1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋምቢያ ውዝግብ

ረቡዕ፣ ጥር 10 2009

የጋምቢያ ፕሬዚደንት ያህያ ጃሜህ ዘመነ ስልጣናቸው ዛሬ በይፋ ያበቃል። ሆኖም፣ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ዝግጁ አልሆኑም። በዚህ ፈንታ፣ በሀገሪቱ የአስቸኳዩን ጊዜ አውጀዋል። ጃሜህ እንደሚጠበቅባቸው ከስልጣን ካልወረዱ የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ፣ በምህፃሩ፣ «ኤኮዋስ» በአንፃራቸው ወታደራዊ ርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ተጠቁሟል።

https://p.dw.com/p/2VzrO
Gambia Yahya Jammeh Präsident
ምስል Reuters/C. G. Rawlins

Gambia Ausnahmezustand - MP3-Stereo


የጋምቢያ ፕሬዚደንት እጎአ ታሕሳስ አንድ 2016 ዓም በፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላሸነፉዋቸው እና ከነገ በስቲያ የፊታችን ሐሙስ የሀገሪቱን አመራር ለመያዝ ቃለ መሀላ ለሚፈፅሙት ሥዩሙ ፕሬዚደንት አዳማ ባሮው ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል።  ይሁንና፣ ከምርጫው በኋላ ሽንፈታቸውን ወዲያውኑ ተቀብለው የነበሩትና ከአንድ ሳምንት በኋላ ሀሳባቸውን የቀየሩት ጃሜህ  ስልጣናቸውን ለመልቀቅ አሻፈረኝ  እንዳሉ ይገኛሉ። ብዙዎቹ ሚንስትሮቻቸውም ስልጣናቸውን ለቀው፣ እንዲሁም፣  ሁከት እንዳይነሳ የሰጉ ቢያንስ 5,000 የሀገሪቱ ዜጎችም ወደ ጎረቤት ሴኔጋል ሸሽተዋል። ፕሬዚደንት ጃሜህ ምርጫው ትክክለኛ አልነበረም በሚል ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ማመልከቻ ያስገቡት ፕሬዚደንት ጃሜህም በስልጣን የመቆየት እቅዳቸውን ለማረጋገጥ ትናንት አስቸኳዩን ጊዜ አውጀዋል።
« እኔ የጋምቢያ ፕሬዚደንት እና የጦር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሰር ፕሮፌሰር ዶክተር ያህያ ጃሜህ ከዛሬ ጥር 17፣ 2017 ዓም ጀምሮ በመላይቱ ጋምቢያ አስቸኳዩን ጊዜ አውጃለሁ። »
ይህን ተከትሎ የጋምቢያ ምክር ቤት የፕሬዚደንቱን ዘመነ ስልጣን በሶስት ወር አራዝሟል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በጃሜህ እምቢተኝነት በጋምቢያ የተፈጠረውን ቀውስ ይበልጡን እንደሚያካርረው «በለንደን የሚገኘው የፖለቲካ ጥናት ተቋም፣ «ቻተም ሀውስ» ተንታኝ አሌክስ ቫይንስ አስታውቀዋል።
« ቀጣዮ ጊዜ በጋምቢያ ፖለቲካ  ሁከት እና አለመረጋጋት የሚታይበት ይመስለኛል። ውዝግቡን ለማብረድ ተጨማሪ ጥረት ይደረጋል። በጋምቢያ ጊዚያዊ ሁኔታ ሰበብም  የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ፣ በምህፃሩ፣ «ኤኮዋስ»ም በአሁኑ ጊዜ ወታደራዊ ርምጃ ለማካሄድ አለማሰቡን ጠቁሟል። » 
የጋምቢያን ውዝግብ ለማብቃት ጥረቱን የቀጠለው «ኤኮዋስ» ፕሬዚደንት ያህያ ጃሜህ ስልጣናቸውን የማይለቁ ከሆነ ፣ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከስልጣናቸው ሊያወርድ እንደሚችል የቡድኑ ጦር ኃይል ምንጮች ሲጠቁሙ  ተሰምተው ነበር።  ይሁንና፣ ወታደራዊ  ጣልቃ ገብነት የ«ኤኮዋስ» ሳይሆን የአዲሱ የጋምቢያ ፕሬዚደንት ውሳኔ እንደሚሆን ነው የናይጀሪያ ፕሬዚደንት መሀመዱ ቡሀሪ ቃል አቀባይ ጋርባ ሼሁ ለዶይቼ ቬለ የገለጹት።
« በጋምቢያ በነገው ዕለት ሰላማዊ የስልጣን ዝውውር ይደረጋል  ብለን ተስፋ እናደርጋለን።  ይህ ካልሆነ ናይጀሪያ በዚሁ ጉዳይ ላይ የመሪነቱን ኃላፊነት ትወስዳለች ብዬ አልጠብቅም።  በዚሁ ጉዳይ የሚወስኑት በነገው ዕለት ስልጣን የሚረከቡት አዳማ ባሮ ናቸው። ከጎረቤት ሃገራት ወታደራዊ ድጋፍ  እንደሚያስፈልጋቸው በግልጽ ከተናገሩ፣ ያኔ ጎረቤት ሃገራት ጉዳዩን ያስቡበታል። ስለዚህ ምን እንደሚወሰን በአሁኑ ጊዜ አይታወቅም። »
ሥዩሙ ፕሬዚደንት አዳማ ባሮ በወቅቱ በጎረቤት ሴኔጋል መዲና፣ ዳካር የሚገኙ ሲሆን፣ «ኤኮዋስ» ለጋምቢያ ውዝግብ በወታደራዊ ርምጃ መፍትሔ ለማስገኘት ከወሰነ  ሴኔጋል ወሳኝ ሚና ልትጫወት እንደምትችል አሌክስ ቫይንስ ገምተዋል።

Adama Barrow Präsident von Gambia
ምስል Getty Images/AFP
Karte Gambia mit Senegal und Casamance
ምስል DW

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ