1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤኮኖሚ፤ ብራዚልና አፍሪቃ

ረቡዕ፣ ግንቦት 8 2004

በአፍሪቃ የተፈጥሮ ሃብትና በወደፊት ገበያ ላይ በማለም ከክፍለ-ዓለሚቱ ጋር የኤኮኖሚና የንግድ ትብብራቸውን እያጠናከሩ በመሄድ ላይ የሚገኙት በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ ሃገራት ዛሬ ቻይናና ሕንድ ብቻ አይደሉም።

https://p.dw.com/p/14w55
ምስል Ricardo Stuckert

በአፍሪቃ የተፈጥሮ ሃብትና በወደፊት ገበያ ላይ በማለም ከክፍለ-ዓለሚቱ ጋር የኤኮኖሚና የንግድ ትብብራቸውን እያጠናከሩ በመሄድ ላይ የሚገኙት በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ ሃገራት ዛሬ ቻይናና ሕንድ ብቻ አይደሉም። ብራዚልና ቱርክም እንዲሁ ባለፉት ዓመታት በዚህ ረገድ ከአፍሪቃ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያስፋፉ ነው የመጡት። ቱርክ በረጅም ጊዜ የኤኮኖሚ ሰሌቷ ከአውሮፓው ሕብረት ይልቅ በአፍሪቃና በአረቡ ዓለም ላይ እያተኮረች ስትሄድ የብራዚል የአፍሪቃ ትብብርም በፍጥነት በመራመድ ላይ ይገኛል።

በዚሁ በብራዚልና በአፍሪቃ ግንኙነት ላይ እናተኩርና አትላንቲክ ውቂያኖስ የሚለያቸው ሁለቱ ወገኖች እንደሚታወቀው ለረጅም ጊዜያት ብዙም የጠበቀ ትስስር አልነበራቸውም። ይህ ሲሆንሁለቱን ወገኖች በመሠረቱ ከታሪክ አንጻር የሚያገናኛቸው አንዳች ነገር ጠፍቶ አይደለም። ብራዚል በዓለም ላይ ሁለተኛው ታላቅ ከአፍሪቃ የመነጨ ማሕበረሰብ በሰፊው የሚኖርባት አገር ናት። ይህም የትራንስ አትላንቲኩ የአንዴ የባሪያ ንግድ ውርስ መሆኑ ይታወቃል።

የያኔው ያኔ ነው፤ ብራዚል በወቅቱ ከአፍሪቃ ጋር በንግድም ሆነ በመዋዕለ-ነዋይ ወይም በፖለቲካና በዲፕሎማሲ መተባበሩ ብዙ ጥቅም እንዳለው ተረድታለች። ይሄው የደቡብ-ደቡብ ትብብር እንግዲህ በረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ የተመሠረተ እየሆነ በመሄድ ላይ ነው። ግዙፏ የላቲን አሜሪካ አገር ዛሬ ከቻይናና ከሕንድ ቀጥላ በዓለምአቀፉ የአፍሪቃ ፖሊሲ ላይ ታላቅ ሚና ያላት አዲሷ ሃይል ናት። መለስ ብሎ ለማስታወስ የአፍሪቃ ሃገራት ከአሥር ዓመታት በፊት ምናልባትም በጥሬ ሃብት ከታደሉት ከአንጎላና ከናይጄሪያ ባሻገር በብራዚል የውጭ ፖሊሲ አጀንዳ ላይ ቦታ አልነበራቸውም።

የብራዚል የአፍሪቃ ፖሊሲ በሰፊው የተቀየረው የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚደንት ሉላ-ዳ-ሲልቫ በጎርጎሮሳውያኑ ዓመት 2003 ክፍለ-ዓለሚቱን በመጎብኘት ግንኙነቱን የሚያስፋፋ አዲስ ምዕራፍ ከከፈቱ በኋላ ነበር። የብራዚል የውጭ ንግድ ከዚያን ወዲህ ምንም እንኳ ከግማሽ የሚበልጠው ከአንጎላ፣ ከናይጄሪያና ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ቢሆንም በአምሥት ዕጅ ነው የጨመረው። አዲሱ የብራዚል የአፍሪቃ ፖሊሲ አገሪቱ እያደገ የሚሄድ የተፈጥሮ ፍላጎቷን ለማሟላት እንደ ቻይናና ሕንድ ሁሉ ባሕር ማዶ ማተኮሯን የሚያመለክት ነው። ከፖለቲካ አንጻርም ብራዚል በዓለም የፖለቲካ መድረግ ላይ እያደገ ለሚሄድ ሚናዋ አፍሪቃን መሻቷ ጉልህ ነው።

Angola Staatspräsident Jose Eduardo dos Santos und Luiz Inacio Lula da Silva
ምስል AP

የብራዚል የአፍሪቃ ፖሊሲ ከኤኮኖሚ ስሌት አንጻር ከጥሬ ሃብት ፍላጎት ባሻገር ለአገሪቱ ምርቶች ገበያን ማረጋገጥም ነው። ብራዚል በይፋ እንደምትለው ይህ በአገር ውስጥ አዳዲስ የሥራ መስኮችን ለመክፈትና ድህነትን ለመታገል የሚጠቅም መሆኑ ታምኖበታል። እርግጥ የብራዚል ፖሊሲ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም በጥሬ ሃብት የታደሉትንና በቂ ገበያ ያላቸውን ያስቀድማል። በቋንቋ መሰሎቹን የቀድሞዎቹን የፖርቱጋል ቅኝ ግዛቶች እንኳ ብንወስድ በነዳጅ ዘይት ሃብት ከታደለችው ከአንጎላ በስተቀር ብራዚል ከሌሎቹ ያላት ግንኙነት በባሕላዊ ትስስርና መለስተኛ የልማት ዕርዳት ትብብር ላይ የሚያመዝን ነው።

ያም ሆነ ይህ ዛሬ የብራዚል ኩባንያዎች ሕልውና በአፍሪቃ ከመቼውም በላይ ጎልቶ መታየቱ አልቀረም። ቫሌ የተሰኘው የማዕድን ኩባንያ ሞዛምቢክ ውስጥ ብቻ በቴቴ ክፍለ-ሐገር ከሰል ለማውጣት እስካሁን 1,7 ሚሊያርድ ኤውሮ በስራ ላይ አውሏል። የብራዚል የአፍሪቃ ንግድ ደግሞ በተፋጠነ ዕድገት በእጥፍ ሲጨምር ከ 13 ወደ 25 ሚሊያርድ ዶላር ከፍ ሊል ችሏል። በአንጎላም በከፊል መንግሥታዊ የሆነው ኩባንያ ፔትሮናስ ነዳጅ ዘይት የሚያወጣ ሲሆን ኦዴብሬሽት የተሰኘው የግል ኩባንያ ደግሞ መንግዶችንና የቢሮ ሕንጻዎችን በመገንባት የታወቀ ነው።

ለንጽጽር ያህል የቻይናና የአፍሪቃ የንግድ ልውውጥ መጠን መቶ ሚሊያርድ ዶላርን አልፎ ከሄደ ሶሥት ዓመታት ያህል አልፎታል። የቻይና ኩባንያዎች በአፍሪቃ ምድር ያልገቡበት ቦታና ዘርፍ መኖሩም ያጠራጥራል። ሕንድም ቢሆን ከኢንዱስትሪ እስከ እርሻ ልማት በአፍሪቃ የምታደርገውን መዋዕለ-ነዋይና ንግዷንም እጅጉን እያስፋፋች ነው የምትገኘው። ሌላው ቀርቶ ቱርክ እንኳ የኢንዱስትሪ ምርቶቿን ለመሸጥ ለአፍሪቃ ገበዮች ትልቅ ትኩረት መስጠቷ የተሰወረ ነገር አይደለም።

ቱርክ ከ 2005 ወዲህ ከአፍሪቃ ጋር ያላትን የኤኮኖሚ ግንኙነት ስታጠናክር ወደ አፍሪቃ የምታሰገባቸው ዋነኞቹ ምርቶች የቤት ዕቃዎችና ቁሳቁስ፣ የተለያየ ጨርቃ-ጨርቅ፣ አልባሳት፣ በኢንዱስትሪ የተመረቱ የምግብ ዓይነቶች፣ ብረታ-ብረት የግንቢያ ዕቃዎች፣ ኤሌክትሮኒክ ምርቶች ናቸው። የቱርክ መንግሥት እንደሚለው አገሪቱ በአፍሪቃ የምታደርግው መዋዕለ-ነዋይ በዓመት አንድ ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ይጠጋል። ሂደቱ ደግሞ የተፋጠነ ዕድገት የሚታይበትም ነው።

Trucks in einer Eisenmine Vale Brasilien
ምስል dapd

የብራዚል የኤኮኖሚ እንቅስቃሴም ከቀድሞዎቹ የፖርቱጋል ቅኝ ግዛቶች ባሻገር በደቡብ አፍሪቃም እየጨመረ ሲሄድ ነው የሚታየው። ሆኖም ከአፍሪቃ ጋር የሚደረገውን ንግድና የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት ለማሳደግ በፖርቱጋል ርዕሰ-ከተማ በሊዝበን የአፍሪቃ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ ጀርመናዊው ጌርሃርድ ዛይበርት እንደሚሉት የመንግሥታቱ ተጨማሪ ድጋፍ ግድ ነው የሚሆነው።

«እነዚህ መንግሥታት የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦቱን ምን ያህል በገንዘብ መደገፍ መቻላቸው ወሣኝ ነው። በቻይና ለምሳሌ፤ ኩባንያዎቹ በተለይም መንግሥታዊ ሲሆኑ በአገሪቱ የወጭ ንግድ ባንክ እየተደገፉ ምርት ወደ ውጭ እንደሚሸጡና መዋዕለ ነዋይ እንደሚያደርጉ እናውቃለን። እዚህ ላይ ብራዚልና ሌሎች የላቲን አሜሪካ ሃገራት ገና ብዙ ነው የሚቀራቸው። ተጨማሪ አቅም ያስፈልጋቸዋል»

ይህ ለምሳሌ የብራዚል የልማት ባንክ ፕሬዚደንት ሉቺያኖ ኩቲኞም የሚቀበሉት ሃቅ ነው። በርሳቸው ዕምነትም የሁለቱን ወገን የኤኮኖሚ ትብብር ወደፊት ለማራመድ ገንዘብ ከሁሉም በላይ ወሣኝነት አለው። በዚሁ የተነሣም የብራዚል መንግሥት ለኩባንያዎቹ የብድር አቅርቦቱን ከፍ እንዲያደርግ ይመክራሉ። በሌላ በኩል የብራዚል የአፍሪቃ ንግድ ሁሌ ከክርክር ነጻ የሆነም አይደለም።ለምሳሌ ከብራዚል አፍሪቃ የሚገባው በማቀዝቀዣ ዲፕ-ፍሪዝ የተሰናዳ የዶሮ ቁርጥራጭ ምርት አገሬውን ዶሮ አርቢ የፉክክር አቅም በማሳጣት ከገበዮች በመፈንቀሉ ጥሩ ዝና የለውም። ይሁን እንጂ ከብራዚል ጋር የሚደረገው ትብብር በጥቅሉ በአፍሪቃ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተወዳጅነት አላጣም። እዚህ ላይ ባለፉት ዓመታት በሰፊው እየጨመረ የመጣው የብራዚል የልማት ዕርዳታ ጠቃሚ ድርሻ ሳይኖረው አልቀረም። የአፍሪቃው የኤኮኖሚ ተመራማሪ ጌርሃርድ ዛይበርት እንደሚሉት የብራዚል የልማት ትብብር ዘይቤ ከአውሮፓው በጣሙን ይለያል።

ብራዚል የፊናንስ ዕርዳታ አታቀርብም፤ ለተባባሪዎቹ ሃገራት በጀት የምታደርግው አስተዋጽኦም የለም። ብራዚል ቻይና በአፍሪቃ እንደምታደርገው ለታላላቅ መዋቅራዊ ፕሮዤዎችም ገንዘብ አትሰጥም። የብራዚል ዕርዳታ የሚያተኩረው አፍሪቃውያን ሸሪኮቿ በሚጠይቁትና ራሷም ባላት ዕውቀት ላይ ነው።

«ይህም የሞቃት አካባቢ የሕክምና ዘዴን፣ የእርሻ ልማትን፣ እንዲሁም የትምሕርትና የሕብረተሰብ ዘርፍን ብራዚል ውስጥ ስኬት በታየባቸው በተወሰኑማሕበራዊ ዕቅዶች ማራመድን ይመለከታል። ብራዚል በአፍሪቃ አገሮች ልማትን ወደፊት ለማራመድ ይሄን በዕጇ ያለ ብቃቷን ለመጠቀም የው የምትፈልገው»

Wirtschaft in Afrika
ምስል AP

እርግጥ እስካሁን በልማት ትብብሩ ዘርፍ የተደረገው መዋዕለ-ነዋይ ዝቅተኛ መሆኑ ሲታሰብ ግን ሃሣቡ ትልቅ ፍሬ መስጠቱን ጥቂትም ቢሆን አጠያያቂ የሚያደርግ ነው።«ለምሳሌ ያህል የብራዚል መንግሥታዊ የልማት ድርጅት የኤቢሲ በጀት ከሞላ ጎደል ከአንድ የአውሮፓ ከመንግሥት ነጻ የሆነ ድርጅት ቢመጣጠን ነው»ለማንኛውም አፍሪቃውን በየት በየቱ ዘርፍ ከላቲን አሜሪካ ሊማሩ እንደሚችሉ የቀድሞው የብራዚል ፕሬዚደንት ሉላ-ዳ-ሲልቫ ከሁለት ዓመታት በፊት በኬንያ ጉብኝታቸው እንዲህ ነበር የገለጹት።

«የአፍሪቃ የእርሻ ምድር የማዕከላዊ ብራዚልን የሴራዶን ያህል የእርሻ ልማት ብቃት አለው። የብራዚል ኩባንያዎች ከአርባ ዓመታት በፊት በሴራዶ አካባቢ በአውቶሞቢል የሚያልፉ ታዛቢዎች መሬቱ ዋጋ የለውም፤ ዛፍ እንኳ አያበቅልም ይሉ እንደነበር ያውቃሉ። ግን በተወሰነ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ሴራዶን በዓለም ላይ ታላቁ የዕሕል ቅርጫት እንዲሆን ለማድረግ በቅተናል። በአፍሪቃም ይህን ለማድረግ ይቻላል»

በሌላ በኩል እርግጥ የሉላ አመለካከት የአካባቢ ተፈጥሮ ተንከባካቢዎችን የሚያስደስት አይሆንም። በብራዚል በብዙ ሺህ ካሪኪሎምትር የሚገመት ስፋት ያለው የሁል-ገብ እርሻ መሬት ለአንድ-ወጥ የባቄላ ምርት ሲባል መውደሙ ይታወቃል። ሆኖም ሉላ ለደቡብ ደቡቡ ግንኙነት መጠናከር ወሣኝ አሰተዋጽኦ ማድረጋቸው ሃቅ ነው።

«ምናልባት የሉላን ያህል በሥልጣን ዘመኑ አዘውትሮ የአፍሪቃ አገሮችን የጎበኘ የመንግሥት መሪ አይገኝም። ሌላ የብራዚል ፕሬዚደንትም ቢሆን እንዲሁ! ሉላ በስምንት ዓመታት ውስጥ 12 ጊዜ ወደ አፍሪቃ ሲጓዙ በዚሁም 31 ሃገራትን ጎብኝተዋል። በ 2003 ሥልጣን ላይ ሲወጡ ብራዚል በአፍሪቃ የነበሯት 17 አምባሳደሮች ቁጥርም ዛሬ 37 ደርሷል»

እንግዲህ ብራዚል ዛሬ በዲፕሎማሲ ረገድ እንበል የጀርመን እኩያ ለመሆን በቅታለች ማለት ነው። ይህም እርግጥ ያላንዳች ስሌት የሆነ ነገር አይደለም። የላቲን አሜሪካዋ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ሃይል ብራዚልም እንደ ጀርመን ሁሉ በተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ የምትሻ ሲሆን ድርጅቱን ለመጠገን የሚያስፈልገውን የብዙሃን ድምጽ ለማረጋገጥ ከአፍሪቃ ጋር መልካም ግንኙነት ማራመዷ ጠቃሚ እንደሆነ ታውቃለች።ይሁን እንጂ የላቲን አሜሪካና የአፍሪቃ ግንኙነት ከፖለቲካ አንጻርም ቢሆን ቢቀር ለጊዜው ጥቂት ድካም ማሳየቱ አልቀረም። ለዚህም መንስዔው ኤኩዋቶሪያል ጊኒ ውስጥ ለትናንትና ለዛሬ ታስቦ የነበረው የሁለቱ ወገን የመሪዎች ጉባዔ ባልተገለጸ ምክንያት ላልታወቀ ጊዜ እንዲሸጋሸግ መደረጉ ነው።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ