1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እነማን ይፈታሉ፤ ማዕከላዊስ መች ይዘጋል?

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 27 2010

በእስር ላይ የሚገኙ የተለያዩ ፖለቲከኞች እንደሚፈቱ ቅም ስቅል እንደሚፈጸምበት የሚነገርለት ማእከላዊ ምርመራም እንደሚዘጋ ቢገለጥም እነማን እንደሚፈቱ ማእከላዊም መቼ እንደሚዘጋ ግን በቁርጥ የተነገረ ቀን የለም። የብዙዎች መነጋገሪያነቱ ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/2qMuF
Symbolbild Guantanamo
ምስል picture-alliance/dpa/M. Shephard

ማእከላዊ፦ ቁም ስቅል እንደሚፈጸምበት በርካቶች ይናገራሉ

በስተመጨረሻ ምን አይነት መግለጫ ይወጣ ይኾን በሚል በርካቶች በጉጉት ሲጠብቁ ነው የከረሙት። ከኹለት ሣምንት በላይ በዝግ ሲካሄድ ከነበረው የኢሕአዴግ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ምሥጢራዊነት የተነሳ መላ ምቶች በየአቅጣጫው ሲሰነዘሩም ነበር። ድንገት ግን ብዙዎች ያልጠበቁት ነገር ረቡእ ዕለት ተሰማ። የጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት ኹለት ነገሮችን ይፋ አደረገ። «በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች» እንደሚፈቱ ገለጠ። ቁም ስቅል መፈጸሚያነቱን በርካቶች የሚናገሩለት ማእከላዊም እንደሚዘጋ በመግለጫው ተነግሯል። ከእስር የሚፈቱት እስረኞች ግን እነማን ናቸው? የማዕከላዊስ መዘጋት በኢትዮጵያ የቁም ስቅል ማክተሚያ ይኾን? በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ያነሱት ጥያቄ ነው። አስተያየት ጥያቄውን አካተናል። 

ሰሞኑን ተስተጓጉሎ የከረመው የኢንተርኔት አገልግሎት ረቡዕ እለት በአዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ ድንገት ነጻ መለቀቁ ብዙዎችን ሳያስደምም አልቀረም። በርካቶችን እጅግ ያስደነቀው ግን ድንገት ሳይጠበቅ የጠቅላይ ሚንሥትሩ ጽ/ቤት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ይፋ ያደረገው መግለጫ ነበር። እየተቀነጫጨበም ቢኾን ይፋ የኾነው መግለጫ የተሰጠው በኢሕአዴግ አራቱ አባል ድርጅቶች አመራር መኾኑ ተገልጿል። መግለጫው የተሰጠውም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ነው። በቀጥታ ሥርጭት ባይኾንም በተለያየ መንገድ ሲያስተላልፍ የነበረው ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው ነበር። ጣቢያው በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮቹ ያቀረባቸውን ቁንጽል የመግለጫውን ይዘቶች ለሰባት እና ስምንት ጊዜያት የቃላት እና ሐረጋት ለውጥ ማድረጉ ብዙዎችን አስደምሟል። የጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤትም መልእክቱ ላይ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ለውጥ አድርጎበታል።  ብዙዎች ትንታኔ የሰጡበት መልእክት ኹለት አበይት ነጥቦች ላይ ያተኩራል። 

እስረኞችን በተመለተ የቀረበው መልእክት እንዲህ ይነበባል። «በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ በአቃቤ ሕግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምሕረት ሕግና ሕገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል:: ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማርያም ደሳለኝ።»

Äthiopien kündigt Freilassung politischer Gefangenen an | Hailemariam DesalegnDesalegn
ምስል picture alliance/AA/E. Hamid

ቁም ስቅል እንደሚፈጸምበት ብዙዎች የሚናገሩለት ማዕከላዊ እንደሚዘጋ የተገለጠው «ሰበር ዜና» በሚል ነበር። በመንግሥት ማኅበራዊ መገናኛ ዘርፍ ገጾች የቀረበው መልእክት እንዲህ ይነበባል፦ «በደርግ ዘመን በምርመራ ስም ልዩ የጭካኔ ተግባር ሲፈጸምበት የነበረውና በተለምዶ ማእከላዊ በመባል የሚታወቀው የምርመራ ማእከል እንዲዘጋ ተደርጎ ሙዝየም እንዲሆን ተወስኗል።» ይኽም በጠቅላይ ሚንሥትሩ መነገሩ ተጠቁሟል። 

«በደርግ ዘመን በምርመራ ስም ልዩ የጭካኔ ተግባር ሲፈጸምበት የነበረው» የሚለውን ሐረግ በርካታ ሰዎች ተቃውመውታል። ማሂር ማሂር በሚል የፌስቡክ ገጽ የቀረበው ጽሑፍ «ማእከላዊ ደርግ ሲያሠቃይበት የሚሉት እነዚህ ማፈሪያዎች እነሡ ሙዚየም ነበር ያደረጉት ወይሥ ካፌና ሬስቶራንት» ነው ሲል ይነበባል። 

ሻም ዓሊ ደግሞ፦ «አፈና የበዛው አሁን በህውሃት ዘመን ነው መዓከላውይ በነሱ ግዜ ነው የማሰቃያ ጉሬ የሆነው» ሲል አስተያየት ሰጥቷል ፌስቡክ ላይ። አብይ ለገሠ ደግሞ፦ «መአከላዊ ጠቧቸው ሌላ ትልቅ መአከላዊ እንደገነቡ ተናግረዋል ስለዚህ መአከላዊ ተዘጋ ብላችሁ አትጨፍሩ» ብሏል። 

ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ በተመሳሳይ ስለማእከላዊ የቀረበውን ሐረግ አስመልክቶ በትዊተር ገጹ ላይ በእንግሊዝኛ፦«ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ‚በደርግ ዘመን በምርመራ ስም ልዩ የጭካኔ ተግባር ሲፈጸምበት የነበረው‘‏ ብለዋል። ያ ያበሳጫል።  እኔ በእሳቸው የአገዛዝ ዘመን በዚያ የሰቆቃ ቤት የተሰቃየ በሕይወት የሚገኝ ሰለባ ነኝ። በዚያን ወቅት እነዚያን መርማሪዎች በሚቀጥለው ቀን ከማየት ሕይወቴን ለማጥፋት እመኝም ነበር። እነዚህ ሰዎች ይቅርታን አስቸጋሪ አድርገውታል» በማለት ሐሳቡን ገልጿል። 
«አንዱን የሰቆቃ ክፍል ዘግቶ ሌላውን መክፈቱ ፋይዳው ምንድን ነው?» ሲል የጠየቀው ደግሞ ብርሃነ ታየ ነው። 

ጦማሪ አቤል ዋበላ ማእከላዊን በተመለከተ ጸደይ በተባለ ስም የቀረበ የትዊተር ጽሑፍን አያይዞ ቀጣዩን መልእክት በእንግሊዝኛ  አስተላልፏል። «እባካችሁ እመቤቲቱን ስንት ዓመቴ እንደኾነ ጠይቁልኝ።  የእኛ ትውልድ (እኔና ጓደኞቼን ጨምሮ) በማእከላዊ ሰቆቃ የደረሰብን በሰባዎቹ የኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ ወቅት በመሳተፋችን የተነሳ ነው» ሲል ተሳልቋል። የጸደይ የትዊተር መልእክት ቁልፍ የፖለቲካ እስረኞች ሊፈቱ ብሎም ማእከላዊ ሊዘጋ ነው መባሉ በመልካም ዜና ይነሳል በሚል ይንደረደራል።  «ማእከላዊን በተመለከተ» ትላለች ጸደይ «ማእከላዊ ላይ  የተላለፈው ተምሳሌታዊ ውሳኔ ብቻ ነው።  መንግሥት ከደርግ ጋር ግንኙነት ካለው እስር ቤት ተያይዞ መነሳቱን ስላልፈለገ ነው እስር ቤቱ በቀላሉ ወደ ሌላ ቦታ ይዛወራል» ብላለች።

እሸቱ ሆማ ቄኖ «የማዕከላዊ ገራፊዎች ወደ የትኛው ሕንፃ ተዘዋወሩ????» ሲል በፌስቡክ ጠይቋል ጠይቋል። ሚኪያስ  ለጥያቄው መልስ ሲሰጥ የአጥናፍ ብርሃኔ የትዊተር መልእክትን አያይዟል። የአጥናፍ ትዊተር ቀጣዩን የእንግሊዝኛ መልእክት ይዟል።  «በነገራችን ላይ ከካዛንቺስ ወደ ባንቢስ ሱፐር ማርኬት በሚወስደው መንገድ የሚገኘው የቀድሞው ዮርዳኖስ ሆቴል አዲሱ ማእከላዊ ነው» ብሏል። ረቡእ ዕለት በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች የወጣው የጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት መግለጫ የምርመራ ተቋሙ መቀየሩ እና ሥራ መጀመሩን ገልጧል። መግለጫው እንዲህ ይላል፦ «በዓለም አቀፍ ስታንዳርድና የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባፀደቀው የሰብአዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብር መሰረት አዲስ የምርመራ ተቋም ተቋቁሞ በሌላ ህንፃ ስራ ጀምሯል።»   

Burundi, Symbolbild Folter
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Delay

ኤደን፦ «ገራፊዎቹ ለፍርድ ይቀርባሉ ወይስ የሙዚየሙ አስጉብኚ ይሆናሉ?» ስትል ለጠየቀችው ተስፋዬ መሠረት እዛው ትዊተር ላይ በቀልድ መልክ ቀጣዩን መልስ ሰጥቷል።  «ወደ አዲሱ እስር ቤት ከደሞዝ ጭማሪ ጋር እድገት ያገኛሉ!»

በነገራችን ላይ ሰሞኑን የተስተጓጎለው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም አገልግሎት ረቡዕ ዕለት መግለጫው ሲሰጥ ሙሉ ለሙሉ ይሠራ እንደነበር ተጠቅሷል። እያስፔድ ተስፋዬ፦ «‏ኢንተርኔቱም ተፈቷል!!!» ብሏል ረቡእ ዕለት በአጭሩ። ብሥራት ተሾመ በበኩሉ በእንግሊዝኛ ቀጣዩን ሐሙስ እለት ጽፏል፦«የትናንቱ የኢሕአዴግ መግለጫ ተከትሎ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ኢንስታግራም፣ ቴሌግራም ....  እና  ሌሎች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አሁን ያለአንዳች ዙር አዙር አዲስ አበባ ውስጥ ይሠራሉ።» 

እንዳልክ ደግሞ ትዊተር ላይ፦ «የሕወሓት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ሠራዊት በግልጽ እንደሚታየው ኢሕአዴግ የፖለቲካ እስረኞችን ለመልቀቅ ቃል መግባቱ አላስደሰታቸውም።  በግድም ቢኾን ዋጡት» ብሏል። 

የፖለቲካ እስረኞችን በተመለከተ የወጣው መግለጫ በተደጋጋሚ ለውጥ ተደርጎበታል። በርካቶች በተደጋጋሚ የተቀየሩትን የመግለጫው ይዘቶች ፎቶ በማንሳት ከመልእክታቸው ጋር አያይዘዋል። ሃይከል፦ «የምንሰማው አማርኛ የተለያየ ካልሆነ በቀር ጠዋት ወሬ ሻጮች በፈረንጅኛ ያከፋፈሉን ወሬና ሃይለማርያምም ሆነ ሌሎቹ አመራሮች ኢቢሲ ላይ ሲሉ የተሰማው የተለያየ ነው» ብሏል።  

የጠቅላይ ሚንሥትሩ ጽ/ቤት የዕረቡ እለት ሰበር ዜና ለ8 ጊዜ ያኽል ቃላቱ እያቀያየረ ተጽፏል ወይንም አርትኦት ተደርጎበታል። ይክም ብዙዎችን ጥርጣሬ ውስጥ ከትቷል። በፖለቲካ እስረኞች ስም ስም ያላቸውን የተወሰኑ እስረኞች ፈትተው ሌሎቹን ሊረሱ ነው ሲሉም ስጋታቸውን ገልጠዋል። 

ይኽንኑ ርእሰ ጉዳይ በተመለከተ ከኢሕአዴግ አመራር አንዱ የኾኑት አቶ ለማ መገርሳ ያደረጉት የቪዲዮ ንግግር ተቀንጭቦ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተሰራጭቷል። በተለይ ደግሞ «የማንም ሥልጣን ገደል ይግባ ከሀገር በላይ አይደለም» የሚለውን ሐረግ በርካቶች ነቅሰው ተቀባብለውታል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ