1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እሳተ ገሞራና መዘዙ፣

ረቡዕ፣ ግንቦት 17 2003

እሳተ ገሞራ፣ ከሚፈነዳበት ቦታ፤ መርዘኛ ጋዝ ፣ የጋለ ዓመድና ጠጠር በመበተን በአካባቢው በሚኖር ህዝብ ላይ ከባድ የህይወት አደጋም ሆነ የጤና እክል ያስከትላል፤ ከዚያም ባለፈ፣ የምድራችንን የአየር ጠባይ ሊለዋውጥ ይችላል። ለእንዴትነቱ--የዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ማብራሪያ አለው።

https://p.dw.com/p/RQ2j
በአይስላንድ የ ግሪምስቮኧትን እሳተ ገሞራ የፈጠረው የአመድ ደመና፣ምስል picture alliance/dpa

ባለፈው ዓመት በሚያዝያ፤ በደቡብ ምሥራቅ አይስላንድ፣ ቫትናዮኩል በተሰኘው በረዶ ከሸፈነው የብስ ፤ ከከርሠ-ምድር የፈነዳው፤ የኢያፍያላዮኩል እሳተ-ገሞራ፣ አውሮፓን አስጨንቆ፣ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ሁሉ እስከማስተጓጎል ደርሶ እንደነበረ የሚታወስ ነው። 20 ኪሎሜትር ወደ ሰማይ ሲትጎለጎል የሰነበተው ይኸው እሳተ ገሞራ፣ ቀን ቆጥሮ ፣ ዓመት ጠብቆ ፤ ይመስላል፤ ባለፈው ቅዳሜ ያገረሸው። ልክ እንዳምናው፣ የዘንድሮው ፍንዳታም፤ በበረራ ላይ ሥጋት ደቅኖ መሰንበቱ አይዘነጋም። በአይስላንድ የአየር ንብረት ምርምር ጽ/ቤት፤ የአፈርና ቋጥኝ ተመራማሪ ዚግትሩዱር አርማንስዶቲር ፤ በዛሬው ዕለት እንዳስታወቁት፤ ካለፈው ሌሊት አንስቶ፣ እሳተ-ገሞራው የሚተፋው የጋለ ዓመድና የሚትጎለጎል ጭስ ቆሟል። ፍንዳታው፣ አሁን ፣ ከእነአካቴው ቆሟል ብሎ በእርግጠኛነት ለመናገር ግን የሚያስችል አይደለም። ከእሳተ-ገሞራው የተተፋው የጋለ ዓመድና ደመና፣ ሰሜን ጀርመን በመድረሱ፣ ዛሬ፣ ጧት ከሃምበርግ -በርሊን የበረራ አገልግሎት እንዲቋረጥ ተደርጎ ነበር። በኋላ ግን እገዳው ተነስቷል። ቀደም ሲል የተደቀነው አደጋ፣ ሰፊውን አውሮፓ እንዳያካትት ሥጋት ከማሳደሩም ሌላ፣ አለ። የበረራ ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ፣ በጀርመን ሀገር ምናልባት 700 በረራዎች ሊሰረዙ እንደሚችሉ አስታውቀው ነበር። ሥጋቱ ፣ ከመጀመሪያውም፤ ፤ ዋንኞቹን የአየር በረራ ማዕከላት፣ ፍራንክፈርትንና ሙዩኒክን የሚመለከት አልነበረም። ትናንት ከፊል የአየር ግዛቷን በእሳተ ገሞራው ደመና ሳቢያ ለበረራ ዝግ እንዲሆን አድርጋ የነበረችው ደንማርክ፣ ዛሬ ሥጋት እንደሌለ ነው የገለጠች።

የእሳተ ገሞራ ዓመድ ለአይሮፕላን ሞተር በጣም አደገኛ መሆኑ ቢታወቅም፤ እጅግ አደገኛ የሚባለው መጠኑ ምን ያህል ሲሆን ነው? ለሚለው ጥያቄ፣ አውሮፓውያኑ እስካሁን ገና አልተስማሙም። በአየር ውስጥ ምን ያህል ዓመድ ሲገኝ ነው አደገኛ የሚሰኘው። በከባቢ አየር ፤ የዐመድን መጠን ብርሃን በሚያንጸባርቅ መሣሪያ መለካት እንደሚቻል፤ በዩሊኽ ጀርመን የምርምር ማዕከል ባለሙያዎች ይናገራሉ፤ ግን ይህ መረጃ ለመሰብሰብ ብቻ እንጂ ፤ አንድ የጋራ መመሪያ ለማውጣት ባለመዋሉ የጀርመን የአየር ፣ የበረራና የኅዋ ምርምር ባለሙያ ሃንስ ቮልከርት ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

ባለፈው ቅዳሜ ማታ ፣ በደቡብ ምሥራቅ አይስላንድ፣ ግሪምስቨኧትን በተሰኘው አካባቢ የፈነዳውና በዚያች ደሴት ማንኛውም አኤሮፕላን እንዳይበር ያስገደደው እሳተ ገሞራ፤ አውሮፓ ውስጥ ያልበረዱ ከሚሰኙት ወይም በማንውም ጊዜ ሊያገረሹ ከሚችሉት መካከል አንዱ ነው። ከ 7 ዓመት በፊትም ከዚያው ቦታ ላይ እሳተ ገሞራ ፈንድቶ እንደነበረ የሚታወስ ነው። ከመፈንዳቱ በፊት ግን፣ የከርሠ ምድሩ ሙቀት እጅግ እየጨመረ በመምጣቱ ፣ በረዶው እየቀለጠ እንደ ጅረት ሲፈስ መሰንበቱን የእሳተ ገሞራ ተመራማሪዎች ታዝበዋል። ከምድር ነውጥ ጋር ተያይዞ የፈነዳው እሳተ ገሞራ፤ 20 ኪሎሜትር ወደ ሰማይ እንፋሎትና የጋለ ዓመድ ከተፋ በኋላም ነበረ ጠበብቱ በዙሪያው የምርምር በረራ ያካሄዱት። በዚሁ የተማራማሪዎች ቡድን ውስጥም በሬይክያቪክ ዩኒቨርስቲ፣ የመልክዓ ምድር ፊዚክስ ባለሙያ ማግኑስ ቱሚ ጉድሙንድሰን ይገኙበታል።

«የጋለው የአመድ ደመና የተንቀሳቀሰው ወደ ምሥራቅ ነው። ይትጎለጎል ወደነበረው ጭስ መጠጋት እጅግ አደገኛ በመሆኑ ብርቱ ጥንቃቄ ነበረ ያደረግን። ባለፉት ዐሠርተ-ዓመታት ካጋጠሙት ፍንዳታዎች ሁሉ ከሰሞኑ የተከሠተው ነበረ እጅግ ኃይለኛ እንደነበረ ሊታወቅ የቻለው። ፍንዳታው፣ ቀስ በቀስ መብረዱ የታወቀ ቢሆንም ፣ የእሳተ ገሞራን ሂደት እንዲህ ነው ብሎ መላ ምት መደርደር የሚቻል አይደለም። »

ተመራማሪዎቹ ባደረጉት በረራ፤ ከፍተኛ ቦታ ላይ ፣ ሰማይ ላይ ማለት ነው፣ ለህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላኖች አደገኛ ሊሆን የሚችል የጋለ ዓመድና ጠጠር መከሠቱን ለመረዳት ችለዋል። ለዚህም ነው፤ እሳተ-ገሞራው ከፈነዳበት ቦታ፣ በ 200 ኪሎሜትር ዙሪያ በረራ እንዳይኖር የተከለከለው። በሬይክያቪክ የአየር በረራ ደኅንነት ተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ወ/ሮ ሂዮርዲስ ጉድሙንድስዶቲር----

«ዓለም አቀፍ በረራዎች፤ አይስላንድ ውስጥ፤ እሳተ-ገሞራ ከፈነዳበት ቦታ በስተደቡብ ፈንጠር ብለው ነው እንዲበሩ መመሪያ የተሰጠው። ምን የባሰ ሁኔታ ሊከተል ይችላል? ወደፊት የምንከታተለው ጉዳይ ነው የሚሆነው። በሚቀጥሉት ቀናት ሰፊ መረጃ ማግኘታችን የማይቀር ነው።»

አብዛኞቹ የአይስላንድ ተወላጆች ባለፈው ሰሞን በፈነዳው እሳተ ገሞራ እምብዛም የተጨነቁ አይመስሉም። እሳተ ገሞራ በሚፈነዳባቸው የአገሪቱ ደቡብ ምሥራቅ ወረዳዎች ህዝብ አይኖርም። ያም ሆነ ይህ ፣ ባለፈው ቅዳሜ፤ በእሳተ ገሞራ ከታወቀችው፤ በሰሜናዊ- ምዕራብ አውሮፓ፤ ፈንጠር ብላ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ከምትገኘው ደሴት ፤ አይስላንድ ፤ ግሪምስቮኧትን ላይ እንደገና ያገረሸው ፍንዳታ ፤ ያምናውን የአየር መንገድ ተጓዦች እንግልትና ኪሣራ የሚያስታውስ ነው የሆነው። አምና ኢያፍያላዮኩል እሳተ ገሞራ፣ በመሃልና ሰሜን አውሮፓ የአየር መሥመር እንዲዘጋ በማስገደድ፣ 10 ሚሊዮን ያህል መንገደኞች እንዲጉላሉ አድርጓል። ያኔ፤ በአኤሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ተኮልኩለው ቀጣዩን የበረራ ጊዜ በመጠባባቅ ቀናት ያሳለፉ መንገደኞች፤ ወይም የበረራ አቅጣጫ መለወጥ ግድ የሆነባቸው ጥቂቶች አልነበሩም። የበረራ አግልግሎት ድርጅቶችም በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የገንዘብ ኪሣራ የደረሰባቸው መሆኑ አልታበለም። እሳተ ገሞራ የሚተፋውና ከፍ ብሎ ወደሰማይ የሚትጎለጎል የጋለ ዓመድና ጭስ እሁን እንደተባለው በበረራ ረገድ፣ እክል በመፍጠር ፣ ጉዞ በማስተጓጎልና ኪሣራ በማድረስ ብቻ የሚወሰን አይደለም። የእሳተ ገሞራ ጭስና ዓመድ፤መለስተኛ ከሆነ በአንድ አካባቢ በዛ ላሉ ወራት የአየሩን ጠባይ ሊያወናክር ይችላል። ኃይለኛ ከሆነም ፣ በዓለም የአየር ንብረት ላይ ለዓመታት የተዛባ ሁኔታ ማስከተሉ እንደማይቀር ነው ጠበብት የሚናገሩት። ወደ ከባቢ አየር ከፍ ብሎ የሚውጣጣው የእሳተ ገሞራ ዓመድማ ደመና፤ የፀሐይን ብርሃንና ሙቀት ይከልላል። የነፋስን አቅጣጫ ይለውጣል። ምዝን የአየር እርጥበት እንዲሁም ወደላይ የሚተን ጋዝ ሁሉም ሲቀዝቀዝ ዝናም ሆኖ ይወርዳል። አንዳንዴ፤ የጠራ ዝናም ሳይሆን ድፍርስ፤ ወይም ጭቃ መሰል ዝናም ይሆናል የሚዘንበው ። የእሳተ ገሞራ የዓመድ ደመና፤ በሺ ኪሎሜትሮች ርቀት ሊንሠራፋ ይችላል።

በአየር ንብረት ረገድ ለውጥ የሚያስከትለው፤ ከእሳተ-ገሞራ ወደ ሰማይ የሚያፈትልከው የድኝ መጠን ነው። ከከባቢ አየር ጋር የሚቀላቀለውም፤ የድኝና ሃድሮጂን ቅልቅል (H2S) እንዲሁም የተቃጠለ የድኝ ጋዝ (SO2) ሆኖ ነው። በከባቢ አየር፤ የድኝና ሃይድሮጂን ቅልቅል ወዲያው ነው ወደተቃጠለ የድኝ ጋዝ የሚለወጠው። ከዚያም፣ ከውሃ ጋር ወደ ዝናም ተለውጦ ሲወርድ የድኝ አሲድ ጠብታዎች (H2SO4)ከፊሉ የፀሐይ ብርሃን ተንጻባርቆ ወደ ኅዋ እንዲመለስ ያደርጋል። ይህም የዓለም አማካይ የአየር ሙቀት እንዲቀነስ ሰበብ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል እ ጎ አ በ 1991 ዓ ም፤ የፈነዳው ከፊሊፒኑ የፒናቱቦ ተራራ የፈነዳው እሳተ-ገሞራ፣ የዓለምን የአየር ሙቀት መጠን በአማካዩ በግማሽ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ያህል ዝቅ እንዲል አስገድዶ እንደነበረ ይነገራል። እ ጎ አ በ 1982 የፈነዳው የሜክሲኮው El Chichon የሙቀቱን መጠን በግምት በግማሽ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነበረ የቀነሰው። በአይስላንድ እ ጎ አ በ 1783 ዓ ም ላኪ በረባለው ቦታ የፈነዳው እሳተ ገሞራም፣ ተመሳሳይ ሁኔታ አስከትሎ እንደነበረ ነው የሚነገረው። በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ፣ ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት 1816 ፤በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ነክ ታሪክ፣ «በጋ ያልታየበት ዘመን» በመባል ይጠቀሳል። ያኔ፤ ከሚያዝያ አንስቶ እስከመስከረም፣ ዝናም ፣ በረዶ ፣ ጠጣር በረዶና ጠጠር ፤ ነበረ ከሰማይ ይወርድ የነበረው። ሰብል ከጥቅም ውጭ ሆኖ፤ ረሃብ ገብቶ፤ ወረርሽኝ በሽታ ተዛምቶ፤ በመቶ ሺ የሚቆጠር ህዝብ ህይወት አጥፍቷል። ለዚህ ምክንያት የሆነው ፤ ከዚያ አንድ ዓመት ቀደም ሲል፤ በኢንዶኔሺያ የፈነዳ እጅግ ኃይለኛ እሳተ-ገሞራ ነበረ ። የኢንዶኔሺያው «ታምቦሮ» እሳተ-ገሞራ ፤ 100 ኪዩቢክ ኪሎሜትር አቧራ ዓመድና ጠጠር ፣ ወደ ከባቢ አየር በመትፋት ነበረ፣ የአየሩን ጊዜያዊ፤ ወቅታዊና ዓመታዊ ጠባይ የለዋወጠው።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ

አርያም ተክሌ