1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከካሪቡኒ ጋር ወደ አፍሪቃ ጉዞ!

እሑድ፣ ሐምሌ 11 2002

ታድያስ ! ተነሱ ወደ አፍሪቃ እንሂድ ይሰኛል ሰሞኑን በጀርመን ብቅ ያለዉ የሙዚቃ አልብም። በተለያዩ አፍሪቃ አገሮች በሚነገሩ ቋንቋዎች የተቀናበረዉ የሙዚቃ አልብም ታድያስ ወደ አፍሪቃ እንሂድ በማለት አድማጩን በስነ-ልቦና የአፍሪቃ አገራትን ባህል ቋንቋን ያስቀኛል።

https://p.dw.com/p/ONsX
ካሪቡኒምስል Karibuni

የሙዚቃ ቅንብሩ በአፍሪቃ የሚነገሩ ተረቶችን ምሳልያዊ አነጋገሮችን፣ የአፍሪቃን ሁኔታ በታሪክ መልክ እያስረዳ ነዉ አስከትሎ ዜማዉን የሚያስደምጠዉ። ካሪቡኒ የሙዚቃ ቡድን ይህን አፍሪቃን የሚያስተዋዉቅ የሙዚቃ አልብም ለሙዚቃ አፍቃሪዎች ሲያያቀርብ የመጀመርያዉ ባይሆንም አሁን በቅርቡ ለገበያ ባቀረበዉ የሙዚቃ አልብሙ በተለይ የኢትዮጽያን ባህል ወግ እና ታሪክ በማካተቱ በኢትዮጽያዉያን ዘንድ ተወዳጅነቱ ከፍ እንዳለ ይነገርለታል። በጀርመንኛዉ "Tadias! Kommt mit nach Afrika" ታድያስ! ተነሱ ወደ አፍሪቃ እንሂድ እንደ ማለት ሲሆን የሙዚቃ አልብሙ መጠርያ ያካተተዉ ሙዚቃ አፍሪቃዉያን በሚጠቀሙባቸዉ የተለያዩ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች እንዲሁም በዘመናዊ የሙዚቃ መሳርያ የተቀናበረ ነዉ። ዜማዉ በተለያዩ የአፍሪቃ አገር ቋንቋዎች እና በጀርመንኛ ቋንቋ ተተርጉሞ የተዜመና የተቀናበረም ነዉ። በተለይ በኢትዮጽያ፣ በኬንያ፣ በታንዛንያ፣ በታንዛንያ፣ በናይጀርያ፣ በቤኒን፣ በማሊ አገሮች ዉስጥ የሚዘመሩ ባህላዊ ነክ የህዝብ ዜማዎችን እንዲሁም ምሳልያዊ አነጋገሮችን በመዉሰድ ልዮ ዉበት ባለዉ የሙዚቃ ቅንብር ያስደምጣል።
የጀርመኑ የሙዚቃ ቡድን "Karibuni" የተሰኘዉን መጠርያዉን አፍሪቃ ከሚነገረዉ ከኪስዋሂሊ ቋንቋ የወሰደ ሲሆን "Karibuni" ማለት እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት መሆኑንም ቡድኑ በድረ-ገጹ ላይ አስቀምጦአል። የ"Karibuni" መስራቾች ጀርመናዊዉ ፒት ቡደ እና በእናትዋ ኢትዮጽያዊት የሆነችዉ ባለቤቱ ጆሴፊነ ክሮንፍሊ ለመጀመርያ ግዜ የአለም ሙዚቃ ለህጻናት በሚል በጀርመን ሙዚቃቸዉን ይዘዉ ብቅ ያሉት እስካሁን በአጠቃላይ አስር ያህል ሙዚቃ አልብምን ለሙዚቃ አፍቃሪዎች በተለይም ለህጻናት አቅርበዋል። የአፍሪቃን ባህል ቋንቋን የሚያስተዋዉቅ ሁለት አልብም ይፋ በማድረጋቸዉ ታዋቂነታቸዉን ይበልጥ አድርጎታል። ከዚህ ቀደም ባወጡት ሰላም ሻሎም በተሰኝዉ ሙዚቃቸዉ በአለም ዙርያ ተደመጭነትን አግኝተዋል።
በእናትዋ ኢትዮጽያዊት የሆነችዉ የቡድኑ አባል ጆሴፊነ ክሮንፍሊ እናቴ በህጻንነቴ የኢትዮጽያን ባህል አስተምራኛለች፣ ይህንን የተማርኩትን ባህል በማስታወስ እና በመጠቀም በተለይ ልጄን ማስተማር በመፈለጌ ነዉ፣ ይህን ለህጻናት መዝሙርና የትረካ አልብም ከባለቤቴ ጋር ለመጀመርያ ግዜ ለማዉጠት ሃሳብን ልናገኝ የቻልነዉ ስትል ትገልጻለች። በዚህም ሆያ ሆዩ፣ እቴ ሜቴ ሌሎች ሌሎችም በኢትዮጽያ ህጻናት የሚያዜሙዋቸዉን የህዝብ ዜማዎች በባህላዊ እና በዘመናዊ የሙዚቃ መሳርያ በማጀብ በጀርመንኛ በመተርጎም በሚጥም መልኩ ለሙዚቃ አፍቃሪዎች በተለይም ለህጻናት ያቀረቡት። በዚህም ጀርመናዊ ተናጋሪዉን እንደ ኢትዮጽያዉያን ሁሉ እቴሜቴ አዘምረዉታል ሀ ሁ ብለዉ ፊደል አስቆጥረዉታል፣ ሆያ ሆዩም አስጨፍረዉታል። በተለይ ይህ የሙዚቃ አልብም ጀርመንኛ በሚነገሩ አገራት እጅግ ተወዳጅ መሆኑ ሲገለጽ በአዉሮጻ የሚኖሩ ኢትዮጽያዉያን ልጆቻቸዉን በቀላሉ ባህላዊ ነገሮችን ለማስተማር ፊደልም አቆጣጠር ለመግለጽ እንደተዳቸዉ ይገልጻሉ።
ምዕራባዉያን አፍሪቃኛ ቋንቋ ሲሉ አልፎ አልፎ ይደመጣል፣ የካሪቡኒ የሙዚቃ አልብም አፍሪቃ የተለያዩ ባህል ቋንቋ ያላቸዉ ማህበረሰቦች የሚኖሩባት አህጉር መሆንዋን በማስረዳት አፍሪቃን ያስተዋዉቃል። አፍሪቃኛ የሚባል ቋንቋ እንደሌለም በትክክል ይገልጻል! የሙዚቃ አልብሙ ለህጻናት ተባለ እንጂ በጀርመን የሚገኙ አዋቂ ምሁራን ከሙዚቃ አልብሙ ብዙ አዉቀናል ብዙ ተምረናል ማለታቸዉም ተገልጾአል። የእለቱ የባህል መድረካችን የካሪቡኒን የሙዚቃ ቡድን አባል ጆሴፊነ ክሮንግሊን አነጋግሮ ሙዚቃዉንም አጠር አጠር ባለ መልኩ ሊያስደምጠን ተዘጋጅቶአል። ለቅንብሩ አዜብ ታደሰ ነኝ ያድምጡ!

Karibuni Willkommen Kiswahili Tadias CD Cover
ታድያስ ! ተነሱ ወደ አፍሪቃ እንሂድ የተሰኘዉ የሙዚቃ አልብም

አዜብ ታደሰ