1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እግር ኳስና አምባ ገነንነት

ረቡዕ፣ ጥር 27 2007

የስፖርቱ ድግስ ግን አልተጓደለም።በየስታዲዮሙ ይዘምራል፤ይዘፍናል፤ ይጨፈራል፤ይደነሳል።-ተመልካች።ተጫዋቹም፤ የኮትዲቫሩ ያያ ቶሬ እንደሚለዉ ለየብሔራዊ ክብሩ ይፋለማል-በኳስ ሥለ ኳስ።

https://p.dw.com/p/1EVeH
ምስል AFP/Getty Images/K. Desouki

ኢኳቶሪያል ጊኒ ዉስጥ ለተያዘዉ የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ፤ ለ ግማሽ ፍፃሜ ዉድድር፤ ዛሬ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ከኮትዲቯር፤ ነገ ደግሞ አስተናጋጅዋ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከጋና ይጋጠማሉ።የኢኳቶሪያል ጊኒ ቡድን ለዚሕ ደረጃ መድረሱ ብዙ ከማከራከር፤ ማወዛገብም አልፎ በሩብ ፍፃሜዉ ጨዋታ ከቱኒዚያ ጋር ያደረገዉን ግጥሚያ የመሩትን ዳኛ ለቅጣት ዳርጓል።የትንሺቱ አፍሪቃዊት ሐገር የእግር ኳስ ቡድን ለዚሕ ደረጃ መድረሱ ብቻ ሳሆን፤ ፍሎሪያ ባወር እንደዘገበችዉ በአምባገነናዊ ሥርዓት የምትገዛዉ ሐገር ታላቁን የአፍሪቃ የስፖርት ዉድድር ማስተናገድዋ ራሱ እንዳጠያየቀ ነዉ።የበዋርን ዘገባ ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የኢኳቶሪያል ጊኒ ና የቱኒዚያ ቡድናት ባለፈዉ ቅዳሜ ያደረጉት ግጥሚያ ዉጤቱ አስደናቂ-2 ለ-1፤ መዘዙ ኖዉክቾትን፤ከካይሮ፤ ቱኒዝን ከባታ ያነካካ-ግራ ነዉ።ርዕሠ-መንበሩን ካይሮ ያደረገዉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (CAF) የሁለቱን ቡድናት ግጥሚያ የዳኙትን ሞሪታኒያዊዉ ራጂንድራፓርሳድ ሴቹምን ስድስት ወር ኳስ ግጥሚያ ባለበት ዝር እንዳይሉ ቀጥቷል።የቱኒዚያ ቡድን ሐምሳ ሺሕ ዶላር፤ የኢኳቶሪያል ጊኒ ባላጋራዉ ደግሞ አምስት ሺሕ ዶላር ተቀጥተዋል።

የእርምጃዉ ምክንያት ዳኛዉ ለኢኮቶሪያል ጊኒ ቡድን የማይገባ ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል የሚል ነዉ።እንደ ቅጣት ምቱ ሁሉ ቡድኑ ለአጠቃላይ ዉድድሩ የቀረበዉ፤ ሐገሪቱም ታላቁን ግጥሚያ ያስተናገደችዉ በጋጣሚ ነዉ።ለአስተናጋጅነት ተመርጣ የነበረችዉ ሞሮኮ የኢቦላን ሥርጭት ፍራቻ ግጥሚያዉን አላስተንጋድም አለች።ኢኮቶሪያል ጊኒ አለሁ።

እርግጥነዉ ትንሺቱ አፍሪቃዊት ሐገር በተለይ በመኪና መንገዶች ጥራት አትታማም።ከትንሺቱ ሐገር ትልቅ ከተማ ባታ አንድ ጫፍ ወደ ሌለኛዉ ምቾት ሳይጓደል ባጭር ጊዜ መድረስ አይገድም።በፈጣኑ ምቹ መንገድ ግራ ቀኝ የተኮለኮሉት ጎጆዎች ካዩ ግን የትንሺቱን ሐገር ተቃራኒ አዉነታ ለማወቅ ተንታኝ አያሻዎትም።ወጣቱ የእግር ኳስ አሰልጣኝ ዩአን ፓብሎም ይናገራል።

Afrika Cup 2015 Elfenbeinküste vs. Algerien
ምስል REUTERS/Amr Abdallah Dalsh

«ኢኳቶሪያል ጊኒ ዉስጥ ሁለት ዓለም ነዉ ያለዉ።የድሆችና የሐብታሞች።ሐብታሞቹ የዕብነ-በረድ ቤት መገንባት ይችላሉ።ድሆች ግን ጎጇቸዉ (እንኳን) በቅጡ አልተሠራም።»

ሐገሪቱን ለ33ኛ ዓመታት የሚገዙት ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ ከሚዝቁት ገንዘብ ያሻቸዉን ያክል ወስደዉ የተረፋቸዉን ለመሰረተ ልማት ይቸሩታል።ኦብያንግ የዘመኑ አምባገነኖች እንደሚያደርጉት ሁሉ ገንዘቡን፤ ኤኮኖሚስቶች «ነጭ ዝሆን» ለሚሉት መንገድ፤ ሕንፃና ብጤዎቻቸዉ ማዋላቸዉ ጫቋኝ ሥርዓታቸዉን ከሩቅ በሚታዩ የመሠረተ-ልማት አዉታሮች ለመሸፈን የዘየዱት ነዉ።

የአፍሪቃ እግር ኳስ የዋንጫ ዉድድርን ሞሮኮ እንደማስተናግድ ሥታስታዉቅ የዉድድሩ ጊዜ የቀረዉ ሁለት ወር ነበር።ሥም፤ክብርና ዝና፤የሚሹት ኦብያንግ በዚያ አጭር ጊዜ ሁሉንም ለማድረግ ፈቀዱ።የሐገሪቱ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አንድሪያስ ዮርገ ምቦሚዮ እንደሚሉት ወጪዉ በርግጥ ቀላል አይደለም።ግን---ኦብያንግ አሉ-አሉም።

Teodoro Obiang Nguema
ምስል S. De Sakutin/AFP/Getty Images

«የአፍሪቃ ዋንጫን በሁለት ወር ጊዜ ማስተናገድ በጣም ዉድ ነዉ።ግን የሚወስነዉ መንግሥት ነዉ እኛ አይደለንም።»ያሁኑን ግጥሚያ ካስተናገዱት አራት ስታዲዮሞች ሁለቱ ለ2012 (እጎአ) ግጥሚያ የተዘጋጁ ነበሩ።የተቀሩትን በሁለት ወር ጊዜ ለማድረስ ግን ብዙዎች እንደሚገምቱት በሁለት አሐዝ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር መፍሰሱ አያጠያይቅም።

የስፖርቱ ድግስ ግን አልተጓደለም።በየስታዲዮሙ ይዘምራል፤ይዘፍናል፤ ይጨፈራል፤ይደነሳል።-ተመልካች።ተጫዋቹም፤ የኮትዲቫሩ ያያ ቶሬ እንደሚለዉ ለየብሔራዊ ክብሩ ይፋለማል-በኳስ ሥለ ኳስ።

«እንደኔ ዉጪ ሐገር ለሚጫወት ወደ አፍሪቃ ተምልሶ መጫዎት ለታላቅ ብሔራዊ ክብር ነዉ።አፍሪቃ ዉስጥ ብዙ ችግር አለ እንዲሕ አይነቱ ግጥሚያ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ነዉ።የዋንጫዉ ግጥሚያ ለአፍሪቃ ታላቅ ፌስታ ነዉ።»

CUF Demonstration in Dar es Salaam
ምስል DW/H. Bihoga

እድልም፤ጥንካሬም፤እልሕም ባንድ አብረዉለት የቶሬ ቡድን ለግማሽ ፍፃሜ ደርሰዋል።ኮትዲቯር።ካሜሩን፤አልጄሪያ እና ቱኒዚያን የመሳሰሉት ለዋንጫ የሚጠበቁ ቡድናት እየተንከባለሉ ወደየሐገራቸዉ ሲሸኙ ያልተጠበቁት ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፕብሊክ ከጠንካሮቹ ጋና እና ኮትዲቯርን እኩል ለግማሽ ፍፃሜ ተሠልፈዋል።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ