1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስራ ማቆም አድማ እስከ የጀዋር የፌስቡክ እገዳ

ዓርብ፣ የካቲት 30 2010

ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች በሳምንቱ ውስጥ ትኩረት የሰጧቸው ጉዳዮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ እና አለመረጋጋት ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ በርካታ ተከታዮች ያሉት የኦ.ኤም.ኤን ቴሌቭዥን ጣቢያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀዋር መሐመድ ከፌስ ቡክ ገጻቸው በተደጋጋሚ መታገዳቸውን መግለጻቸው አነጋግሯል፡፡

https://p.dw.com/p/2u46k
Symbolbild Facebook Ausfall 27.01.2015
ምስል Reuters/D. Ruvic

ከስራ ማቆም አድማ እስከ የጀዋር የፌስቡክ እገዳ

በፍጥነት የሚለዋወጠው የወቅቱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ፤ አነጋጋሪ የነበሩ ጉዳዮች እንኳ ትኩረት የመሳቢያ ጊዜያቸው ከጥቂት ቀናት እንዳያልፍ አድርጓል፡፡ በማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ ይህ ሁኔታ ይበልጡኑ ጎልቶ ይስተዋላል፡፡ ሳምንት ይሻገር የነበሩ እና በርካቶች ይቀባበሏቸው የነበሩ አጀንዳዎች በዕለታዊ ክንውኖች እና ሁነቶች ተተክተዋል፡፡ አብዛኞቹ በኢትዮጵያ ካለው የፖለቲካ የፖለቲካ ቀውስ ጋር የተዛመዱ ናቸው፡፡  

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተወካዮች ምክር ቤት በአከራካሪ ሁኔታ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ መቀስቀሱ የቅዳሜ እና እሁድ መነጋገሪያ ነበር፡፡ አዋጁን በመቃወም ከሰኞ እስከ ረቡዕ በኦሮሚያ የተጠራው የስራ ማቆም አድማ ሌላው ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ አልፏል፡፡ በክልሉ ካለው ተቃውሞ እና አድማ ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች እየታሰሩ ስላሉ ሰዎችም በርካቶች ጽፈዋል፡፡ 

ከኦሮሞ አራማጆች (አክቲቪስቶች) መካከል አንዱ የሆነው ገረሱ ቱፋ አድማው መሳካቱን እና አዋጁ እስኪነሳ ተመሳሳይ አድማዎች መቀጠል እንዳለባቸው ረቡዕ ዕለት በፌስ ቡክ ገጹ አስፍሯል፡፡ “ህገ ወጡን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመቃወም የተደረገው ሁሉን አቀፍ ቤት ውስጥ የመቀመጥ ተቃውሞ በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ ካለፈው አርብ ጀምሮ በተሳካ ሁኔታ ተካሄዷል። የስርዓቱን የማፈን ምኞት እንዳጨለመበት ምንም ጥርጥር የለውም። ልክ በኦሮሚያ ውስጥ በተደረገው ልክ ሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ቢደረግ ኖሮ ደግሞ ጨቋኙን ሃይል በበለጠ ሊያሽመደምድ እንደሚችል ምንም ጥያቄ የለውም። ይህ የገዳዮች አዋጅ እስኪነሳ ድርስ ህዝቡ ትንፋሽ እየወሰደ መቀጠል ይኖርበታል” ብሏል። 

Äthiopien Proteste | Ambo Town
ምስል DW/M. Yonas Bula

ጋልጋሉ አባ ዋቆ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ግን “ትልቁ ችግር ያለዉ ፊንፊኔ ሆነ ሳለ ትልቁ ጉልበት እየባከነ ያለዉ ሩቅ የኦሮሚያ ወረዳ ላይ” ነው ሲሉ በአድማው ዋዜማ በገጻቸው ባወጡት ጽሁፍ ተከራክረዋል፡፡ “የኦሮሚያ መንገድ በመዘጋቱ አዲስ አበባ ዉስጥ ጭንቀት ይፈጠራል። ነገር ግን ይህ ጭንቀት ወደ ትግል ሊቀየር የሚችለዉ በሶስት ቀን አድማ አይደለም። ለአንድ ሳምንት የሚዘልቅ አድማ እንኳን ቢጠራ መንገዶቹ ሙሉ በሙሉ እስካልተዘጉ ድረስ አዲስ አበባ ላይ ያለዉ ተፅዕኖ የሸቀጥ የዋጋ ንረት ብቻ ነው። ከአንድ ሳምንት በላይ የሚቆይ አድማ ለመሸከም ህዝቡ አቅም ያለዉ አይመስለኝም። አሁን አድማ በተጠራ ቁጥር የሚሆነዉ ወይንም እየሆነ ያለዉ የታጋይህን አቅም ወይም ጉልበት መቀነስ ብቻ ነው። አሁን ኦሮሚያ ዉስጥ ያለው አስተዳደር በአብዛኛው ከህዝቡ ጋር የተሰለፈ ነው፤ ግማሹ በፍርሃት ግማሹ አምኖበት። ወደ ለዉጥ ጎዳና በፍጥነት እንድንገባ ከተፈለገ አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ትዕዛዝ የሚሰጡት እና የሀገሪቷን ችግር እየፈጠሩ ያሉትን ማስደንገጥ ነው። ይህ ሳይሆን ሌላ ቦታ ላይ ትኩረት እና ጉልበት መጨረስ በየትኛዉም መመዘኛ ተገቢ አይመስለኝም” ሲሉ ጽፈዋል።

አቡ ኢምራን የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ አድማው ተጽዕኖ አስከትሏል ባይ ናቸው። “የሶስት ቀን የስራ ወይም የንግድ ማቆም አድማ ምን ያህል የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ እንደሚያሽመደምድ ለማወቅ freshman economics ኮርስ ማስታወስ በቂ ነው” ሲሉ በዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመት የሚሰጠውን የኢኮኖሚክስ ትምህርት አንስተዋል። ከአድማው መጠናቀቅ በኋላ በፌስ ቡክ ገጹ ሀሳቡን ያካፈለው ሲራክ ተመስገን በበኩሉ “የሰሞኑ አድማ የጠቀመው ጌቶችን ብቻ ነው” ብሏል፡፡ ምክንያቱንም አንድ ሁለት ሲል ዘርዝሯል፡፡ “አንደኛ ከዚህ ቀደሙ [አንጻር] ተፅዕኖ መፍጠር ያልቻለ እና ዜጎችን ወደ ፍርሃት የመለሰ ነበረ። ሁለተኛ ብዙ ዜጎች ሞተዋል፣ታስረዋል። ሶስተኛ የኦህዴድ መዋቅር ተሰነጣጥቋል። የአንዳንድ ኦሮሚያ ከንቲባዎች እና ምክትል ከንቲባዎች ታስረዋል። የኦሮሚያ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጭምር ታስረዋል። አራተኛ የጃዋር [መሐመድ] ፌስቡክ ገጽ ከአንድ ቀን በላይ በፌስቡክ ተዘግቶበታል። የመረጃ ፍሰቱ በጣም ቀንሶ ነበረ” ሲል ምክንያቶቹን ደርድሯል፡፡ 

ሲራክ የጠቀሰው የኦ.ኤም.ኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና ዳይሬክተር የአቶ ጀዋር መሐመድ የፌስ ቡክ ገጽ መታገድ ነገር በርካታ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡ አቶ ጀዋር በዚህ ሳምንት የተከናወነውን እና ከዚህ ቀደም የነበሩ አድማዎችን ጨምሮ በኦሮሚያ ያሉ ተቃውሞዎችን የሚየሳዩ መረጃዎችን፣ ፎቶዎችን እና ቪዲዎችን በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው በተከታታይ በማውጣት ይታወቃሉና ነው ገጻቸውን እንዳይጠቀሙ በፌስቡክ ታግደዋል መባሉ መነጋገሪያ የሆነው፡፡

የፌስ ቡክ የማረጋገጫ ምልክት የተሰጠው እና ከአንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉትን ገጻቸውን ለመጠቀም እንደተቸገሩ በትዊተር ገጻቸው ሲያሳውቁ የቆዮት አቶ ጀዋር እንደ አማራጭ በሚል በወዳጆቻቸው የተከፈተ ሌላ ገጽን መጠቀም ጀምረዋል፡፡ አዲሱ የፌስ ቡክ ገጽ በጥቂት ቀናት ብቻ 98 ሺህ ተከታይ አፍርቷል፡፡ አቶ ጃዋር ስለ ገጻቸው መዘጋት ሂደት እና ከፌስ ቡክ ጋር ስለነበራቸው ውይይት ትላንት ምሽት ለዶይቼ  ቬለ ተከታዩን ብለው ነበር፡፡ 

Facebook Datenschutz Internet Symbolbild
ምስል dapd

“የዛሬ ሁለት ሳምንት አካባቢ የመጀመሪያው የስራ ማቆም አድማ እየተካሄደ ባለበት ወቅት በፍጥነት እየለጠፍክ ስለሆነ አላግባብ ተጠቅመህበታል፣ ለጊዜው አግደህናል አሉኝ፡፡ ከዚያ ጻፍኩላቸው፡፡ በመገናኛ ብዙሃን ዘገባው ከወጣ በኋላ ደውለውልኝ በስህተት ነው ያገድንህ፣ ስፓም መስሎን ነበር ይቅርታ ብለው ኤሜይል ጻፉልኝ፡ ደውለውም ወደ 30 ደቂቃ የሚሆን ጊዜ በስፋት ተወያየን እና ከእንግዲህ በኋላ እንዲህ አይነት ችግር አይገጥምም ተባልኩ፡፡ ከዚያ አንድ ሳምንት ገደማ ቆይተን እንደገና አንዳንድ የማወጣቸውን ፎቶዎች ማንሳት ጀመሩ፡፡ ከዚያ ምንድነው እየሆነ ያለው ስል አሁንም ይቅርታ ጠይቀው መልሰው ለቀቁት፡፡ አሁን ይሄኛው ዘመቻ ሲጀመር ደግሞ አሁንም በድጋሚ ብሎክ አደረጉኝ፡፡ ብሎክ ሲያደርጉኝ ጻፍኩላቸው፡፡ የምጻጻፋት ሰው አይታው፣ አላወቅችም ነበርና ተመልሶ ተለቀቀ፡፡ 

እየሆነ ያለው የቴክኒካል ችግር ነው እነርሱ እያሉ እያሉት፡፡ ግን ያ ነው ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ፍጥነት ነው እንዳይባል በጣም ፍጥነት ቀንሼ ነበር፡፡እንደውም የመጨረሻው ላይ ብሎክ ስደረግ 10 ጽሁፎች ብቻ ነበር ፖስት ያደረግኩት፡፡ እረፍት ወስጄ፣ ከሰዎች ጋር ስልክ እያወራሁ ቆይቼ ነው ተመልሼ ፖስት ላደርግ ስል ነው ብሎክ ያደረጉኝ፡፡ እና ከዚህ ረገድ ስታየው የቴክኒካል ጉዳይም አይመስለኝም፡፡ የእኔ ጥርጣሬ ምናልባት በድርጅቱ ውስጥ ያለ ግለሰብ ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ በድርጅት ደረጃ አሊያም በመንግስታት ጫና ያደረጉት ሊሆን ይችላል ብዬ ነው የምገምተው” ሲሉ አብራርተዋል።

ከሰኞ እስከ ሐሙስ ባሉት ቀናት አራት ጊዜ የፌስ ቡክ ገጻቸው እንደተዘጋባቸው የሚናገሩት አቶ ጀዋር ይህም የሚሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ተጠቃሚ በሚበዛበት ጊዜ እንደሆነ ይገልጻሉ። ገጻቸው መልሶ ሲለቀቅላቸው የነበረው ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሊት ሲሆን እንደሆነ ያስረዳሉ። እንዲህ አይነት አካሄድ ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም አሳሳቢ ነው ባይ ናቸው። 

“ለእኔ የሚያሳስበኝ የእኔ ፌስ ቡክ መከልከሉ ብቻ ሳይሆን እንደዚህ አይነት ትላልቅ መድረክ ያላቸው ኩባንያዎች የእኛ ተጠቃሚዎችን፣ የአራማጅ ማህብረሰቡን፣ የመገናኛ ብዙሃኑን ሳንሱር የሚያደርጉ ከሆነ፣ የምትለጥፈውን ነገር እንዳትለጥፍ የሚያደርጉ ከሆነ፣ እንዳትጠቀመው የሚያደርጉ ከሆነ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በግለሰብ ደረጃ እየሆነ ከሆነ ይህን የሚያደርጉት እንደመገናኛ ብዙሃን ሰዎች ፌስ ቡክን እንደ ምንጭ እንጠቀማለን ስለዚህ ያንተንም ሆነ የእኔ መረጃ ምን ያህል ደህንነቱ የተጠበቀ ነው የሚለው በጣም ነው የሚያስፈራው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፌስ ቡክ ጋር ዘለግ ያለ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ እየያዝን ነው፡፡ ምናልባትም ሌሎች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችንም የምናደርግ ይሆናል” ሲሉ ወደፊት ሊወስዱ ስላሰቡት እርምጃ ለዶይቼ  ቬለ ተናግረዋል።  

Äthiopien Siraj Fegesa
ምስል DW/Y.G.Egiziabher

ከፌስ ቡክ ገጻቸው ጋር ለ36 ሰዓታት ተቆራርጠው የነበሩት አቶ ጀዋር ሐሙስ ምሽት ገጻቸውን መልሰው መጠቀም መቻላቸውን ይፋ አድርገዋል። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የተያያዙ እና ሌሎችም መረጃዎችንም ማጋራት ቀጥለዋል። በእርሳቸው ገጽ በጉልህ እንደሚስተዋለው ሁሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከተለያዩ ሁነቶች ጋር አቆራኝተው ሲያነሷቸው ሰንብተዋል። በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጌታቸው አምባዬ በኩል ይፋ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም መመሪያ እና አዋጁን ለመተግበር የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የሰጡት መግለጫም መወያያ ሆኗል፡፡ 

አቶ ሲራጅ "በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው አለመረጋጋት የቀለም አብዮት መልክ እየያዘና በግልጽ ስልጣን የመፈለግ አዝማሚያ እየታየበት መሆኑን"መግለጻቸው አነጋግሯል። የሀሩን ቲዩብ አዘጋጁ አብዱራሂም አህመድ በትዊተር ገጻቸው "ኢሕአዴግ አንዴ ኮማንድ ፖስት አንዴ የቀለም አቢዮት ከምትል የህዝብን ብሶት ስማና ለሀገራችን የሚበጀውን ጊዜው ሳይረፍድ አድርግ" ሲሉ መክረዋል። ደረጀ አቶምሳ በፌስቡክ "ለመሆኑ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የቀለም አብዮትን ትርጉም ያውቁታል ወይ? የቀለም አብዮት ማለት ሠላማዊ ትግል ነው። ሠላማዊ ትግል ነው ብሎ ካመኑ ምኑ ነው ጥፋቱ? ወይስ ሰውየው የመጡበትን ነው የሚያወሩት?" ሲሉ ጠይቀዋል።

ኤልያስ ግደይ በበኩላቸው “የቀለም አብዮት ፤ ኢትየጵያ ውስጥ የመሳካት እድሉ ዜሮ ነው፡፡ ግብፅ፣ ቱኒዚያም ሆነ ሊቢያ ምን አተረፉ? ወታደራዊ መንግስት፡፡ አክቲቪስቶቹም፤ ፀፀት እና እስር፡፡ በአመፅ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አይመሰረትምና” ብለዋል በፌስቡክ ገጻቸው። “የሰሞኑ ቋንቋ ደግሞ የቀለም አብዮት ነው” ሲሉ የጻፉት አንዋር አንዋር የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ደግሞ በነገሩ ላይ ምጸታዊ  አገላለጽን መጠቀም መርጠዋል። “አሁን ደግሞ በቀለም ያሸበረቀ ልብስ ለብሰን ስንሄድ የቀለም አብዮት ብለው ሊያስሩን ነው ማለት ነው!? ሴቶችዬ ጠንቀቅ በሉ” ሲሉ ተሳልቀዋል። 

ተስፋለም ወልደየስ