1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤቦላ ያስከተለዉ መገለል

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 25 2007

በኤቦላ ወደተጠቁት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ደርሰዉ የሚመለሱ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ለተወሰኑ ቀናት ተገልለዉ እንደቆዩ የሚደረጉ ርምጃዎች አዎንታዊ ምላሾችን እያስተከሉ አይደለም።

https://p.dw.com/p/1Dglf
Chinesische Helfer in Liberia 23.10.2014
ምስል picture-alliance/Xinhua/Landov

በተለይ በዩናይትድ ስቴትስ ጊሊ፣ ላይቤሪያ እንዲሁም ሴራሊዮን ዉስጥ በኤቦላ እየተሰቃዩ የሚገኙ ወገኖችን በሙያቸዉ ሲረዱ ቆይተዉ የተመለሱ የጤና ባለሙያዎች ይህን ርምጃዉ በበጎ አልተመለከቱትም። የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦችም ድርጊቱ ሌሎች ወደእነዚህ አካባቢዎች ሄደዉ በሙያቸዉ የአቅማቸዉን እንዳያደርጉ እንቅፋት እንደሚሆን ስጋታቸዉን በግልፅ ተናግተዋል።

የኤቦላ ተሐዋሲ ከተዛመተበትና ከፍተኛ ጉዳት ካስከተለባቸዉ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ዉጭ በአዉሮጳና ዩናይትድ ስቴትስ 19 ሰዎች በተሐዋሲዉ ተይዘዉ ህክምና ተደርጎላቸዋል። ወይም አሁም እየተደረላቸዉ ነዉ። አብዛኞቹ ታዲያ አንድም የጤና ባለሙያዎች ናቸዉ አንድም የእርዳታ ሠራተኞች ናቸዉ ወደምዕራብ አፍሪቃ ሃገራቱ በመሄድ በተሰለፉበት መስክ አገልግሎት ሲሰጡ በዚህ በሽታ የተያዙት። በቅርቡ ሴራሊዮን ዉስጥ በኤቦላ ተይዘዉ ለህክምና የተላኩት የተመድ ባልደረቦች ናቸዉ። እነዚህ ሰዎች ፓሪስ አቅራቢያ በሚገኝ ሃኪም ቤት ዉስጥ ከፍተኛ ጥበቃና ክትትል እየተደረገላቸዉ እንደሚገኙ የፈረንሳይ ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል። ቀደም ሲልም አሜሪካ ዉስጥ ከሐምሌ መጨረሻ አንስቶ እስከጥቅምት አጋማሽ ድረስ ዘጠኝ ሰዎች በኤቦላ ተይዘዉ አንዱ ህይወቱን ሲያጣ ሌሎቹ ድነዋል ቀሪዎቹም ህክምና ላይ ይገኛሉ። ስፔን ዉስጥ ሶስት ታመዉ ሁለቱ ህይወታቸዉን አጥተዋል። ፈረንሳይ ዉስጥ ሁለት ታማሚዎች አንዱ ድኗል ሌላኛዉ ህክምና ላይ ናቸዉ። ብሪታንያ አንድ ዜጋዋ ታሞ ሲድን ጀርመን ዉስጥ ሲታከሙ ከነበሩ አንዱ ሲድን ሌላዉ ህክምናዉ ቀጥሏል አንድ ደግሞ ህይወቱን አጥቷል። ኖርዌይ የእርዳታ ሠራተኛ የነበረ ዜጋዋ በኤቦላ ተሐዋሲ ቢያዝም ታክሞ መዳኑ ተነግሯል። ምንም እንኳን የኤቦላ ተሐዋሲ ወረርሽኝ የተቀሰቀሰዉ ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ ቢሆንም ለህክምናም ሆነ ለእርዳታ ተግባር ወደዚያ ያቀኑት የድንበር የለሽ ሃኪሞች፤ የዓለም የጤና ድርጅት፤ የአሜሪካን የበጎ አገልግሎት ባልደረቦች በተሐዋሲዉ በመያዛቸዉ ወደየሀገራቸዉ ተወስደዉ፤ አንዳንዶችም የሌላ ሀገር ዜጋ ቢሆኑም የተሻለ ህክምና ወዳለበት እየተወሰዱ በተደረገላቸዉ የህክምና እርዳታ ተሐዋሲዉን አሸንፈዉ ነፍሳቸዉ ተርፎ እነሱም በአደባባይ የምስጋና አየር ሲተነፍሱ ታይተዋል። ይህን ያስተዋሉት የቀድሞዉ የተመድ ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ኤቦላን የድሆች በሽታ ብለዉታል። እንደእሳቸዉ ትዝብት እንደዉም በሽታዉ ከበለፀጉት ሃገራት በአንዱ ዉስጥ ተከስቶ ቢሆን ኖሮ ምላሹ አሁን ከምናየዉ የተለየ ይሆን ነበር።

Sonderisolierstation
ምስል picture-alliance/dpa/Federico Gambarini

«በሽታዉ ከአፍሪቃ ይልቅ በሌላ ስፍራ የተከሰተ ቢሆን ኖሮ በሽታሽን ለመቆጣጠር የሚወሰደዉ ርምጃ እጅግ የፈጠነ ይሆን ነበር። በዚያ ላይ በሽታዉ በበለፀገ ሀገር ተከስቶ ቢሆን ዛሬ መድሃኒት ወይም ክትባት ተገኝቶ እናይ ነበር። ስለኤቦላ ላለፉት 40 ዓመታት እናዉቃለን። የድሀ በሽታ ነዉ። እናም አንዳንዱ ኩባንያዎቹ ገንዘብ አፍስሰዉ ምርምሩን አካሂደዉ መድሃኒት ቢያቀርቡ ድሀዉ ወገን ሊገዛዉ እንደማይችል ያስባሉ። በዚህ ምክንያትም እኔ የድሆች በሽታ የምላቸዉን በሚመለከት አንዳንዴ በቂ ምርምር ያለማድረግ አዝማሚያ ይታያል።»

ኤቦላ ተሐዋሲ ያደረሰዉና የሚያደርሰዉ ጉዳት ከምንም በላይ የሰዉን ልጅ ህይወት መቅጠፉ ዛሬም ስጋትነቱ እንዳለ ነዉ። አንዳንድ ሃገራት ዉስጥ በሽታዉ በተሐዋሲዉ በተያዙ ሰዎች ምክንያት ለቀናት ታይቶ ወዲያዉ ሊቆጣጠሩት መቻላቸዉ ቢነገርም ማለት ነዉ። ከእነዚህ ሃገራት መካከል ናይጀሪያ አንዷ ናት። ማሊ ደግሞ ምንም እንኳን የዓለም የጤና ድርጅት በአሁኑ ወቅት ምንም ዓይነት የኤቦላ ታማሚ እንደሌለባት ቢገልፅላትም በተሐዋሲዉ ተይዞ መጨረሻ ህይወቱ ያለፈች የሁለት ዓመት ሕፃን ልጅ በተጓዘበት የሕዝብ መጓጓዣ የተሳፈሩ ሰዎች የተለየ ክትትል እንዲደረግላቸዉ ጠቁሟል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ እንደገለፁትም 108 ሰዎች ከተጠቀሰዉ በተሳፈረበት ዉስጥ ነበሩ ከእነሱ መካከል ደግሞ 33ቱ የጤና ባለሙያዎች ናቸዉ። ስለበሽታዉ አመጣጥ የሚያጠኑ ባለሙያዎች ታዲያ ሰዎቹ ምንም እንኳን በአንድ መጓጓዣ አብረዉ ቢሳፈሩም ከሕፃኑ ጋ አካላዊ ንክኪ ስላልነበራቸዉ ስጋቱ ያን ያህል እንዳልሆነ አስገንዝበዋል። የሕፃኑ ታላቅ እህት ትኩሳት ቢታይባትም ለጊዜዉ ከወባ በስተቀር የተገኘባት በሽታ የለም። ሌሎች የቤተሰብ አባላትም ትኩሳትም ሆነ ሌላ የበሽታ ምልክት ባይታይባቸዉም ለጥንቃቄ ሲባል በአንድ ሃኪም ቤት ዉስጥ ክትትል እየተደረገላቸዉ ነዉ። ለነገሩ የኤቦላ ተሐዋሲ ምንነቱ እስኪለይ 21ቀናት ተደብቆ እንደሚቆይ የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

Ebola Virus Aufnahme mit Elektronenmikroskop
የኤቦላ ተሐዋሲ በመሣሪያ ጎልቶምስል Reuters/NIAID

ከታማሚ ሰዎች አቅራቢያ የነበሩ ሰዎችን ለጥንቃቄ ገለል አድርጎ የማቆየቱ ርምጃ በዩናይትድ ስቴትስ አንዲት ሌላ የኤቦላ ታማሚን ስታስታምም የነበረች ነርስ ላይ ሊሰራ እንዳልቻለ ሰሞኑን ሲነገር ተሰምቷል። ነርሷ ከቤቷ እንዳትወጣ ቢነገራትም ምንም የህመም ስሜት እንደሌላት በመግለፅ የቁም እስር ያለችዉን ርምጃ ተጋፍታ በጎዳና ብስክሌት ስታሽከረክር ታይታለች። ጋዜጠኞችም መቀርጸ ድምፃ ካሜራቸዉን ይዘዉ ሲከታተሏት ዉለዋል። ነገሩ ግራ የሚያጋባ ይመስላል። የሰዉም አስተያየት በሁለት ወገን የተከፈለ መስሏል አንዱ እሷ ጥንቃቄ ማድረጓን ስላመነች ሊሆን እንደሚችል ሲገምት በተቃራኒዉ ግን ነርሷ ለራሷም ሆነ ለሌሎች ህይወት ግድ የሌላት ናት የሚል ትችትን አስከትሎባታል። ያንን በይፋ የተቃወሙ ወገኖች ይህ ርምጃ ሌሎች የኤቦላ ታማሚዎችን ከመርዳት እንዲቆጠቡ የሚያደርግ ነዉ ሲሉ አዉግዘዉታል። ይህን አስተያየት ከሰጡት ከዋነኞቹ መካከልም ኮፊ አናን አንደኛዉ ናቸዉ።

Dousseyni Daou Hospital in Kayes Mali Ebola Kind
ምስል picture-alliance/AP Photo/Baba Ahmed

«በዚህ ጨዋታ ወደፊት ልንሄድበት የሚያስችለን ብቸኛዉ መንገድ የህክምና ባለሙያዎችና መድሃኒቶችን የጫኑ ሄሊኮፕተሮችን ወደስፍራዉ በመላክ ይህን ወረርሽኝ እዚያዉ ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ መቆጣጠር ስንችል ብቻ ነዉ። የጤና ባለሙያዎች በዚህ ገብተዉ እንዳይራዱ የማናበረታታቸዉ ከሆነ በሽታዉን ልቆጣጠረዉ አንችልም፤ ሁላችንም አደጋ ላይ እንወድቃለን።»

እሳቸዉ እንደገለጹትም የኤቦላ ተሐዋሲን ለመከላከል የሚቻለዉ ድንበሮችን በመዝጋት፤ አለያም በሽታዉ ወደተቀሰቀሰበት አካባቢ ሄደዉ በሙያቸዉ የረዱ ወገኖችን አግልሎ በማስቀመጥ እንዳልሆነ በበሽታዉዎች ላይ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማትም ቀደም ሲሉ ገልጸዋል። ምንም እንኳን በአንዳንድ የአሜሪካን ግዛቶች ባለስልጣናት የወሰዱት ርምጃ ለየአካባቢያቸዉ ኗሪ ኅብረተሰብ ጥንቃቄ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ባይካድም በሳይንስ ያልተደረገፈና ተገቢ ያልሆነ እንደሆነ ነዉ የተናገሩት።

«ይህ ተገቢ ያልሆነና ያለመታደል ሆኖ በሳይንስ እንኳ ያልተደገፈ ነዉ። ከዓለም የጤና ድርጅት እና ከአሜሪካን የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ተቋም ዶክተሮች እንዳመለከቱት በሽታዉን በመቆጣጠር ሂደት ሊሠራ የሚችለዉ የመጨረሻዉ አስከፊ ነገር ድንበሮችን መዝጋትና የሚደረገዉ እገዳ እና ሊደረግ የሚችለዉ እርዳታ እንዳይደረግ የማስፈራራት ስጋት ነዉ። እርግጥ ነዉ ባለስልጣናቱ ኃላፊነት ላለባቸዉ ኅብረተሰብ ጥንቃቄ ለማድረግ መሞከራቸዉን እደግፋለሁ። ነገር ግን በእርግጥም ስጋቱ ካለ ኅብረተሰቡን ለማዳን ይህን ስጋት ማስወገድ የሚቻልበት ብቸኛዉ መንገድ ወረርሽኙን ለማቆም ጥረት ማድረግ ነዉ። በተቃራኒዉ የጤና ባለሙያዎችን የሚያስፈራራ አካሄድ የምንጠቀም ከሆነና እነሱም ችግሩ ወዳለበት የማይሄዱ ከሆነ ግን በመጨረሻ በጨዋታዉ ቀድሞ መገኘት አይቻልም።»

US-Krankenschwester Kaci Hickox
ተገልላ እንድትቆይ የተነገራት አሜሪካዊቷ ነርስምስል Reuters

ሴራሊዮን ዉስጥ የምግብ ርዳታ ያልደረሳቸዉ በርካታ ዜጎች ተገልለዉ ከተቀመጡበት ስፍራ ምግብ ለመፈለግ መዉጣታቸዉን ለግብረ ሠናይ ተግባር በስፍራዉ የሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች ዛሬ አመልክተዋል። የኤቦላ ተሐዋሲ ስርጭትን ለመቆጣጠር በሚል በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ከአንድ ሰፊ አካባቢ ሰዎች እንዳይወጡ፤ ወደዚያም ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ወገኖች እንዳይገቡ ለማድረግ ተሞክሯል። በዚህ ስፍራ የሚኖሩ ወገኖችም በየቤታቸዉ እንዲቀመጡነዉ መመሪያ የተላለፈዉ። መንግሥት ከዓለም የምግብ መርሃግብር ጋ በመሆን ምግብና አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ነበር ኃላፊነት የወሰደዉ። የክርስቲያን ኤድ ባልደረባ የሆኑት ጄን ካማራ እንደገለጹት በዛሬዉ ዕለት ምግብ ያልደረሰላቸዉ አካባቢዎች ሲያንኳኩና ድምጻቸዉን ሲያሰሙ ዉለዋል። በሌላ በኩል ፊሊፒንስ ላይቤሪያ ዉስጥ በሰላም አስከባሪነት ተሰማርተዉ የከረሙ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ወታደሮቿ ከዚያ የሚመለሱበት ቀን ስለቀረበ ወደቤተሰባቸዉ ከመቀላቀላቸዉ በፊት ተገልለዉ የሚቆዩበት ስፍራ ማዘጋጀቷን የሀገሪቱ ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ይፋ አድርገዋል። ወታደሮቹ በሚቀጥለዉ ሳምንት ወደሀገራቸዉ የሚመለሱ ቢሆንም ተገልለዉ የቆዩበት ስፍራ ለጊዜ ባለመገለፁ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ባለስልጣናት ገና ለገና ወደእኛ ግዛት ሊመጡ ይችላሉ በሚል ስጋት ይመስላል ተቃዉሞ እያሰሙ ነዉ። እርግጥ ነዉ የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለዉ ላይቤሪያ በኤቦላ ወረርሽኝ ክፉኛ ተጎድታለች። ከ6 ሺህ በላይ በተሐዋሲዉ ተይዘዋል፤ ከሁለት ሺህ የሚበልጡ ደግሞ አልቀዋል። በበሽታዉ ወደተጎዱ አካባቢ ለተለያዩ ግዳጆች ተሰማርተዉ የሚመለሱ ወገኖችን በተለይም የጤና ባለሙያዎችን ሲመለሱ ለቀናት አግልሎ ማስቀመጡ ሌሎች የጤና ባለሙያዎች ለተፈላጊዉ እርዳታቸዉ ወደዚያ እንዳይሄዱ ማከላከሉ እንደማይቀር ኮፊ አናን ያሳስባሉ።

Liberia Ebola Quarantäne Zelt
ተገልሎ የማቆያ ድንኳንምስል Reuters/Ahmed Jallanzo/UNICEF

«እነዚህ የጤና ባለሙያዎች ሴቶቹም ሆኑ ወንዶቹ ወደተፈለጉበት እየሄዱ ክብር የሚገባዉ ተግባር የሚያከናዉኑ የዘመናችን የየዕለት ጀግኖቻችን ናቸዉ። ነገር ግን አንዳንዴ እንዲህ ያለዉ አስተያየት ይሰማል። እናም እንዲህ ባለ አያያዝ እንዲቆዩ መደረጉ እኔ አክብሮት የጎደዉ ነዉ ባይ ነኝ። እነዚህ አስተያየቶች ሲሰሙ ደግሞ ሚስቶች ወይም ባሎችና ልጆች፤ የሙያ እርዳታቸዉን ሊሰጡ ወደዚያ መጓዛቸዉን መቃወም ይጀምራሉ።»

ወደምዕራብ አፍሪቃ ሄደዉ የተመለሱ ብቻ ሳይሆኑ ከዚያ አካባቢ ወደተለያዩ ሃገራት በሚሄዱ ተጓዦች ላይም እገዳ የጣሉ ሃገራት አሉ። በዚህ ምክንያትም ሰሞኑን አሜሪካ ኒዉኦሪሊየንስ ዉስጥ በዚሁ በሽታ ላይ በሚካሄደዉ የባለሙያዎች ዉይይት የሴራሊዮን፤ ጊኒና ላይቤሪያ የጤና ባለሙያዎች መሳተፍ አልቻሉም። ከከተማዋ የጤና ቢሮ የተላከላቸዉ ደብዳቤ 21ቀናት ተገልለዉ እንደሚቆዩ ያመለክታልና።

እርግጥ ነዉ በሽታዉ አደገኛና በቀላሉ ከታማሚዉ ሰዉ ተገቢዉን ጥንቃቄ ወዳላደረጉ ሰዎች መተላለፉ የማይቀር መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም የተመድ እንዳሳሰበዉ በተለይ የጤና ባለሙያዎች ላይ ተግባራዊ ሲሆን የታየዉ የተጋነነ መመሪያ የራሳቸዉን ህይወት ለአደጋ አጋልጠዉ በሙያቸዉ ሰዎችን ለመርዳት የተሰለፉትን ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ የሚያደርግ ነዉ ሲል ተችቶታል። የህመም ምልክት ያልታየባቸዉን ሃኪሞች አግልሎ ማቆየቱ አሉታዊ ዉጤት እንዳያስከትልም ስጋቱን ገልጿል። የአፍሪቃ ኅብረት በቅርቡ በርካታ የጤና ባለሙያዎችን ወደምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ለመላክ መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል። ከዚህ ዉስጥም 200 የሚሆኑት ኢትዮጵያ የምታሰማራቸዉ ይሆናሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ