት ምን ሁኔታን ይጠብቃ? ለሚለዉ ጥያቄ ኦይዋሌ ቶሞሪ ሲመልሱ?

«የኤቦላ ተዋሐሲ የተሰራጨባቸዉ ሃገሮች በአሁኑ ሰዓት ከአዉሮጳ ሕብረት ሃገራት እና ከዩኤስ አሜሪካ በርካታ ርዳታን እያገኙ ነዉ። ቢሆንም ርዳታ አቅራቢዎቹ የሚሰሩት በራሳቸዉ መረሃ-ግብር ነዉ። በኤቦላ የተጎዱት ሃገሮች ርዳታዉን ለማንቀሳቀስ እና እንዴት ርዳታዉ መሰራጨት እንዳለበት ለመናገር ምንም አይነት ስልጣኑ የላቸዉም። ሕክምና ማዕከሉ የሚሰሩት ምሁራን ስራቸዉን ሲጨርሱ ሻንጣቸዉን ሸክፈዉ ሀገሪቱን ለቀዉ ይሄዳሉ። ግን እነዚህ ባለሞያዎች ወደየመጡበት ተመልሰዉ ሲሄዱ የኤቦላ ተዋሐሲን ለመዋጋት የተገነባዉ የሕክምና ማዕከል በቀጣይ ስራዉን እንዴት ያከናዉናል? መንግስታቱስ ይህ የሕክምና ማዕከል ፣ ስራዉን እንዲቀጥል ለማድረግ የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ይኖራቸዋል? ርዳታስ ብናገኝ እንዴት አድርገን ነዉ ማዕከሉ በቀጣይነት ስራዉን እንዲሰራ ማድረግ የምንችለዉ ብለንም እኮ ማሰብ መቻል ይኖርብናል። የራሳችንን ባለሞያዎችን ለማሰልጠን ገንዘብ ከማዉጣት ይልቅ፤ ከዉጭ ሃገር በመጡ ባለሞያዎች ላይ ራሳችንን ጥገኛ አድርገናል። ይህ ደግሞ የርዳታ አቅራቢዉ ሃገር ችግር ሳይሆን ይህ የአፍሪቃዉያኑ ችግር ነዉ። እንደሁልግዜዉ ሁሉ ሌላዉ መጥቶ ችግራችንን እስኪፈታልን ድረስ እንጠብቃለን። ይህን ትምህርት ነዉ ከዚህ ልንቀስም የሚገባን። ይህ ሁኔታ ከአስር ዓመት በኋላ እንደገና ቢከሰት ምንም አይደንቀኝም»

Medeor Ebola Behandlungszentrum in Liberia
ምስል DW/J. Kanubah

ይንን ጉዳይ በተመለከተ የናይጀርያዊዉ የተዋሐሲ ጉዳዮች ባለሞያዉ ኦይዋሌ ቶሞሪ ከአፍሪቃዉያኑ ምሁራን ምንን ይጠብቃሉ ?

« የፖለቲካዉ አሰራር እና አስተዳደር ትክክል አይደለም! የሚሉ ጠንካራ ወኔ እና ድፍረት ያላቸዉ በርካታ ሰዎች ያስፈልጋሉ። ለምሳሌ እንዳለመታደል ሆኖ የኔ የሆነዉ የናይጀርያ መንግስት የሚሰማዉ፣ መስማት የሚፈልገዉን ነዉ። በአፍሪቃ እጅግ በርካታ ጠንካራና ብልህ ሰዎች አሉ ግን እየተፈፀመ ያለዉን ነገር ዐይናቸዉን ጨፍነዉ ነዉ ማለፍ የሚፈልጉት። መንግስት እኛን ይsሻል እኛም መንግስትን እንዋሻለን አሁን ግን ሰዎች በጥንካሪ ተነስተዉ በቃ! ማለት መቻል አለባቸዉ። በጣም ብዙ ተጎድተናል። የፖለቲካ አመራሮችን ሳይሆን መዉደድ ያለብን ሃገራችንን ነዉ። አለበለዝያ ግን ለመድረስ የፈለግንበት ዓላማ ላይ መድረስ አንችልም» የናይጀርያዊዉ የተዋሐሲ ጉዳዮች ባለሞያዉ ኦይዋሌ ቶሞሪ በናይጀርያ የምርምር አካዳሚ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ በዲሞክራቲክ ኮንጎ በጎርጎረሳዉያኑ 1995 ዓ,ም ኤቦላ ተዋሐሲ ስርጭት ሲከሰት በዲሞክራቲክ ኮንጎ በዓለም የጤና ድርጅት ዉስጥ ቅርንጫፍ ዉስጥ በማገልገላቸዉ ይታወቃሉ። የለቱ ጤናና አካካቢ ዝግጅታችን እስከዚሁ ነበር ለመሰናዶዉ አዜብ ታደሰ ነኝ ጤና ይስጥልኝ!

አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ