1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ኤን ፔ ዴ»ን በሕግ የማሳገዱ ጥረት መክሸፉ

ማክሰኞ፣ ጥር 9 2009

በካርልስሩወ ከተማ የሚገኘው የጀርመን ፌዴራል ሕገ መንግሥታዊው ምክር ቤት የቀኝ አክራሪው የጀርመን ብሔራዊ ፓርቲ፣ በምህፃሩ «ኤን ፔ ዴ» በሕግ እንዲታገድ የቀረበውን ማመልከቻ ውድቅ አደረገ። ማመልከቻውን ያስገባው የ16ቱ የጀርመን ፌዴራል ክ/ሃገር ውክልና ም/ቤት፣ ነበር። «ኤን ፔ ዴ»ን ለማገድ ሙከራ ተደርጎ ሲከሽፍ ያሁኑ ሁለተኛው ነው።

https://p.dw.com/p/2Vwax
Deutschland Karlsruhe Entscheidung des Bundesverfassungsgerichts zu NPD-Verbot
ምስል Reuters/K. Pfaffenbach

M M T/ New NPD Verbot gescheitert - MP3-Stereo

የቀኝ አክራሪው  የጀርመን ብሔራዊ ፓርቲ፣ «ኤን ፔ ዴ በሕግ አይታገድም። የካርስስሩወ ፌዴራል ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት በጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓም  የጀርመን ክፍላተ ሀገር ውክልና ምክር ቤት፣  «ቡንድስራት» ያስገባውን ማመልከቻ በዛሬው ውሎው ውድቅ ማድረጉን ችሎቱን የመሩት አንድሪያስ ፎስኩለ አስታውቀዋል። 
«  በሁለተኛው የዳኞች ምክር ቤት አስተያየት መሠረት፣  «ኤን ፔ ዴ» በርግጥ ከሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ጋር የማይጣጣም አጀንዳ ይከተላል፣ ሆኖም፣ በወቅቱ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ያስችለዋል ማለት የሚያደፋፍር ተጨባጭ ክብደት ያለው ማስረጃ በወቅቱ አልቀረበም። » 
ዳኛው ፎስኩለ እንዳስረዱት፣ ምንም እንኳን «ኤን ፔ ዴ» ሕገ መንግሥት ተፃራሪ ዓላማ ቢኖረውም፣ የሀገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመናድ አቅሙ የለውም፣ ዓላማውንም በኃይል ተግባራዊ የማድረግ አሰራር መከተሉንም በማስረጃ ማረጋገጥ አልተቻለም። እርግጥ፣ ፓርቲው በማስፈራራቱ እና ዛቻ በመሰንዘሩ ዘዴ ቢጠቀምም፣ ይህ ለእገዳ እንደማያበቃው ብይኑ አመልክቶዋል። ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት «ኤን ፔ ዴ»  የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት ጥሷል በሚል ፓርቲው እንዲታገድ እና ከመንግሥት የተመደበለት በጀት እንዲቋረጥበት በመጠየቅ የቀረበለትን የ16ቱ የጀርመን ፌዴራል ክ/ሃገር ውክልና ም/ቤት፣ የ«ቡንድስራት» ማመልከቻ  በመረመረበት አሰራሩ ላይ ትኩረቱን ያሳረፈው በተለይ ፓርቲው ምን ያህል በህብረተሰቡ ዘንድ ተፅዕኖ ማሳረፍ ይችላል በሚለው ነጥብ ላይ ነበር። በመጨረሻ በተካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ «ኤን ፔ ዴ»፣  በምክር ቤት ውክልና ለማግኘት ከሚያስፈልገው አምስት ከመቶ ድምፅ በጣም ያነሰ፣ ማለትም ፣ 1,3% የመራጩን ድምፅ ብቻ ነበር ያገኘው ።  
 የዛሬው የካርልስሩወ ችሎት «ኤን ፔ ዴ» ን ለማሳገድ እና የተደረገው ሁለተኛው ሙከራ ነበር። የመጀመሪያው የማሳገጃ  ማመልከቻ በጎርጎሪዮሳዊው 2003 ዓም ነበር የቀረበው። በዚያን ጊዜ ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት፣ የቀረበለት ማስረጃ ተዓማኒ አልነበረም በሚል ውድቅ አድርጎታል። ምክንያቱም፣ መንግሥት መረጃ ለማግኘት የተጠቀመባቸው እና በችሎቱ ወቅትም የምስክር ቃላቸውን የሰጡት አንዳንዳንዶቹ ሰዎች የ«ኤን ፔ ዴ» አመራር አባላት ነበሩ።
በጀርመን ሀገር ካለፉት 60 ዓመታት ወዲህ አንድም ፓርቲ ታግዶ አያውቅም። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲህ እጎአ በ1952 ዓም በምህፃሩ «ኤስ ኤር ፔ» የተባለው የሂትለር ናዚ አራማጅ ተከታይ ፓርቲ፣ በ1956 ዓም ደግሞ በዚያን ጊዜዋ ምዕራብ ጀርመን የኮሚኒስት ፓርቲ በሕግ መታገዳቸው የሚታወስ ነው።  ፓርቲያቸው ሕገ ወጥ ተግባር እንደማያካሂድ የተናገሩት የ«ኤን ፔ ዴ» መሪ ፍራንክ ፍራንስ ከብይኑ በኋላ በሰጡት አስተያየት፣ በሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ብይን እንዳልተገረሙ እና የጠበቁት እንደነበር ገልጸዋል። የቡንድስራት ፕሬዚደንት የራይንላንድ ፋልስ ፌዴራዊ ግዛት ጠቅላይ ሚንስትር ማሉ ድራየር ደግሞ  «ኤን ፔ ዴ»ን ለማሳገድ ቡንድስራት ያደረገው ጥረት ባይሳካም፣ ምክር ቤቱ በማመልከቻው በቀኝ አክራሪው አኳያ የያዘውን የተቃውሞ አቋም ማጠናከሩን አስታውቀዋል።

Deutschland Mainz Malu Dreyer besorgt
ማሉ ድራየርምስል picture-alliance/dpa/A. Dedert
NPD Verbotsantrag
ምስል picture-alliance/dpa

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ