1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንቆቅልሽ፣ የአነጋገር ዘይቤና ፍቺ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 5 2002

እንቆቅልሽ የምንጫወተዉ አካባቢን ለመመርመር ለማጥናት በነገሮች መካከል ያለዉን ተመሳሳይነት እና ልዩነት የምንፈትሽበት ባህላዊ የማስተማርያ ዘዴ ነዉ፣ ይሉናል ምሁራን።

https://p.dw.com/p/L1UK
ምስል UNO

እንቆቅልሽ ተጫዋቾች ከአራቱ የቋንቋ ክህሎቶች መካከል፣ የመናገር እና የማዳመጥን ችሎታቸዉን በርግጥ ያዳብራሉ። እንቆቅልሾቻችን በተለይ ነባር የሆነዉን ባህላችንን የመግለጽ ሁኔታም ይታይባቸዋል። ይህ ማለት ግን ሰዎች በአካባቢያቸዉ ያለዉን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዉጤቶችን በእንቆቅልሽ መልክ አይጠቀሙባቸዉም ማለት አይደለም። እንቆቅልሽ በአገራችን በተለይ ለህጻናቱ እዉቀትን ለመገብየት የቋንቋ ችሎታን ለማዳበር ማህበራዊ ግንኘትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል። ለምሳሌ እንቆቅልሽ የሚጫወቱ ሰዎች እንቆቅልሽ ሲጠይቁ ህግና ስርአትን አክብረዉ ነዉ። እንደ የህብረተሰቡ እምነትም ጨዋታዉ የተለያየ ስርአት እና ደንብ አለዉ። በአገራችን በተረት ዉስጥ በሃሳብ ስንዝሮ ብለን የምናዉቀዉ አይነት ምስል ጀርመናዉያንም በባህላቸዉ ዛንድ ማን በሚል መጠርያ በጣም አጭር እና ረዘም ያለ ሪዝ ያንጠለጠለ ምስል እንዳላቸዉ በተለይ በህጻናት ዘንድ ታዋቂ እንደሆነ እና ባለፉት ሶስት ሳምንት ግድም ሃምሳኛ አመቱ እንደተከበረለት ባለፈዉ ሳምንት ዝግጅታችን አዉስተን ነበር። ይህንኑ በማስታከክ በአገራችን በተለይ ስላለዉ ዘይቤያዊ አነጋገር ተረት እና እንቆቅልሽ ከምሁራን ጋር ያደረግነዉ ዉይይት ዛሪም ይቀጥላል። እንቆቅልሽ የምንጫወተዉ አካባቢን ለመመርመር አካባቢን ለማጥናት በነገሮች መካከል ያለዉን ተመሳሳይነት እና ልዩነት የምንፈትሽበት ባህዊ የማስጠማርያ ዘዴ መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በቋንቋ ጥናት ተቋም መምህር የሆኑት አቶ መስፍን መሰለ አንድ እንቆቅልሽ ልጠይቅሽ ሲሉ ቃለ ምልልሳቸዉን ይጀምራሉ። «ላዩ በድን ታቹ በድን መሃሉ ነፍስ አድን የሆነ ነገር ምንድ ነዉ? ብለን ስንጠይቅ ላዩ በድን የሆነ ነገር ታቹ በድን የሆነ ነገር ምንድን ነዉ ብለን እንመረምራለን» እዚህ ላይ ታድያ ይላሉ መምህር መስፍን «የነገሮችን ልዩነት ተመሳሳይነት እንፈትሻለን እናወጣለን እናወርዳለን፣ ታድያ ስናስብ የማስታወስ ችሎታችን ይዳብራል የቋንቋ ችሎታ ይዳብራል እናም ታቹ በድን ላዩ በድን ነፍስ የሚያድነዉ መሃል ያለዉ ነገር ምንድ ነዉ ብለን ስንጠይቅ ታቹ በድን ምጣድ ነዉ ላዩ በድን አክንባሎ ሲሆን ነፍስ የሚያድነዉ ደግሞ እንጀራ ሆኖ እናገኘዋለን» ሲሉ ያስረዳሉ። እኔም ልጠይቅ በተራዩ!
እንቆቅልህ ምን አዉቅልህ - ዙርያዉ ዘንዶ ማህሉ ብርንዶ ምንድ ነዉ? እወቁልኝ! ዙርዉ ዘንዶ ማለት እንደ ዘንዶ ተጠቅልሎ የተኛዉ፣ የምድጃ ከተር ሲሆን፣ መሃሉ ብርንዶ፣ እንደ ብርንዶ ስጋ የቀላዉ ደግሞ ፍም ነዉ። አብዛኞቹ እንቆቅልሾቻችን እና ወጎቻችን በግጥም መልክ የሚቀርቡ ሲሆን ዘዩ ጠቀስም ናቸዉ። ታድያ ፍቻቸዉን ለማወቅ ባህሉን የህብረተሰቡን አኗር ጠንቅቀን ማወቅ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ይላሉ መምህር መስፍን መሰለ በመቀጠል
«ጉድ መጣ ጉድ መጣ ከምድር ዉስጥ ልቃቂት ወጣ!»
ተብሎ ሲጠየቅ ጉድ መጣ ጉድ መጣ ከምድር ዉስጥ ልቃቂት ወጣ የሚለዉ ግጥም መሰል ወይም ዜማ የመፍጠር ሁኔታ ይታይበታል። እናም እወቅልኝ ሲል ይጠይቃል፣ በዜማ፣ ከምድር የሚወጣ በቅርጽም በቀለምም ልቃቂት የሚመስል ነገር ምንድን ነዉ፣ ብለን ስንመረምር፣ በባህላችን በአካባቢያችን የምናዉቀዉ ነገር ነጭ ሽንኩርት ሆኖ እናገኘዋለን» መምህር መስፍን በመቀጠል እንቆቅልሽ አሉ ምን አዉቅልህ አልኻቸዉ
«ወድቆ የማይሰበር ሞቶ የማይቀበር አባቴ የሰጠኝ ወንበር ምንድን ነዉ እወቂልኝ!» ወድቆ የማይሰበር ሞቶ የማይቀበር ነገር ስም ነዉ በዘይቤም አነጋገር በአገራችን ስም ከመቃብር በላይ ይዉላል የሚባል ነገር አለ» ሲሉ በመቀጠል ያስረዳሉ።
እንቆቅልሽ በአገራችን በተለይ ለህጻናቱ እዉቀትን ለመገብየት የቋንቋ ችሎታን ለማዳበር ማህበራዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ያገለግላል። ለምሳሌ እንቆቅልሽ የሚጫወቱ ሰዎች እንቆቅልሽ ሲጠይቁ ህግና ስርአትን አክብረዉ ነዉ። እንደ የህብረተሰቡ የተለያየ ስርአት አለዉ። በእንቆቅልሽ ጨዋታ ግዜ መጠነኛ የሆነ ስድብም አለ። ስድቡ ተጠያቂዉ መልስ ባለማወቁ ምክንያት ተሸናፊ ነዉ። ጠያቂዉ ደግሞ ተጠያቂዉ የማይመልሰዉን ጥያቄ በማቅረቡ አሸናፊ ነዉ። አሸናፊዉ የበላይነቱን ለማሳየትም አገር ስጠኝ ይላል። ተሸናፊዉ አገር ይሰጠዋል፣ አልበቃኝም አነሰኝ ካለ ይጨምርለታል፣ አይ ይህም አልበቃኝም፣ የጸሃይ መዉጫን፣ ምስራቅ ስጠኝ ብሎ ሊያዝም ይችላል። ለምሳሌ ተሸናፊዉ ጎንደርን ከሰጠ አሸናፊዉ እሺ ጎንደርን እወስዳለሁ ካለ እንዲህ በማለት የስድም ናዳዉን ማዉረድ ይጀምራል። «ጎንደር ላይ ተቀምጬ፣
ሁሉ በጄ ሁሉ በደጄ፣
እኔ በሰጋር በቅሎ ተቀምጬ፣
አንተ አሽከሪን በገጣባ አህያ አስቀምጬ፣
አይነት አይነቱን ለነፍሴ፣
ግርድፍ ግርድፉን ለፈረሴ፣
በኔ ጉሮሮ ጠጅ ይንቆርቆር፣ በአንተ ጉሮሮ አጥንት ይሰንቀር» እያለ የመርገም እና የስድም ናዳ ይደረድራል። ስድቡ ካልበቃዉም ይቀጥላል፣ እንደ ሰፊድ ይለምጥህ፣ እንደ ደጋን ያጉብጥህ፣ በመጨረሻ ይህን ሁሉ የስድብ ናዳ ተሸናፊዉ ላይ ካወረደበት በኻላ፣ በል ጨርሴ እንዳልሰድብህ ሲመሽ አሳዳሪዪ፣ ሲቸግር አበዳሪዩ፤ በማለት የማለዘብያ ነገር ያመጣለታል።
ታድያ እንዲህ አይነቱ የስድብም ሆነ የርግማን ሁኔታ ሲኖር፣ በባህሉ ጨዋታ ክቡር ነዉ፣ የሚለዉን ነገር ይገልጻል። ተጫዋቾች ቢሰደቡም፣ ቢረገምም በጨዋታዉ ሂደት ተቀብሎ ዝም ነዉ እንጂ፣ ምንም ነገር አይልም። ባይሆን ተሸናፊዉ ከቻለ ሌላ እንቆቅልሽ አምጥቶ አሸናፊ ሆኖ አገር ስጠኝ የሚልበትን፣ እርግማን ሊያወርድ የሚችልበትን ሁኔታ ሲፈልግ ይታያል። በዚህም ታድያ የእንቆቅልሽ ተጫዋቾች ከአራቱ የቋንቋ ክህሎቶች መካከል የመናገር እና የማዳመጥን ችሎታ በርግጥ ያዳብራሉ።
እንቆቅልሾቻችን ነባር የሆነዉን ባህላችንን የመግለጽ ሁኔታ ይታይባቸዋል። ይህ ማለት ግን ሰዎች በአካባቢያቸዉ ያለዉን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዉጤቶችን በእንቆቅልሽ መልክ አይጠቀሙባቸዉም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ከዘመናዊዉ እንቆቅልሽ «እግር የላትም ትራመዳለች፣ አፍ የላትም ትናገራለች» እወቅልኝ! ይህንን ጠይቄ የዛሪዉን መረሃ ግብሪን ልደምድም። እግር የላትም ትሄዳለች፣ አፍ የላትም ትናገራለች፣ ሰአት ናት!

FAO Welternährungstag in Äthiopien
ምስል UN Photo/Rick Bajornas

አዜብ ታደሰ