1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከስፖርቱ ዓለም

ሰኞ፣ ሚያዝያ 28 2005

በአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ትናንት በኢጣሊያና በኔዘርላንድ ሻምፒዮናው ለይቶለታል።

https://p.dw.com/p/18T3L
ምስል picture-alliance/dpa

በጀርመን ባየርን ሙንሺን ቀደም ብሎ ሻምፒዮንነቱን ማረጋገጡ የሚታወስ ሲሆን የስፓኙ ባርሤሎናም ከግቡ ሊደርስ ምንም ያህል አልቀረውም። ይህ በዚህ እንዳለ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር የጀርመን ክለቦች የስፓኝ ተጋጣዎቻቸውን አሸንፈው ለፍጻሜ ካለፉ ወዲህ ማን ከማ ይበልጥ የሁለቱን ሃገራት የእግር ኳስ ጥንካሬ ማነጻጸሩ ቀጥሏል።

በሊጋው ሻምፒዮና ላይ እናተኩርና ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ጁቬንቱስ በትናንትናው ዕለት ፓሌርሞን 1-0 በማሸነፍ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ የኢጣሊያ ሤሪያ-አ ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል። ለዩቬ በ 59ኛዋ ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን የግጥሚያውን ጎል ያስቆጠረው የቺሌው ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች አርቱሮ ቪዳል ነበር። ጁቬንቱስ ያለፉ ስምንት ግጥሚያዎቹን በሙሉ በማሸነፍ ብርቱ ጥንካሬ ሲያሳይ በአጠቃላይ ለ 29ኛ ለሻምፒዮንነቱ የበቃውም ሁለተኛውን ናፖሊን በ 11 ነጥቦች በመብለጥ ነው።

ናፖሊ በበኩሉ ግጥሚያ ኢንተር ሚላንን 3-1 ረትቷል። ኤሢ ሚላን ቶሪኖን 1-0 ረትቶ በሶሥተኝነቱ ሲቀጥል ለመጪው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ተሳትፎ የሚያበቃውን ቦታ ለማስከበር በሮማ ሽንፈት የደረሰበትን አራተኛውን ፊዮሬንቲናን በአራት ነጥቦች ልዩነት ማራቁ ሆኖለታል። በተቀረ ሮማ አምሥተኛ ሲሆን ቦሎኛን 6-0 የቀጣው ላሢዮ ደግሞ ከኡዲኔዘ ቀጥሎ ሰባተኛ ነው። በነገራችን ላይ ለላሢዮ ከስድሥት አምሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው የጀርመኑ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ሚሮስላቭ ክሎዘ ነበር። የመጨረሻው ፔስካራ ደግሞ ውድድሩ ሊጠቃለል ገና አራት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ከወዲሁ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ተከልሷል።

Kombo-Bild van der Wiel Taiwo Coentrao
ምስል DW/AP

ከኢጣሊያ ሌላ በኔዘርላንድም ሻምፒዮናው ሲለይለት ቀደምቱ ክለብ አያክስ አምስተርዳም ቲልቡርግን 5-0 በመሸኘት በአራት ነጥቦች ልዩነት በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ የክብር ዲቪዚዮኑ ሻምፒዮን ለመሆን በቅቷል። አያክስ የዳች ሻምፒዮን ሲሆን በጠቅላላው ለ 32ኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ሁለተኛው አይንድሆፈን ደግሞ በበኩሉ ግጥሚያ ኒሜኸንን 4-2 በማሸነፍ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የሚያበቃውን ቦታ እንደያዘ ቀጥሏል።

የአያክስ በተከታታይ ሻምፒዮን ሊሆን መብቃት ምክንያቱ የራሱ ጥንካሬ ብቻ ሣይሆን የተፎካካሪዎቹ ጽናት ማጣትም ጭምር ነው። አይንድሆፈንም ሆነ ፋየኖርድ ወይም ኤንሼዴ በውድድሩ መጀመሪያ ያሳዩትን ጥንካሬ እስከ መጨረሻው ሊገፉበት አልቻሉም። ይህ ለመጪው ውድድር ወቅት ጠቃሚ ትምሕርት እንደሚሆናቸው አንድና ሁለት የለውም። ከኔዘርላንድ ባሻገር እፍ ሲ ኮፐንሃገን ለአሥረኛ ጊዜ የዴንማርክ ሻምፒዮን ሲሆን በቱርክም ጋላታሳራይ ኢስታምቡል ለ 19ኛ ሻምፒዮንነቱ በቅቷል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና በአምሥት ዓመታት ውስጥ አራተኛ ሻምፒዮንነቱን ለማክበር በጣሙን ተቃርቧል። ቡድኑ ሬያል ቤቲስን 4-2 ሲረታ የድሉ ዋስትናም በተለይ በ 56ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ሊዮኔል ሜሢ ነበር። ባርሣ አራት ግጥሚያዎች ቀርተው በ 11 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ሁለተኛው ሬያል ማድሪድ በፊታችን ረቡዕ ማላጋን መርታት ከተሣነው ሻምፒዮንነቱን ያረጋግጣል። በፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ውድድር አትሌቲኮ ማድሪድ ሶሥተኛ ሲሆን ሬያል ሶሢየዳድ አራተኛ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የማንቼስተር ዩናይትድ ሻምፒዮንነት ያለቀለት ነገር ሲሆን ትልቁ ፉክክር ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ተሳትፎ ለመብቃት በሶሥተኛና በአራተኛው በቼልሢይና በአርሰናል መካከል የተያዘው ነው። ሁለቱን ክለቦች የምትለያቸው አንዲት ነጥብ ብቻ ስትሆን ቼልሢይ በተለይም ትናንት ሻምፒዮኑን ማንቼስተር ዩናይትድን 1-0 በመርታት ጠቃሚ ዕርምጃ አድርጓል። ውድድሩ ሊጠቃለል ሶሥት ጨዋታዎች ሲቀሩ ከአርሰናል አንጻር አንድ ግጥሚያ የሚጎለው ቼልሢይ ሶሥተኝነቱን ለማስከበር የተሻለው ዕድል አለው።

Fußball Bundesliga 32. Spieltag Borussia Dortmund FC Bayern München Elfmeter
ምስል picture-alliance/dpa

የጀርመን ቡንደስሊጋ ሻምፒዮን ማንነት ቀድሞ ቢለይለትም ከሶሥት ሣምንታት በኋላ በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲዮም ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ የሚገናኙት ባየርን ሙንሺንና ዶርትሙንድ ባለፈው ሰንበት በሊጋ ግጥሚያ መገናኘታቸው የብዙዎችን ትኩረት መሳቡ አልቀረም። ግጥሚያው 1-1 በሆነ ውጤት ሲፈጸም ብዙ ሽኩቻ የታየበት ሆኖ አልፏል። ባየርን ሌቨርኩዝን ኑርንበርግን 2-0 በመርታት የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎውን ሲያረጋግጥ በቀሪዎቹ ሁለት ሣምንታት ዋናው ማተኮሪያ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ላለመከለስ በዝቅተኞቹ ክለቦች የሚደረገው ትግል ይሆናል።

ግሮይተር ፉርት ባለፈው ሣምንት ቀድሞ ሲያቆለቁል ብሬመን፣ ዱስልዶርፍና አውግስቡርግ ቀሪዎቹን ግጥሚያዎች የሚያሳልፉት በጭንቀት ነው። በተለይም ከዘጠናኛዎቹ ዓመታት ወዲህ ከቀደምቱ የቡንደስሊጋ ክለቦች አንዱ ሆኖ የኖረው ቨርደር ብሬመን ውድድሩ ሲጀመር እንዲህ ይዳከማል ብሎ ያሰበ ማንም አልነበረም። የሆነው ሆኖ ብሬመን በፊታችን ቅዳሜ በሜዳው ከፍራንክፉርት በሚያደርገው ግጥሚያ ካሸነፈና አውግስቡርግ ደግሞ ቢቀር በእኩል ለእኩል ውጤት ከተወሰነ ቡንደስሊጋ-አንድ ውስጥ መቆየቱን ለማረጋገጥ ይችላል።

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ከቫሌንሢየን በ 1-1 መወሰኑ አመራሩ ወደ ሰባት ዝቅ እንዲል አድርጓል። ውድድሩ ሊጠቃለል አራት ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ ኦላምፒክ ማርሤይ ባስቲያን 2-1 አሸንፎ ሁለተኛ ነው። ሊዮን ናንሢይን 3-0 ሲረታ በሶሥተኝነት ይከተላል። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ቤንፊካና ፖርቶ በአንዲት ነጥብ ብቻ በመለያየት በጦፈ ፉክክራቸው እንደቀጠሉ ነው። ቤንፊካ በ 73 ነጥቦች ቀደምቱ ሲሆን ከፖርቶ አንጻር አንድ ግጥሚያ የሚጎለው በመሆኑ ዕድሉ ምናልባትም የላቀ ነው።

በአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ ሶሥተኛ ዙር የመልስ ግጥሚያዎች የኢትዮጵያው ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም እንኳ ባይሸነፍም ወደ ምድቡ ዙር ማለፉ ሳይሳካለት ቀርቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው ግጥሚያ ከግብጹ ክለብ ከዛማሌክ 0-0 ሲለያይ ያለፈው ሰንበት የመልስ ግጥሚያ በ 3-3 ውጤት መፈጸሙ አልበጀውም። ዛማሌክ በውጭ ሜዳ ጎሎች በማስቆጠሩ ወደፊት አልፏል። ከዛማሌክ ሌላ የኮንጎው ሌኦፓርድ፣ የአንጎላው ሊቦሎ፣ የግብጹ አል-አህሊ፣ የአይቮሪ ኮስቱ ሤዌ ስፖርት፣ የካሜሩን ኮተንና የቱኒዚያው እስፔራንስ ወደ ምድቡ ዙር መሻገሩ ከተሳካላቸው ክለቦች መካከል ናቸው። የምድቡ ዙር በፊታችን ሐምሌ ወር የሚጀመር ሲሆን የሰንበቱ ተሸናፊዎች የኮንፌደሬሺኑን ዋንጫ ውድድር ይቀላቀላሉ።

Hamburg Marathon 2013
ምስል picture-alliance/dpa

ጃሜይካ-ኪንግስተን ላይ ትናንት በተካሄደ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር በሴቶች 1,500 ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያዊቱ ጉደቶ ፈይኔ አሸናፊ ሆናለች። የጃማይካ ተወዳዳሪ ኬኒያ ሢንክሌር ሁለተኛ ስትወጣ አሜሪካዊቱ ሃይዲ ዳል ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽማለች። የዕለቱ አስደናቂ ውጤት አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ በመቶ ሜትር ሩጫ ያስመዘገበው ነበር። ጌይ ጃሜይካዊውን ኔስታ ካርተርን ቀድሞ በ 9,86 ሤኮንድ ጊዜ ነው ያሸነፈው።

ከስድሥት ዓመታት በፊት በ 100, 200 እና በ 4x100 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ለነበረው አሜሪካዊ ግሩም ትንሣዔ ነው። በሴቶች 100 ሜትር ጃማይካዊቱ ቬሮኒካ-ካምፕቤል-ብራውን ስታሸንፍ የለንደን ኦሎምፒክ የ 200 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ አሜሪካዊት አሊሰን ፌሊክስ በአምሥተኝነት ተወስና ቀርታለች። በ 200 ሜትር ሩጫም ድሉ በወንዶችና በሴቶች የጀሜይካ ሲሆን አሜሪካውያን በ 110 ሜትር መሰናክል ቀደምቱ ሆነዋል።

በቶኪዮ ዓለምአቀፍ ውድድር ደግሞ በ 800 ሜትር ሁለት ኬንያውያን ቀድመው ከግባቸው ሲደርሱ በ 5000 ሜትር የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ሃብታምነሽ ተሥፋይ፣ ዓለሚቱ ህሩዬና ገነት ያለው ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል አሸናፊ ሆነዋል። ከመቶ እስከ አራት መቶ ሜትር አብዛኛውን ድል የተጎናጸፉት የአሜሪካ አትሌቶች ናቸው።

በዚህ በጀርመን በሃኖቨር በተካሄደ የማራቶን ሩጫ ደግሞ በወንዶች የደቡብ አፍሪቃው አትሌት ሉሳፎ አፕሪል ያለፈውን ዓመት ድሉን ደግሞታል። የኢትዮጵያ አትሌቶችም ግሩም ውጤት አስመዝግበዋል። መኳንንት አየለ ሁለተኛ ሲወጣ ሶሥተኛ የሆነው ሣሙዔል ደሜ ነው። በሴቶች የኡክራኒያዋ ኦሌና ቡርኮቭስካ ስታሸንፍ ኬንያዊቱ ኤድናህ ኩዋምባይ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ማርታ ለማ ከኢትዮጵያ ሶሥተኛ ወጥታለች።

Box-Weltmeister Wladimir Klitschko besiegt Mormeck
ምስል Reuters

የኡክራኒያው ቭላዲሚር ክሊችኮ ባለፈው ቅዳሚ ምሽት በከባድ ሚዛን ግጥሚያ ሶሥት የዓለም ሻምፒዮንነት ማዕረጎቹን ሊያስከብር ችሏል። ክሊችኮ በጀርመን-ማንሃይም ውስጥ በተካሄደ ግጥሚያ ማዕረጉን ያስከበረው የኢጣሊያ ተጋጣሚውን ፍራንቼስኮ ፒያኔታን በስድሥተኛው ዙር ላይ በመዘረር ነበር። ቭላዲሚር ክሊችኮ በ 63ኛ ፕሮፌሺናል ግጥሚያው ለ 60ኛ ድሉ መብቃቱ ነው። ለኢጣሊያዊው ተጋጣሚ ለፓኒዬታ ደግሞ ሽንፈቱ በሰላሣ ግጥሚያዎች የመጀመሪያው ሆኗል።

በላስ ቬጋስ በተካሄደ ግጥሚያም የዓለም ቡጪ ካውንስል ሻምፒዮን ፍሎይድ ሜይዌዘር ጁኒየር ከአንድ ዓመት ዕረፍት በኋላ የተሣካ መልስ ሊያደርግ በቅቷል። የ 36 ዓመቱ አሜሪካዊ የቀላል ክብደት ክብሩን ያስጠበቀው ባለፈው ቅዳሜ ምሽት የአገሩን ልጅ ሮበርት ጉዌሬሮን በዳኞች አንድ ድምጽ በመርታት ነው። ሜይዌዘር እስካሁን ባደረጋቸው 44 ግጥሚያዎች አንዴም አልተሸነፈም።

Tennis Tommy Haas gewinnt BMW Open München
ምስል CHRISTOF STACHE/AFP/Getty Images

ጀርመናዊው ቶሚ ሃዝ ትናንት በሚዩኒክ-ኦፕን ፍጻሜ ከአገሩ ልጅ ከፊሊፕ ኮህልሽራይበር ጋር ባደረገው ግጥሚያ በሁለት ምድብ ጨዋት 6-3,7-6 አሸናፊ ሆኗል። የ 35 ዓመቱ ቶሚይ ሃዝ በአንድ የኤቲፒ ፍጻሜ ሲያሸንፍ ከአምሥት ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው አንጋፋ ተጫዋች መሆኑ ነው። የማድሪድ-ኦፕን ደግሞ በትናንትናው ዕለት ተከፍቶ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በተረፈ በጂሮ-ዲ-ኢታሊያ የመንገድ ላይ የቢስክሌት ውድድር ትናንት ሁለተኛው ደረጃ እሽቅድድም ከተደረገ በኋላ በቡድን ስካይ ከብሪታኒያ አንደኝነቱን ሲይዝ የስፓኝ ሞቪስታር ሁለተኛ ነው፤ የካዛክስታኑ አስታና ደግሞ በሶሥተኝነት ይከተላል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ