1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«እስታርባክስ«፧ የገባውን ቃል እንዲያከብር መጠየቁ፧

ሐሙስ፣ መጋቢት 13 1999

ዋና ጽህፈት ቤቱ፧ ሲያትል ዩ. ኤስ. አሜሪካ የሚገኘው፧ በምሥራቅ አፍሪቃ በተለይም በኢትዮጵያ ቡና፧ በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ የከበረው ኩባንያ፧ የኢትዮጵያን የቡና ምርቶች፧ በ«ሲዳሞ«፧ «ሐረር«ና «ይርጋጨፌ« ስም፧ የንግድ ምልክቱን ተቀብሎ እንዲሠራና፧ በዚህ ረገድ የሚገኘውን ትርፍ ገቢ ለኢትዮጵያ ቡና አምራች ገበሬዎች እንዲያካፍል የቀረበለትን ጥያቄ፧ እንደሚቀበለው ቃል ይግባ እንጂ፧ እስካሁን ተግባራዊ አላደረገውም።

https://p.dw.com/p/E0d3
የእስታርባክስ ባለሥልጣናት፧ዳብ ሔይና አለን ፓንሰሌት፧ ሐሙስ፧ የካቲት 8,1999 ዓ ም፧ በአ.አ. በተካሄደው ጉባዔ፧
የእስታርባክስ ባለሥልጣናት፧ዳብ ሔይና አለን ፓንሰሌት፧ ሐሙስ፧ የካቲት 8,1999 ዓ ም፧ በአ.አ. በተካሄደው ጉባዔ፧ምስል AP Photo
እስታርባክስ፧ ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ፧ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በሰጠው የጋራ መግለጫ፧ ኩባንያው፧ ኢትዮጵያ፧ የንግድ ምልክት ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ከእንግዲህ እንቅፋት አይሆንም ብሎ ነበር። ከኢትዮጵያውያን ሌላ፧ Oxfam የተሰኘው የብሪታንያው የግብረ ሠናይ ድርጅትም የኢትዮጵያ ቡና አምራቾች የሚገባቸውን የገቢ ድርሻ እንዲያገኙ የበኩሉን ትግል በማካሄድ ላይ ነው።
ተክሌ የኋላ..........
Starbacks ስሙ፧ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የማይረሳ ሆኗል፧ በተለይ በኢትዮጵያውያን ቡና አምራቾች ዘንድ! ይህ አሜሪካዊ ኩባንያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቡና ንግድ እጅግ የከበረ በዓለም ዙሪያ ከ 13,000 በላይ የቡና መደብሮችና ቡና መጠጫ ቦታዎች ያሉት ሲሆን፧ ወደ 40,000 ከፍ ለማድረግም እቅድ አለው። ገሚሱ፧ ከአሜሪካ ውጭ በተለያዩ አገሮች የሚከፈት ይሆናል።
ኩባንያው፧ አሠራሩ፧ እጅግ ዘመናዊ መሆኑም ይነገርለታል። ለተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ የቆመ ከአዳጊ አገሮችና ከእርዳታ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ የሚሠራ ነው ይባላል። ለፍትኀዊ የንግድ ልውውጥ የቆመ እንደሆነም ይነገርለታል። የብሪታንያው የግብረ-ሠናይ ድርጅት «ኦክስፋም« ግን፧ ወጥሮ በመያዝ፧ «ቃል በተግባር ይፈተን!« ማለቱን እንደቀጠለ ነው። ይኸው ድርጅት ትናንት፧ Seattle Times በተሰኘው ጋዜጣ፧ ኩባንያው በቡና ችርቻሮ ከሚያገኘው ገቢ፧ ለኢትዮጵያ ቡና አምራቾች ላቅ ያለ ድርሻ ይእሰጥ ዘንድ አሳስቧል።
እስታርባክስ፧ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ዙሪያ ታዋቂነት እንዲያገኝ ከኢትዮጵያውያን ጋር እኩል ራእይ እንዳለው ከመግለጹም ከምሥራቅ አፍሪቃ በተለይም ከኢትዮጵያ የሚገዛውን የቡና ምርት መጠን በእጥፍ ከፍ እንደሚያድርግ ቃል ገብቷል።
ኩባንያው ከኢትዮጵያ የሚገዝን ቡና በችርቻሮ ንግድ፧ ግማሽ ኪሎግራም ገደማ የሚሆነውን ኻያ ስድስት ዶላር ድረስ እንዲያወጣ በማድረግ ይቸበችበዋል። አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ቡና አምራቾች ግን በቀን ቢበዛ በአንድ ዶላር ገቢ ነው የሚንከላወሱት። የኩባንያው ባለቤት Howard Schultz በዓለም ውስጥ፧ እጅግ የጠነተኑ ሀብታሞች ከሚባሉት ቱጃሮች አንዱ ሲሆኑ፧ ትናንት ለተጠየቁት አስተያየት፧ ምላሽ ከመሥጠት ተቆጥበዋል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ግን፧ ለአንድ መጽሔት በሰጡት ቃል፧ «እስታርባክስ፧ ከማንኛውም በላይ ላቅ ያለ ግምት በመስጠት፧ ህዝብን መሠረት ያደረገ የንግድ ድርጅት ነው« ማለታቸው ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያን መንግሥት ጥቅም አስከብራለሁ ብለው የቆሙት በዋሽንግተን የሚገኙት የህግ ጠበቃ Robert Winter በበኩላቸው እንዲህ ነበር ያሉት።
«እናንተም እንደ እኛ፧ ኢትዮጵያ በንብረቷ የንግድ ምልክት፧ ይበልጥ የመቆጣጠር መብት ሊኖራት ይገባልብላችሁ ታምናላችሁ ይህም ሲሆን፧ ኢትዮጵያ በኤኮኖሚ አመቺ ሁኔታ ይፈጠርላታል። እነሱ ግን ይህን ለመግታት ነው የሚፈልጉት። የእስታርባክስ ኀለፊ፧ ሃዎርድ ሹልትዝ፧ በዓለም ውስጥ እጅግ ምርጥ የሆነ ቡና የሚገኘው በኩባንያቸው መሆኑን አንድ ሲዜ ሲናገሩ፧ እንዲህ ብለው ነበር።
«ጀርመናዊ፧ ጃፓናዊ፧ አሜሪካዊ ሆንክ ፊሊፒናዊ ትርጉም የለውም። ሁላችንም፧ በኑሮአችን፧ የጋራ እሴቶች ያስፈልጉናል። ይህም ፍላጎት ከሰዎች ጋር መገናኘትና መተሣሠር ነው።«
የብሪታንያው የግብረ-ሠናይ ድርጅት ኦክስፋም፧ በእስታር ባክስ በጎ-ፈቃድ መጓደል፧ የኢትዮጵያ ቡና አምራች ገበሬዎች፧ በዓመት 88.5 ሚልዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ይቀርባቸዋል ሲል፧ ኩባንያውን መውቀስ-መክሰሱን፧ እንደቀጠለ ነው።