1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መሻሻል የሚያሻዉ ከተሞችና የዉኃ አቅርቦት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 19 2009

የዓለምን የዉኃ ይዞታ የቃኘ ጥናት በጎርጎሪዮሳዊ 2016ዓ,ም የሙቀት መጠኑ በመላዉ ዓለም ለተከታታይ 3 ዓመት እጅግ ከፍ ማለቱን ያመለክታል። ይህም መሠረተ ልማታቸዉ ያልተስፋፋ በርካታ የአፍሪቃና የእስያ ሃገራትን ለዉኃ እጥረት እንዳጋለጠም ጠቅሷል። ከምንም በላይ ለሰዎች ሕይወት የንጹሕ ዉኃ ጥያቄዉ አሁንም በቂ ምላሽ እንዳላገኘም አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/2aAJ9
Wassertropfen - Tag des Wasser
ምስል dpa

ከተሞችና የዉኃ አቅርቦት

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለዉ ከ663 ሚሊየን የሚበልጡ ሕዝብ ዛሬም ንጹሕ የመጠጥ ዉኃ ሰለጠንኩ በምትለዉ ዓለማችን እያገኘ አይደለም። ከምንም በላይ በሚኖርበት አቅራቢያ ንጽሕ ዉኃ ባለመኖሩ ረዥም ሰዓታት ተጉዞ ያዉም ለጤና አስጊ የሆነ ዉኃ ለመጠጥ ለመቅዳት መገደዱንም ይዘረዝራል። ይህ የመላዉን ዓለምን ገጽታ የሚያመላክት ነዉ። ዉኃን ለንግድ ማዋሉ እንዳለ ሆኖ የተለያዩ የዉኃ አካላትን በፍሳሽም ሆነ በልዩ ልዩ ነገሮች መበከልም የነገን መዘዝ ያላገናዘበ አሁን የሚታይ መሠረታዊ ችግር ነዉ። የዘንድሮዉን የዓለም የዉኃ ቀን አስመልክቶ ዋተር ኤድ የተሰኘዉ ድርጅት ይፋ ያደረገዉ ዘገባ እንደሚያመለክተዉ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖረዉ 40,9 ሚሊየን ሕዝብ ንጹሕ የመጠጥ ዉኃ አያገኝም። በዚህም ተመሳሳይ ችግር ካለባቸዉ ሃገራት ከሕንድ፣ ቻይና እና ናይጀሪያ ቀጥላ ኢትዮጵያ በአራተኛ ደረጃ ትገኛለች። እንዲያም ሆኖ ግን ከ17 ዓመት በፊት የነበራት ዉሱን የንጹሕ ዉኃ አቅርቦት፤ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የሚያበረታታ ለዉጥ ማሳየቱንም ዘገባዉ በመቶኛ ስሌት ቀምሮ ያሳያል። መረጃዉ አገም ጠቀም አይነት ቢመስልም በተግባር ግን ዉኃ ላይ ተኝታ፤ በዉኃም ተከባ፤ ዛሬም ዜጎቿ ስለ ዉኃ ችግር የሚያወሩባት ሀገር መሆኗ ግልጽ ነዉ። ለዚህም በየከተሞች በየቀኑ ጀሪካን ይዞ ከቦታ ቦታ ዉኃ ፍለጋ የሚንከራተተዉ ወገን አይነተኛ ማሳያ ነዉ። በተለያዩ ጊዜያት ስለ ከተማዋ የዉኃ ችግር ብዙ ተብሎላታል። ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተከናወኑ አንዳንድ ተግባራት ችግሯ የተቀረፈ ቢመስል አሁንም ግን ነዋሪዎቿ ከፈረቃ ዉኃ ጥበቃ እና ያገኟትንም እያብቃቁ ከመጠቀም አላለፉም። ሐረር፤ የቱርስቶች መስሕብ እና እንግዳ አስተናጋጇ ከተማ። እንኳን ለእንግዶቿ ለራሷም ነዋሪዎች ዉኃ አጥሯታል ይላሉ ነዋሪዋ።

Äthiopien Afar Mann schöpft Wasser
በአፋር ምድር ዉድ የሆነዉ ዉኃምስል DW/G. Tedla

ከሐረር ብዙም የማትርቀዉ ድሬደዋም ያላት የዉኃ ጥማት እንዳለ ነዉ። ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲዟዟር የዉኃዉ ችግር ከየት የት ይጠናል የሚለዉን ታዝቧል። አፋር አካባቢ ያስተዋለዉን ግን አይዘነጋዉም። ወደ መቀሌ ሲሄድ ደግሞ በብዙ ደጅ ጥናት የምትመጣዉን ዉኃ ከወተት አመሳስለዉ ነግረዉታል።

በዉኃ ዘርፍ ምርምር እና ጥናት ሁለት ዲግሪዎቻቸዉን ያገኙትና ዉኃን በሚመለከት የመንግሥት መሥሪያ ቤት እና በኋላም በግላቸዉ ላለፉት 23 ዓመታት የሠሩት፤ በዩኒቨርሲቲም ደረጃ በዚሁ ዘርፍ የሚያስተምሩት አቶ ይግዛዉ ሐጎስ በመቀሌ የዉኃ አቅርቦቱ አሁንም ለዉጥ እንደሌለዉ ቢናገሩም። በቅርቡ ግን ሊሻሻል የሚችል ተስፋ አላቸዉ። ስላለዉ የዉኃ አቅርቦት እንዲህ ይላሉ።

Händewaschen in schlammigem Wasser in Pampore
ምስል picture-alliance/dpa

አፋር፤ ሐረር፤ ድሬደዋ፤ እነዚህ አካባቢዎች ሲጠቀሱ ፋ ያለች ፀሐይ፤ ጠንከር ያለ ሙቀት፤ ቆላ እና በረሃማነት ሊታሰብ ይችላል። መሠረተ ልማቱ ባለመስፋፋቱ እንጂ ሌሎች ከቆላማ የአየር ንብረት አልፈዉ በረሃማ በሆኑ ሃገራት ይህ በመሟላቱ፤ ዉኃ አነሰም በዛ በየደጁ መፍሰሱ ሲታይ፤ አቅም እና የታቀዱ መርሃግብሮችን የማስፈጸሙ ጥያቄ ይነሳል። ዉኃን ለኅብረተሰቡ ማዳረስን ዓላማቸዉ ያደረጉ የተለያዩ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በዉኃ አቅርቦት ረገድ ለሚያከናዉኗቸዉ መርሃግብሮች ግዙፍ በጀቶችን እየጠቀሱ ሲንቀሳቀሱ ይታያል። ዘገባዎችንም በየጊዜዉ ሲያቀርቡ ይደመጣል። ዘጋቢያችን ዮሐንስ በዚህ ረገድ የታዘበዉን አጋርቶናል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ!

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ