1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከስፖርቱ ዓለም

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 1 2005

36ኛው የማዕከላዊና ምሥራቅ አፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ሰንበቱን በአስተናጋጇ በኡጋንዳ አሸናፊነት ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/16zJ4
ምስል Getty Images/AFP

36ኛው የማዕከላዊና ምሥራቅ አፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ሰንበቱን በአስተናጋጇ በኡጋንዳ አሸናፊነት ተፈጽሟል። ኡጋንዳ ለዚህ ድል የበቃችው የፍጻሜ ተጋጣሚዋን ኬንያን 2-1 በመርታት ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ ባለፈው ማክሰኞ ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያው በኡጋንዳ 2-0 ተረትቶ ቀድሞ መሰናበቱ አይዘነጋም።

ቡድኑ አዲስ መጤዋን ደቡብ ሱዳንን በምድብ-አንድ መክፈቻ ግጥሚያው 1-0 ከመርታቱ በስተቀር ተጨማሪ ስኬት ሳያገኝ ቀርቷል። ለመሆኑ ውድድሩ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ምን ትርጉም ወይም ክብደት ነበረው? ለመጪው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ለሚደረገው ዝግጅትስ ምን ልምድ ለመቅሰም ተችሏል? እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን በተመለከተ ዛሬ ቀትር ላይ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌደሬሺን የግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቶ መላኩ አየለን በስልክ አነጋግሬ ነበር፤ ቃለ ምልልሱን ያድምጡ!

እግር ኳስ ከየትኛውም የስፖርት ዓይነት ይልቅ በዓለም ላይ ዝነኛውና ተወዳጁ ቢሆንም አስከፊ ገጽታ ሊኖረው እንደሚችልም በቅርቡ በኔዘርላንድ የ 41 ዓመቱ ዳኛ ሪሻርድ ኒውቨንሁይዘን በወጣት ተጫዋቾች ተደብድቦ መሞቱ እንደገና አሳይቷል። በአፍሪቃም ቢሆን እግር ኳስ የሃይማኖትን ያህል ተመላኪ ሲሆን በግብጽ ለምሳሌ አሌክሣንድሪያ ውስጥ በስታዲዮም ዓመጽ 74 ሰዎች መገደላቸው የሊጋው ውድድር እንዲቋረጥ አድርጎ ነው የቆየው። ዛሬ የግብጽ ሕብረተሰብ በአዲስ ውዝግብ ተወጥሮ በሚገኝበት ወቅት ደግሞ የባሰ እንዳይመጣም ያሰጋል።

Das Spiel
ምስል DW

ግብጽ ውስጥ ለነገሩ እግር ኳስና ፖለቲካ የተሳሰሩ ሆነው ነው የኖሩት። የተለያዩት ጽንፈኛ የየክለቡ ደጋፊ ቡድኖችም የተደራጀ ባህርይ ያላቸው ናቸው። ጀርመናዊው የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር ያን ቡሰ የዓለምአቀፉ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የአምነስቲይ ኢንተርናሺናል ባልደረባ ሲሆኑ የግብጽን እግር ኳስ መድረክም በቅርብ የሚከታተሉ ናቸው። በርሳቸው አባባል ለምሳሌ ዝነኛው ክለብ አል አህሊ የግብጽ ሕዝብ መለያ ሆኖ ነው የሚታየው።   

አል አህሊ በግብጻውያን በራሳቸው የተመሠረተው የመጀመሪያው ክለብ ሲሆን በብሪታኒያ ቅኝ ገዢዎችና በአገሪቱ የዘውድ አገዛዝ አንጻር ብሄራዊ መለያ ነበር። ያን ቡሰ የየክለቡ ደጋፊ ቡድኖች በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ያላቸውን ጠንካራ ሚና ሲጠቅሱ ስታዲዮሞችም ብሶትን ለመግለጽ አመቺ ቦታዎች ሆነው መኖራቸውን ያስታውሳሉ።

«አንድ ሕብረተሰብ ድህነት የሰፈነበት፤ ወይም እንደ ሙባራክ ዘመን ጭቆናም የተጫነው ከሆነ የኳስ ሜዳዎች ሁሌም ብሶትን መግለጫና መሸሻ ቦታዎች ሆነው ኖረዋል። መተንፈሻዎች ናቸው። ይህን መሰሉ ነገር በእግር ኳስ ዘንድ ብቻ ያለ ይመስለኛል» 

ለማንኛውም የግብጽ እግር ኳስ ክለቦች ተከታዮች ሆስኒ ሙባራክን ከሥልጣን ለማስወገድ በተደረገው ትግል ጠቃሚ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ አሁንም የሞሐመድ ሙርሢን መንግሥት በመታገል ላይ መሆናቸው ነው የሚነገረው። ያን ቡሰ እንደሚያስረዱት ጽንፈኞቹ ቡድኖች ከሙስሊም ወንድማማቾች ቀጥለው በሚገባ የተደራጁት ወገኖች ናቸው። ይህ ጥንካሬ እርግጥ ለፍትህ ስራ ላይ ከዋለ ጉዳት የለውም። ከዚህ ውጭ ግን ትርፉ ጉዳት በቻ ነው የሚሆነው።        

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ