1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱርክ ምሁራን እጣ

ዓርብ፣ የካቲት 24 2009

ከቱርኩ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ከመቶ ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራ ተባረዋል ወይም ታግደዋል ። ከመካከላቸው በርካታ የዩኒቨርስቲ መምህራን እና ፕሮፌሰሮች ይገኙበታል። በስህተት ለዚህ ተዳርገናል የሚሉት አብዛኛዎቹ ምሁራን ንጽህናቸውን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ ።

https://p.dw.com/p/2YYLu
Türkei Prozess über Akademiker in İstanbul
ምስል DW/K. Akyol

Türkei Akadamiker - MP3-Stereo

ይሁን እና  ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤቶችም ሆነ ወደ አውሮጳ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ለመውሰድ መንገዱ ተዘግቶባቸዋል ።ባለፈው አመት ሐምሌ አጋማሽ ላይ ከተካሄደው የቱርክ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ የቱርክ ዩኒቨርስቲዎች 4811 ፕሮፌሰሮችን እና መምህራንን ከስራ አባረዋል ። ከመካከላቸው እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው ወደ ሥራ ገበታቸው የተመለሱት ። ከዚህ በተጨማሪ 2800 የዩኒቨርስቲው መምህራን የሥራ ውሎች አልታደሱም ወይም እንዲቋረጡ ተደርጓል ። ከየዩኒቨርስቲዎች አስተዳደርም ከ1100 በላይ ሠራተኞች ተባረዋል ። ምክንያቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ደግፋችኋል የሚል ነው ። በቱርክ ትልቅ ቦታ የነበራቸው የህገ መንግሥት ጉዳይ ጠበቃ እና በኢስታንቡሉ የማራማራ ዩኒቨርስቲ አስተማሪ የነበሩት ፕሮፌሰር ኢብራሂም ካቦጉሉ ሥራቸውን ካጡት ምሁራን  አንዱ ናቸው ። 

«ከቱርክ ህዝብ 99 በመቶው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ተቃውሟል ። እኛም እንዲሁ ባለን ኃይል ተቃውመናል ።ይሁንና የሐምሌ 15 ቱን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተቃወሙ እየተገፉ ነው ።»  ከተባረሩት ምሁራን መካከል 300ው በጎርጎሮሳዊው 2016 በቱርክ መንግሥት እና በኩርዶች መካከል ሰላም እንዲወርድ ጥሪ አስተላልፈው ነበር ።ይህ አሁን በመንግሥት አይን የሽብር ፕሮፖጋንዳ ነው ። የህግ መምህር ሜህሜት ሴሚል ኦዛንሱ በዚህ ጉዳይ ውስጥ የሉበትም ። ሆኖም ከስራ ተሰናብተዋል ።ፓስፖርታቸውንም ተቀምተዋል ። በምን ምክንያት ይህ እርምጃ እንደተወሰደባቸው በግል ሳይነገራቸው በይፋ በተሰጠ መግለጫ ነው የሰሙት።  
« ምሁራኑ የተባረሩበት ምክንያት በመንግሥት መግለጫዎች እንደተዘረዘረው የአሸባሪ ድርጅቶች አባልነት ፣ እና ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ያለ ግንኙነት እና ቅርበት ነው ።»

Türkei Entlassung Akademiker Ceren Akcabay
ምስል DW/D. Ekin

ኦዛንሱ  እርምጃ የሚወሰደው በዘፈቀደ መሆኑን ነው የሚናገሩት እንደ ፕሮፌሰር ካቦጉሉ ሁሉ ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ ይፈልጋሉ ። ይሁን እና ህጋዊ መንገድ ተዘግቷል ። ቤቱታቸውን የሚያየው የሚያየው ለዚሁ ጉዳይ ብቻ የተቋቋመ ልዩ ኮሚሽን ብቻ መሆኑን ከኢስታንቡሉ የጠበቆች ምክር ቤት ሴቭራል ባሊካያ ይናገራሉ ። 

Türkei Istanbul Beyazit Universität
ምስል picture-alliance/dpa/r. Hackenberg

«አምስት አባላት ያሉት ኮሚሽን ነው በመላ ሀገሪቱ ከፕሮፌሰሮች መባረር አንስቶ እስከ ማህበራት መዘጋት ድረስ የሚነሱ ተቃውሞዎችን የሚያየው ። ህገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ጉዳዩን የሚመለከትበት እድል የለም ። በዚህ የተነሳም ጉዳዩን ወደ አውሮጳ ህብረት የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት መውሰድ የሚቻልበትም መንገድ ተዘግቷል ።»

በሀገር ውስጥ ያሉትን አማራጮች ሁሉ ከተጠቀሙ በኋላ ነው ጉዳዩን ከሀገር ውጭ ወዳለ ፍርድ ቤት መውሰድ የሚቻለው ።  ለዚህ ወሳኙ ይ,ይግባኝ ሰሚው ኮሚሽኑ ፍጥነት ነው ይላሉ ጠበቃ ባሊካያ 
« ኮሚሽኑ ሥራውን አሁን በአፋጣኝ የሚጀመር ከሆነ ባለጉዳዩ አቤቱታውን ለማቅረብ ምናልባት 10 ዓመት ሊወስድበት ይችላል ።ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ ይህም ከሆነ ነው ወደ አውሮጳ ፍርድ ቤት መሄድ  የሚቻለው ።»
በሺህዎች ለሚቆጠሩ አቤቱታዎች 5 ዳኞች ብቻ መሰየማቸው እያነጋገረ ነው ። በከሚሽኑን ሃላፊነቶች እና አሠራር ላይ ያተኮሩ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ ። ከመካከላቸው ኮሚሽኑ ለአቤቱታዎቹ ውሳኔ የሚሰጠው በምን መስፈርቶች ነው ? እያንዳንዱ ጉዳይስ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል ? የኮሚሽኑ አባላትስ ለተሰጣቸው ሃላፊነት ብቁ ናቸው የሚሉት ይገኙበታል።

 

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ