1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እርጅናን በእርግጥ ማስቀረት ይቻላል?

ሐሙስ፣ ኅዳር 2 2003

በዚህ በጀርመን ሀገር፣ የኑዋሪዎቹ የህይወት ዘመን ወይም ዕድሜ ከጊዜ ወደ ጊዜ ክብረወሰን እየያዘ በመምጣት ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/Q5ZX
በዕድሜ ጠና ያሉ ሰዎች፣ ለጤንነትና ለሰውነት ማጠንከሪያ እንቅሥቃሴ ሲያደርጉ፣ምስል DW-TV

ከየሁለቱ ሰው አንዱ ቢያንስ 80 ሳይደፍን ከዚህ ዓለም በሞት አይለይም። ከየሁለት ሴቶች አንዷ 85 ትደፍናለች። አዝማሚያው፣ በኮሎኝ፣ የማክስ ፕላንክ ተቋም የሚሠሩ አንዳንድ የሥነ ህይወት ተመራማሪዎችን ጭምር ማስገረሙ አልቀረም። በመሠረቱ፣ የእነርሱ ምርምር ያተኮረው ፣ ሰዎች እንዴት ረዘም ላለ ጊዜ መኖር ይችላሉ በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ነው። ስለሰው ለመመራመር በቅድሚያ ትኩረት ያደረጉትም በትላትሎች ላይ ነው።

(ድምፅ)-------------

በኮሎኙ፤ የማክስ ፕላንክ የምርምር ተቋም በጥቃቅን ትላትሎች ላይ ነው። በማጉሊያ መነጽር ብቻ ሊታዩ በሚችሉ! እ ጎ አ በ 1980ኛዎቹ ዓመታት፣ ተመራማሪዎች፣ በአንድ የትል የዘር መለያ ኅዋስ ላይ ለውጥ በማድረግ ፣ ያ፣ በቤተ ሙከራ የኅዋስ ለውጥ የተደረገበት ትል ከተለመደው የህይወት ዘመኑ በላቀ ሁኔታ 10 እጥፍ ለመኖር መብቃቱን ያረጋገጡበት ሁኔታ ነበረ። ስለሆነም እርጅና ከዘር ኅዋስ ጋር የተገናኘ በመሆኑ፣ በዘር ኅዋሳት ንጥሮች ላይ ፣ ሰው- ሠራሽ ለውጥ በማስተዋወቅ የተለየ ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችል ያኔ ነበረ የተደረሰበት። የኢምንቱን ትል አጠቃላይ ኅዋሳት ከሚያጠኑት የማክስ ፕላንክ ተቋም ተመራማሪዎች መካከል፤ አስተባባሪው ራልፍ ፔትሪ፣ እንዲህ ብለዋል።

«ይኸው ትል አንዳንድ ምልክት ተደርጎባቸው የሚታወቁ ነገሮችን ለመግታት አስችሏል።

ማየት የምንችለው ነው። አስገራሚ ነገር!? ለምሳሌም ይህል የህመም ምልክቶችን በስዕል እናያለን። የመርሳት- የመሳት፤ የእርጅና ወይም የነቀርሳ? ይህ ተመልሶ የሚጋጥም ይሆን?»

በኢምንት ትል ፣ ፈራፍሬ በሚያድኑ በራሪ ነፍሳትና አይጦች ላይ ምርምራቸውን ያጠናከሩት ሳይንቲስቶች፤ ስለሰዎች የእርጅና ሂደት፤ እንዲሁም ከእርጅና ጋር ተያይዘው ስለሚመጡ ህመሞች ሰፊ ግንዛቤ ለማግኘት ነው ተስፋ የሚያደርጉት።

«በዚህ ጉዳይ ላይ የምንገነዘበው ዐቢይ ጉዳይ፤ የተጠቀሱት ህመሞች፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከእርጅና ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ነው። ለምን እንደምናረጅ፤ መሠረታዊ ግንዛቤ ሲኖረን ሂደቶች ምን እንደሚመስሉ ስናውቅ ፤ ከዚህ ጋር የተዛመዱትን በሽታዎች ለመታገል የሚያችለውን አብነት እናገኘዋለን። እናም፤ በአጠቃላይ የሚያረጁ ሰዎችን የአካላት ጤንነት ለማሻሻል ምናልባት አንድ መፍትኄ እናገኝ ይሆናል። »

ፔትሪ እንደሚሉት፣ በተፈጥሮ ፤ እንስሳት፣ ከእርጅና ጋር የተያያዙት ሁኔታዎች እስከዚህም አይሰማቸውም። በእኛ ሰዎች ግን የተለየ ነው። በህክምና ግሥጋሤ ሳቢያ በንጽህና አጠባበቅም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በእርጅና ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት ይቻላል።

« የህዝብን ቁጥር የጭማሪ ሂደት፣ በምንመረምርበት ጊዜ፣ ባለፉት 150 ዓመታት ፤ በየ 10ሩ ዓመት በግምት የሁለት ዓመት ከመንፈቅ የዕድሜ ጭማሪ መኖሩን መገንዘብ እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ፤ እንደሚታየው ከሆነ ይኸው ሂደት ፍጻሜ የሚኖረው አይመስልም።»

ዕድሜ ከመጨመርና ከእርጅና ጋር ተያይዞ፣ የሚከሠቱ በሽታዎችን፤ መርሳት-መሳት፣ ካንሠርና የመሳሰሉትን በተጠናከረ መልኩ መታገል ይኖርብናል ማለት ነው። ስለዚህ፤ በተለይ በኢንዱስትሪ በገሠገሡ አገሮች ፣ በእርጅና ላይ መመራመሩ ዐቢይ ትርጉም ተሰጥቶታል። በዚያም በህዝብ መጠን ላይ የጎላ ለውጥ ነው የሚታየው። የሚወለዱት በጣም ጥቂት ሲሆኑ አረጋውያኑ ግን ብዙዎች ናቸው። አዝማሚያው የሆነው ሆኖ ለ ራልፍ ፔትሪ ግልጽ ነው።

የማክስ ፕላንክ ተቋም ተመራማሪዎች እንዳሉት ምርምሩ ይቀጥላል። ግን የኢምንቱን ትል ያህል ሰው እሥር እጥፍ ዕድሜ ይኖረዋል? ማን ያውቃል? ምናልባት!—

እጅግ ረጅም ዕድሜ እንዲኖረው የሚሻ፣ አብረው የሚዘልቁትን ጣጣዎችም ልብ ሊላቸው ይገባል።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ