1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከስፖርቱ ዓለም

ረቡዕ፣ የካቲት 6 2005

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የተካሄደው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባለፈው ምሽት በናይጄሪያ አሸናፊነት ተፈጽሟል። ናይጄሪያ ከረጅም ጊዜ በኋላ ለሶሥተኛ የአፍሪቃ ዋንጫ ድሏ የበቃችው በጆሃንስበርጉ ሶከር-ሢቲይ

https://p.dw.com/p/17cC4
ምስል Reuters

ስታዲዮም በተካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያ ቡርኪና ፋሶን በመደበኛ ጊዜ 1-0 በመርታት ነው። ለናይጄሪያ ብቸኛዋን የድል ጎል በመጀመሪያው አጋማሽ ያስቆጠረው ሰንዴይ እምባ ነበር።

ናይጄሪያ ከዚህ ቀደም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ 1980 እና በ 1994 የአፍሪቃ ዋንጫ አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል። ለወትሮው እንደ ቡድን መጣጣም የሚጎለው የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን ዘንድሮ ባልተጠበቀ ሁኔታ አንድነት የሰመረበት ሆኖ ሲታይ ከሰከነ የአጨዋወት ስልቱ አንጻር ዋንጫውን መውስዱ ተገቢ ነው ለማለት ይቻላል። ከ 19 ዓመታት ቆይታ በኋላ ናይጄሪያን መልሰው ለድል ያበቁት ተጫዋቾችም ዛሬ በአገሪቱ ፕሬስ «የአፍሪቃ ነገሥታት» በመባል በሰፊው ነው የተወደሱት።

ለአገር ውስጥ ተጫዋቾች ሰፋ ያለ ዕድል በመስጠቱ በጅምሩ ትችት ዘንቦበት የነበረው የቡድኑ አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺም እንዲሁ እንደ ተጫዋችና እንደ አሰልጣኝ ለዋንጫ ባለቤትነት በመብቃት ከግብጻዊው ከሞሐመድ-ኤል-ጎሃሪይ አቻ መሆኑ ተሳክቶለታል። የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን አንደኛ በመውጣቱ የ 1,5 ሚሊዮን ኤውሮ ሽልማትም ሲያገኝ ድሉ በፊታችን ሰኔ ወር ብራዚል ውስጥ ለሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የፊፋ ኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ተሳትፎም የሚያበቃው ነው። በዚያም ስፓኝንና ኡሩጉዋይን የመሳሰሉት ታላላቅ ቡድኖች ይጠብቁታል።

Sport Fußball Africa Cup of Nations 2013 Finale Nigeria Burkina Faso
ምስል Getty Images

የቡርኪና ፋሶ ብሄራዊ ቡድንም ቢሆን በፍጻሜው ግጥሚያ ቀደም እንዳሉ ጨዋታዎቹ ጠንክሮ መታየቱ ባይሆንለትም ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍጽሜ መድረሱ ራሱ የሚደነቅ ውጤት ነው። ቡድኑ በግማሽ ፍጻሜው ጋናን ያህል ከባድ ተጋጣሚ አልፎ ለፍጻሜ መብቃቱን የጠበቁት ብዙዎች አልነበሩም። የቤልጂጉ ተወላጅ አሰልጣኝ ፓውል ፑትም ቡድኑን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ላሳየው ጨዋታ በጣሙን ነው ያደነቀው። በውድድሩ በጠቅላላው ከታዩት ተመልካችን ካረኩ ግጥሚያዎች መካከልም አይቮሪ ኮስት ከቱኒዚያ፤ ደቡብ አፍሪቃ ከሞሮኮ፤ አይቮሪ ኮስት ከናይጆሪያና ቡርኪና ፋሶ ከጋና፤ እንዲሁም ከኛ አንጻር ኢትዮጵያ ከዛምቢያ ነበሩ።

የዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጫ ከሣሪዎች እንዳለፉት ውድድሮች ሁሉ በተለይም የአይቮሪ ኮስት ዓለምአቀፍ ከዋክብት ናቸው። አይቮሪ ኮስት ገና በሩብ ፍጻሜው በናይጄሪያ ተሸንፋ ስንብት ስታደርግ የቡድኑ አምበል ዲዲየር ድሮግባ፣ ወንድማማማቾቹ ኮሎና ያያ ቱሬ ወይም ዲዲየር ዞኮራ በአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ታሪክ ውስጥ የአገሪቱ የሽንፈት መለያ ሆነው እንደሚኖሩ አንድና ሁለት የለውም። ለዚህ ደግሞ ዓለም ያወቃቸው ከዋክብት ራሳቸውን እንጂ ሌሎችን ሊወቅሱ አይችሉም።

ብዙዎች እንደ ዋንጫ ባለቤት ያዩዋት ጋናም በቀላል ተጋጣሚ ተሸንፋ በግማሽ ፍጻሜው መገታቷ ምናልባት ለረጅም ጊዜ የሚከነክናት ነው የሚሆነው። ሌላ የሚጠቀስ ድክመት ካለ ያለፈው ዋንጫ ባለቤት ዛምቢያ ገና ከጅምሩ በምድቡ ዙር ተወስና መቅረቷና በተለይ ደግሞ ከጠንካሮቹ የማግሬብ ሃገራት ከቱኒዚያ፣ አልጄሪያ ወይም ሞሮኮ አንዱ እንኳ ለሩብ ፍጻሜ ሳይደርስ መቅረቱ ነው። የደቡብ አፍሪቃ እንደ አስተናጋጅ አገር በሩብ ፍጻሜ ተሰናብቶ መቅረትም ደካማነት ነው።

Africa Cup Team Äthiopien vs Sambia
ምስል DW

በተረፈ 29ኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ከ 31 ዓመታት በኋላ ወደ ውድድሩ ለተመለሰችው ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የትምሕርት ሆኖ አልፏል። በሌላ በኩልም ቡድኑ ደረጃን የጠበቀ እግር ኳስ መጫወት እንደሚችል ለራሳቸው ለተጫዋቾቹ ብቻ ሣይሆን ቁልቁል ሲያዩዋቸው ለቆዩት ሃገራት ጭምር ያመለከተም ነበር። ይህም መልካም ነገር ነው። ለተሻለ ውጤት ለመብቃት ምን ምን መደረግ እንደሚኖርበት ባለፈው ሣምንት ፕሮግራማችን ያመላከትነው ነገር ሲሆን ዛሬ እንደገና አንመለስበትም።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በታላላቅ ውድድሮች ግንባሩን ሊያሰምታ የሚችል የብሄራዊ ቡድን ጽንስ ማፍረቷ እሰዬ የሚያሰኝ ሲሆን እርግጥ ጉዞው ወደፊት እንዲሆን አሁን ምርጫው ሳይውል ሳያድር ዕጅን ጠቅልሎ ለሥራ መነሣት፤ የጎደለውን ማሟላት ነው። በተቀዳሚም ቡድኑ ለዓለም ዋንጫና ለቀጣዩ የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜዎች ለመድረስ በሚያካሂዳቸው ማጣሪያ ግጥሚያዎች ስኬት እንዲያገኝ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ሊያገኝ ይገባዋል። መጪው 30ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያን ከተሳትፎ ባሻገር ለጥሩ ውጤት የሚያበቃ እንዲሆንም ምኞታችን ነው።

Fußball Bundesliga 21. Spieltag FC Bayern München FC Schalke 04
ምስል Reuters

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች

የአውሮፓ ቀደምት የእግ ኳስ ሊጋዎች ውድድር በመልሱ ዙር እየገፋ ሲሆን ሰንበቱ ያለፈው ታላላቁ ክለቦች ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ባየርን ሙኒሺንና ባርሤሎና በየፊናቸው አመራራቸውን ባጠናከሩበት ሁኔታ ነው። ኤፍ ሲ ባርሤሎና ጌታፌን 6-1 ቀጥቶ በመሸኘት አመራሩን ወደ 12 ነጥቦች ከፍ ሲያደርግ ሁለተኛው አትሌቲኮ ማድሪድ በአንጻሩ በቫሌካኖ 2-1 ተሸንፏል። የአትሌቲኮ መሸነፍ ሶሥተኛው ሬያል ማድሪድ የከተማ ተፎካካሪውን እስከ አራት ነጥቦች ልዩነት እንዲቃረብ ነው ያደረገው። ሬያል ማድሪድ በበኩሉ ግጥሚያ ሤቪያን 4-1 ረትቶ ነበር።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ማንቼስተር ዩናይትድ ትናንት ኤቨርተንን 2-0 ሲያሸንፍ አመራሩን እንደ ባርሣ ሁሉ በ 12 ነጥቦች ለማስፋት በቅቷል። ለዚሁ ምክንያት የሆነውም የሁለተኛው የማንቼስተር ሢቲይ በሳውዝሃምፕተን 3-1 መረታት ነው። ማንቼስተር ዩናይትድ በወቅቱ ሂደቱ ዘንድሮ ለሃኛ የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫው የሚበቃ ነው የሚመስለው። ሶሥተኛው ቼልሢይም ካለፉት ሣምንታት ክስረቱ በኋላ ዊጋን አትሌቲክን 4-1 በማሸነፍ እንደገና ነፍስ ዘርቷል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን ሻልከን 4-0 ሲያሸንፍ ከ 2010 ወዲህ እንደገና ለሻምፒዮንነት እየተቃረበ ነው። ባየርን አሁን ሊጋውን በ 15 ነጥቦች ልዩነት የሚመራ ሲሆን ሁለተኛው ዶርትሙንድ በሃምቡርግ በደረሰበት 4-1 ሽንፈት ስለ አንደኝነት ማለሙን መተዉ ግድ ሆኖበታል። ውድድሩ ሊጠናቀቅ ገና 13 ግጥሚያዎች ሲቀሩ ፉክክሩ ይበልጡን በአውሮፓ ሽምፒዮና ሊጋ ተሳትፎና ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ላይ የሚያተኩር ነው የሚመስለው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ ፊዮሬንቲናን 2-0 በማሸነፍ አመራሩን ወደ አምሥት ነጥቦች ሲያሳድግ ሁለተኛው ናፖሊና ሶሥተኛው ላሢዮ እርስበርሳቸው ባደረጉት ግጥሚያ 1-1 ተለያይተዋል። ኢንተር ሚላን ቺየቮን 3-1 ሲረታ ከላሢዮ አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ አራተኛ ነው። በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ውድድርም ባስቲያን 3-1 ያሸነፈው ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ዋነኛ ተፎካካሪው ኦላምፒክ ሊዮን በሊል በመረታቱ ለስድሥት ነጥቦች አመራር በቅቷል።

በኔዘርላንድ የክብር ዲቪዚዮን ፋየኖርድ ሮተርዳም አልክማርን 3-1 በማሸነፍ አንደኛውን አይንድሆፈንን በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ተቃርቧል። ፋየኖርድን ለድል ያበቁት በተለይ ወጣት ኮከቦቹ ዣን-ፓውል-ቡቲዩስና ቶኒያ ፊሄና ናቸው። አይንድሆፈን በበኩሉ ግጥሚያ ከአርንሃይም በእኩል ለእኩል ውጤት ሲወሰን አያክስና ኤንሼዴም አንዳንድ ነጥብ መጣል ተገደዋል። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ቀደምቱ ፖርቶና ቤንፊካ በየበኩላቸው ግጥሚያዎች በአቻ ውጤት ሲወሰኑ በእኩል 46 ነጥቦች መምራታቸውን እንደቀጠሉ ነው።

Tennis Australian Open - Victoria Azarenka
ምስል Reuters

ቴኒስ

የስፓኙ ኮከብ ራፋኤል ናዳል ቺሌ ውስጥ በቪና-ዴል-ማር በተካሄደ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድር ትናንት በነጠላና በጥንድ ፍጻሜ ግጥሚያዎች መሸነፉ ግድ ሆኖበታል። ጉልበቱ ላይ ደርሶበት በነበረ ጉዳት ለሰባት ወራት ሳይወዳደር ለቆየው ለናዳል ውጤቱ አስከፊ ነው የሆነው። ራፋኤል ናዳል በነጠላ በአርጄንቲናዊ ተጋጣሚው በሆራኪዮ ዜባሎስ በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 ሲሸነፍ በጥንድም ከሁዋን ሞናኮ ጋር በመሆን ከኢጣሊያ ተጫዋቾች ከፓኦሎ ሎሬንሢና ከፖቲቶ ስታራሴ ባደረገው ግጥሚያ 6-2,6-4 ተረትቷል።

ከዚሁ ሌላ ሰንበቱን ተካሂደው በነበሩ የዓለም ፌደሬሺን-ካፕ ምድብ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች የሚከተሉት ውጡቶች ተመዝግበዋል። ቼክ ሬፑብሊክ ኦስትራቫ ላይ አውስትራሊያን 4-0 ስታሸንፍ ኢጣሊያም ሪሚኒ ላይ አሜሪካን 3-2 ረትታለች። ሩሢያ ደግሞ ጃፓንን ሞስኮ ላይ 3-2 ስታሸንፍ ስሎቫኪያም ሰርቢያን በተመሳሳይ ውጤት ረትታለች። በተጨማሪ ስዊትዘርላንድ ከቤልጂግ 4-1፤ ስዊድን ከአርጄንቲና 3-2፤ እንዲሁም ስፓኝ ከኡክራኒያ 3-1 ተለያይተዋል።

በተቀረ በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ በሴቶች ቪክቶሪያ አዛሬንካና በወንዶች ደግሞ የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች ቀደምት ሆነው መምራታቸውን እንደቀጠሉ አዲስ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል። የቤላሩሧ አዛሬንካ በ 10,325 ነጥቦች የምትመራ ሲሆን ሤሬና ዊሊያምስ በ 9,970 ሁለተኛ፤ማሪያ ሻራፖቫ ደግሞ በ 9,545 ሶሥተኛ ናት። በወንዶች ኖቫክ ጆኮቪች በ 12,960 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ሮጀር ፌደረርና ኤንዲይ መሪይ ራቅ ብለው ይከተሉታል።

በእግር ኳስ ለማጠቃለል ነገና ከነገ በስቲያ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የጥሎ ማለፍ ሩብ ፍጻሜ ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት ሤልቲክ ግላስጎው ከጁቬንቱስ ቱሪን የሚገናኝ ሲሆን ቫሌንሢያ ደግሞ የፓሪስ-ሣንት-ዠርማን አስተናጋጅ ነው። በማግሥቱ ረቡዕም የኡክራኒያው ሻህትዮር ዶኔትስክ ከጀርመኑ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ፤ እንዲሁም ሬያል ማድሪድ ከማንቼስተር ዩናይትድ ይጋጠማሉ። በተለይ ይሄው የመጨረሻው የሬያልና የማኒዩ ግጥሚያ በታላቅ ጉጉት ነው የሚጠበቀው።

ከሣምንት በኋላም አርሰናል ከባየርን ሙንሺን፤ ፖርቶ ከማላጋ፤ ጋላታሳራይ ኢስታምቡል ከሻልከና ኤ ሲ ሚላን ከባርሤሎና ቀጣዮቹ ጨዋታዎች ይሆናሉ። እዚህም አርሰናል ከባየርንና ሚላን ከባርሤሎና ክብደት የሚሰጣቸው ግጥሚያዎች ናቸው። የመልስ ግጥሚያዎቹ የካቲት 26 እና 27 ይካሄዳሉ።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ