1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከቁም ታሣሪነት ወደ ወህኒ ቤት የተወረወሩት፣ የበርማዋ የቃውሞው ወገን መሪ፣ ሳን ሱቺ፣

ሐሙስ፣ ግንቦት 6 2001

የበርማ የተቃውሞው ወገን መሪ፣ የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋ ወ/ሮ አውንግ ሳን ሱቺ፣ ዛሬ፣ ከቁም ታሣሪነት ወደ መደበኛ እሥር ቤት ከመወርወራቸውም ይፋ ክስ ቀርቦባቸዋል። ምክንያት፣ ባለፈው ሳምንት አንድ አሜሪካዊ፣ መኖሪያ ቤታቸው ድረስ ሄዶ ጎብኝቷቸዋል የሚል ነው።

https://p.dw.com/p/Hqg8
ሳን ሱቺ፣ በመኖሪያ ቤታቸው፣ምስል picture-alliance/dpa

የተባለው አሜሪካዊ፣ በባህር ዋኝቶ፣ ከተከበበው የሳን ሱቺ ቤት በመግባት ጥቂት ቀናት ማሳለፉ የተገለጠ ሲሆን፣ የሳን ሱቺ ጠበቃ እንዳስታወቁት፣ የፍርድ ቤቱ ምርመራ ሰኞ ይቀጥላል። ወ/ሮ ሳን ሱቺ በቀረበባቸው ክስ ከ 3-5 ዓመት እሥራት ሳቢያ ያሠጋቸዋል ነው የሚባለው። 6 ዓመታት በቁም እሥራት ላይ የቆዩት የ 63 ዓመቷ የተቃውሞው ወገን መሪ፣ የፊታችን ግንቦት 19 ነጻ ይለቀቃሉ ተብሎ በመጠበቅ ላይ ነበር። ከደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ Bernd Musch-Borowska ለላከው ዘገባ ጥንቅር፣ ተክሌ የኋላ--

ብሔራዊ የዴሞክራሲ ማኅበር የተሰኘው የበርማ የተቃውሞ የፖለቲካ ድርጅት እናዳስታወቀው፣ አውንግ ሳን ሱቺና 2 ሠራተኞቻቸው ከስ ሳይመሠረትባቸው አልቀረም። በትክክል የተጠቀሰ ጉዳይ ባይኖርም ፣ የቁም እሥራቱን የሚጻረር ተግባር ፈጽማችኋል መባላቸው እንደማይቀር ነው የሚታሰበው። ባለፈው ሳምንት ፣ አንድ የአሜሪካ ዜግነት ያለው፣ ከሳን ሱቺ ቤት በስተጀርባ የሚኖር ሰው የጽጥታ አስከባሪ ኃይሎችም የደረሱበት ሰው፣ በኢንያ ባህር ዋኝቶ፣ በድብቅ ወደ ሳን ሱቺ ቤት በመጓዝ አነጋግሮአቸዋል። በስደት የሚገኙ በርማውያን እንደሚሉት፣ ሰውየው፣ ከ 2 ቀናት በላይ በኖቤል ተሸላሚዋ ቤት ውስጥ ቆይቷል። ሳን ሱቺ፣ ለብዙ ዓመታት በቁም እሥር ላይ ሳሉ ከውጭው ዓለም ጋር ግንኙነት እንዳይኖራቸው ታግደው መቆየታቸው አይዘነጋም። የበርማውያን ስደተኞች ጋዜጣ፣ «ኢራዋዲ»እንደዘገበው፣ አንድ የውጭ ሰው ወደ ሳን ሱቺ የተላከው ምናልባት ሆን ተብሎ ፣ የበርማ ወታደራዊ «ሁንታ» የተቃወሞው መሪ ነጻ እንዲለቀቁ ያስገቡትን ማመልከቻ ዋጋ በማሳጣት የአሥራቱን ጊዜ ለማራዘም ፈልጎ ሳይሆን አልቀረም። በሌላም በኩል አሜሪካዊው፣ ጋዜጠኛ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል።

ካለፉት 19 ዓመታት፣ 13 ቱን ነጻነታቸውን ተነፍገው፣ በተለይ ባለፉት 6 ዓመታት ሳይቋረጥ፣ በቁም እሥር ላይ ያሰለፉት የ 63 ዓመቷ ወይዘሮ፣ ባለፈው ሳምንት ፣ ጤንነታቸው ትንሽ መታወኩ፣ የመዝለፍለፍ ሁኔታ እንደታየባቸው ታውቋል። ለ 12 ወራት ጸንቶ የቆየው ቁም እሥራት፣ ሊያበቃ 2 ሳምንት ነበረ የቀረው።

ባለፈው የካቲት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የኖቤል የሰላም ሽልማት ባለቤት የሆኑት ሳን ሱቺ እንዲለቀቁ ያደረገው ጥረት አንዳች አወንታዊ ውጤት አላስገኘም። በተባበሩት መንግሥታት የብሪታንያ አምባሳደር ጆን ሰውየርስ፣ ኒውዮርክ ላይ በሰጡት ቃል ላይ እንዳሉት፣ የበርማ ወታደራዊ መንግሥት የገባው ቃል ግልጽነት የጎደለው ነው።

«በዚህ ጥያቄና መንግሥቴ አሳሳቢ አድርጎ በሚያያቸው ጉዳዮች ዙሪያ፣ ተጨባጭ ውጤት ባለመገኘቱ በጣም እናዝናለን። በእርግጥ ይህ የሚያሳየው ፣ ጉዳዩ ወደተባባሰ ሁኔታ መገፋቱን ነው።»

በስደት የሚገኙ በርማውያን፣ የፖለቲካ እሥረኞችን የሚደግፉበት የመረዳጃ ማኅበር እንዳስታወቀው፣ በሀገራቸው ከ 3,000 በላይ የፖለቲካ እሥረኞች ይገኛሉ። ብዙዎቹ የጤንነታቸው ይዞታ አሳሳቢ መሆኑን የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ድርጅት HRW አስታውቋል። ድሮ ራሳቸው የፖለቲካ እሥረኛ የነበሩት አውንግ ሚዮ ቴን፣ የፖለቲካ እሥረኞቹ፣ መሠረታዊውን ሰብአዊ መብት የተነፈጉ ናቸው ይላሉ።

«የፖለቲካ እሥረኞቹ፣ በዚያው በእሥር ቤት አድልዎ ይፈጸምባቸዋል፣ ማንኛውም እሥረኛ ያለው መብት ሁሉ ይነፈጋቸዋል። በእሥር ቤቱ ደንብ መሠረት ፣ ማንበብና መጻፍ ይቻላል፣ ነገር ግን፣ ይህም ለፖለቲካ እሥረኞቹ የተነፈገ ነው።»

HRW ፣ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ፣ የበርም የፖለቲካ እሥረኞች፣ ሳን ሱቺ ጭምር በነጻ ይለቀቁ ዘንድ በሰፊው እንዲጥር ጥሪ አስተላልፏል።

ተክሌ የኋላ፣

አርያም ተክሌ፣

►◄