1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውሳኔው ከደመወዛቸው ተቀማጭ እንዲያደርጉ ያስገድዳል

ማክሰኞ፣ ጥር 2 2009

የእስራኤል ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በእስራኤል ያሉ ተገን ጠያቂዎችን አስመልክቶ የወጣ ህግ ላይ የቀረበን ማሻሻያ አጽድቋል፡፡ ማሻሻያው ተገን ጠያቂዎች ከሚያገኙት ደመወዝ ውስጥ 20 በመቶውን ብቻ ተቀማጭ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነው፡፡ ማሻሻያው ተገን ጠያቂዎች ያለፍላጎታቸው ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንደሚለሱ ለማድረግ ነው በሚል ተተችቷል፡፡

https://p.dw.com/p/2VXDH
Flüchtlingslager Holot für afrikanische Asylsuchende in Israel
ምስል picture-alliance/dpa/O. Weiken

Israeli govt Decision affect African immigrants - MP3-Stereo

የእስራኤል መንግስት  ከአፍሪካ በተሰደዱ ተገን ጠያቂዎች ላይ አድልዎ ያደርጋል በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳዎች ደርሰውበታል፡፡ ተገን ጠያቂዎችን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት በምክር ቤት ያሳለፈው የደመወዝ አከፋፈል ውሳኔም የመድሎው አንድ ማሳያ አንደሆነ እየተተቸ ይገኛል፡፡

ውሳኔው አፍሪካውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ለስራቸው ከሚቀበሉት ክፍያ ውስጥ 20 በመቶውን ተቀማጭ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ተቀማጭ የሆነው ገንዘብ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ተሰብስቦ እንደሚሰጣቸው በውሳኔው ተቀምጧል፡፡ አንድ ተገን ጠያቂ እመለሳለሁ ባለበት ጊዜ ወደ ሀገሩ ካልሄደ ገንዘቡ በመንግስት ይወረሳል፡፡

እስራኤል በስደተኞች ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ በሚከታተሉ ወገኖች ዘንድ ይህ ውሳኔ አልተወደደም፡፡ የሀገሪቱ ዕለታዊ ጋዜጣ የሆነው ሀሬትዝ በዕለተ ሰንበት ዕትሙ “የእስራኤል ስርቆት ከተገን ጠያቂዎች” በሚል ርዕስ ስር ውሳኔውን የሚተች ርዕሰ አንቀጽ አስነብቧል፡፡ “ውሳኔው ዝቅተኛ ክፍያ የሚከፈላቸውን ተገን ጥያቄዎች ህይወት የበለጠ አስቸጋሪ የሚያደርግ ነው” ሲል ጽፏል፡፡ ጋዜጣው ይህ የሚደረገው የተገን ጠያቂዎችን መንፈስ ለመስበርና ተማርረው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እንደሆነ ወንጅሏል፡፡    

በእየሩሳሌም ባለ የኢትዮጵያ ይሁዳውያን የመብት ተሟጋች ተቋም ውስጥ የሚሰሩት አቶ መብራቱ መሸሻ ጉዳዩን ከሁለት አቅጣጫ መመልከት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

“መጀመሪያ እነሱን እንደ ህጻን አድርገው ነው የሚያዩዋቸው፡፡ ማንኛውም ሰው ደምወዝ ሲቀበል የሚጠቅምበትን ተጠቅሞ፣ የሚያስቀምጠው ካለ አስቀምጦ እንደማንኛውም ትልቅ ሰው በራሱ ደምወዝ መጠቀም ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ እንደ ህጻን አድርገው የሚያዩዋቸው፡፡ ይህ በኤርትራውያን ወይም በሱዳናውያን [ዓይን] ስታየው ነው” ይላሉ፡፡   

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በእስራኤል ውስጥ በይፋ የሚታወቁ 46 ሺህ ገደማ አፍሪካውያን ተገን ጠያቂዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ኤርትራውያን አሊያም ሱዳናውያን ናቸው፡፡ ተገን ጠያቂዎቹ ከቴል አቪቭ ከተማ ሁለት ሰዓት ያህል በመኪና በሚያስኬደው ሆሎት በተሰኘ በርሃ ውስጥ ባለ ማቆያ ቦታ ኑሯቸውን እንዲገፉ ይገደዳሉ፡፡ ወደ ከተሞች ለስራ የሚወጡ ተገን ጠያቂዎች ከአሰሪዎቻቸው የሚያገኙት ከተለመደው አነስተኛ ክፍያ እንደሆነ ይነገራል፡፡

Israel Flüchtlinge in Holot Haftanstalt
ምስል Getty Images/AFP/M. Kahana

እንደ አቶ መብራቱ አባባል ከሆነ በእስራኤል ህግ መሰረት አሰሪዎች ለሰራተኞቻቸው ከሚከፍሏቸው ውስጥ የተወሰነውን አስልተው የማስቀመጥ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሰራተኞቹ ጡረታ ሲወጡ ወይም አደጋ አጋጥሟቸው ከስራ ከተገለሉ በአሰሪዎቻቸው በኩል የተጠራቀመውን ገንዘብ ይጠቀማሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት የተላለፈው ውሳኔ ከእስራኤል መንግስት አንጻር ሲታይ ከዚህ ጋር የሚያያዝ ጭምር እንደሆነ አቶ መብራቱ ያስረዳሉ፡፡

“ይሄ ውሳኔ እንደሚመስለኝ አንደኛ ለእነሱ ተገን ላለመስጠት ይመስለኛል እንዲዚህ ያደረጉት ፡፡ ሶስቱን ለመያዝ ማለት ነው፡፡ ዜግነት እንዲኖራቸው አልፈለጉም ወይም ጥገኝነት እንዲጠይቁ አልፈለጉም፡፡ እንደማንኛውም ሰው ሰርተው በደመወዛቸው እንዲጠቀሙም አልፈለጉም፡፡ አሰሪዎችም እነርሱን እንደማንኛውም ዜጋ የተወሰነ አስቀምጠው ጉዳት በሚደርሰባቸው ወይም በሚያረጁ ጊዜ እንዲሰጧቸው አላደረጉም፡፡ ሁሉንም አላደረጉም” ሲሉ የእስራኤል መንግስትን አካሄድ ይተነትናሉ፡፡

በተገን ጠያቂዎቹ ላይ እየተደረገ ያለውም ሆነ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ይሁዳውያን ላይ የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከዘረኝነት አመለካከት ጋር የሚያያዙ እንደሆኑ አቶ መብራቱ ይከሳሉ፡፡ ከአውሮፓ በተለይም ከምስራቅ አውሮፓ ተሰደው በእስራኤል እየሰሩ የሚገኙት ከአፍሪካውያኑ ሶስት እጥፍ ቢሆኑም እነርሱን የሚመለከት ምን ነገር እንዳልተደረገ አንስተው ይከራከራሉ፡፡

“ያሉት አፍሪካውያን በጣም ቢበዙ 50 ሺህ የሚሆኑ ናቸው፡፡ ግን ህጋዊ ያልሆኑ ፈረንጅ መጤዎች ከ100 ሺህ የበለጡ ናቸው፡፡ ስለ እነርሱ ህግ አይወጣም፤ ስለእነርሱ አይወራም፡፡ እንደውም ሀገራቸው ሄደው ተመልሰው መምጣት ይችላሉ፡፡ የሚወራው ስለአፍሪካውያን ብቻ ነው፡፡ ለምንድነው ብለህ ስትጠይቅ ዘረኝነት ካልሆነ ሌላ ምክንያት ልትሰጠው አትችልም” ይላሉ አቶ መብራቱ፡፡

እስራኤል በበረሃ ላዘጋጀቸው ማቆያ ጣቢያዋ እስከ 250 ሚሊዮን ዶላር እንዳወጣች ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ ሀገሪቱ ካስጠለለቻቸው ተገን ጠያቂዎች መካከል 20 ሺህ ያህሉን ወደየሀገራቸው እንዲመሰሉ ማድረጓን ማስታወቋ አይዘነጋም፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ