1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከቦኮ ሐራም ጋር ንግግር

ዓርብ፣ ግንቦት 15 2006

በድጋሚ ሽብር፣ በድጋሚ ግድያ፤ ናይጀሪያ ውስጥ የተከሰተው ፍንዳታ በሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲበላሽ እያደረገው ነው ተብሏል። በርካታ ናይጄሪያውያን መንግሥት በአፋጣኝ ከቦኮ ሐራም ጋር መነጋገር ያስፈልገዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

https://p.dw.com/p/1C4mO
ምስል picture-alliance/dpa

ሰሜን ናይጄሪያ ካኖ ውስጥ በሚገኘው የክርስትያኖች መንደር ባለፈው ሰኞ የተከሰተው የአሸባሪዎች ፍንዳታ እንዲሁም ማክሰኞ ዕለት ጆስ ውስጥ በሙስሊሞች እና ክርስትያኖች መካከል የታየው ግጭት ናይጀሪያውያን ስጋት እንዲያድርባቸው አድርጓል። በርካታ የሐይማኖት ተቋማት እና ማኅበራት በሚገኙበት ካዱና ውስጥ የሰፈነው ውጥረት ይበልጥ ስጋቱን አንሮታል። ክርስትያኖች እና ሙስሊሞች ናይጀሪያ ከቦኮሐራም ጋር በአስቸኳይ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል። በናይጄሪያ «የሙስሊም መብት ላዕላይ ምክር ቤት» አባል የሆኑት ባየሮ አብዱላህ ጥላቻውን ከጀርባ የሚያቀጣጥሉት ፖለቲከኞች ናቸው ይላሉ።

«ናይጄሪያ ውስጥ የተከሰተው አብዛኛው ቀውስ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የተባባሰው በፖለቲከኞች ራስ ወዳድነት ነው። ገንዘባችንን መስረቅ ሲፈልጉ ክርስትያን እና ሙስሊም መሪዎች በአንድነት ነው የሚመጡት። ያኔ ስለ እምነት የሚያውቁት ነገር የለም። ገንዘቡን መዝብረው ጥይት እና መሳሪያ በመግዛት ከውጪ ያስገባሉ።»

ቦኮ ሐራምን የተመለከተ ጉባዔ በፈረንሣይ መዲና ፓሪስ
ቦኮ ሐራምን የተመለከተ ጉባዔ በፈረንሣይ መዲና ፓሪስምስል Alain Jocard/AFP/Getty Images

ቄስ ጄምስ ዉዬ የተባሉ ናይጄሪያዊ እና ኢማም ሙሐማድ አሻፋ መንግሥት ከቦኮሐራም ጋር ንግግሩን እንዲያጠናከር አጥብቀው ይሻሉ። ሁለቱ የሐይማኖት አባቶች ቀደም ሲል በነፍስ የሚፈላለጉ ባላንጣዎች ነበሩ። እጎአ ከ2013 አንስቶ ግን ጥላቻቸውን ቀብረው ስለሠላም መስበክ እና መነጋገር ጀምረዋል። ካዱና ውስጥ ለሴቶች መብት የሚሟገቱት ሐፍሳት ሞሐመድ በበኩላቸው ናይጄሪያውያን እምነት ሳይለየን መነጋገር አለብን ይላሉ።

«መተባበር አለብን። ምክንያቱም ይኽ ችግር ሁላችንንም የሚነካ መሆኑን መመልከት ያስፈልገናል። የችግሩ ገፈት ቀማሾች ክርስትያኖችም ሆኑ ሙስሊሞች ናቸው። የክርስትያንም ሆነ የሙስሊም ቤተሰቦች ችግር ደርሶባቸዋል። ሌላው ቀርቶ የሀገሪቱ መንግሥት ጭምር ተጎድቷል። የተፈጠረውን ክፍተት እንደድልድይ ማገናኘት እንዳለብን ይሰማናል። እናም ነገሮችን ከእምነት ውጪ መመልከት ያሻናል።»

በቦኮ ሐራም የታገቱት ልጃገረዶች እንዲመለሱ የሚጠይቅ ሠልፍ
በቦኮ ሐራም የታገቱት ልጃገረዶች እንዲመለሱ የሚጠይቅ ሠልፍምስል Reuters

ብዙዎች ይኽ በሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች መካከል የሚደረገው ንግግር ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ባይ ናቸው። አለበለዚያ አሸባሪዎች በሁለቱ እምነት ተከታዮች መካከል እንዲሰርጽ የሚፈልጉት ጥላቻ ስር ከሰደደ በኋላ ወደ ኋላ ለመመለስ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው ሲሉም አጥብቀው እየሞገቱ ነው።

የንግግሩ አስፈላጊነት ከየአቅጣጫው በሚሰማበት በአሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ በቦኮሐራም የታገቱትትን 200 ልጃገዶች ለማስለቀቅ ትብብር አደርጋለሁ ብላለች። አያይዛም ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ ቻድ የሰፈሩ 80 ወታደሮቿን በፍለጋው ከናይጄሪያ ወታደሮች ጋር እንዲሰማሩ እንደምታደርግ ገልጣለች። ወታደሮቹ ልጃገረዶቹ እስኪለቀቁ ድረስ እንደሚቆዩ የአሜሪካ መንግሥት አስታውቋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዓርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ