1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 ዚምባብዌ እና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

ሐሙስ፣ ጥር 18 2009

ባለፈው ማክሰኞ ፍርድ ቤት ለቀረቡት ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች የቆሙት ጠበቃ ሊዮን ሙሪኒጋኒ እንዳሉት ሰሚ አላገኙም እንጂ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ደቡብ አፍሪቃ መሄድ እንዲፈቀድላቸው ተማጽነው ነበር ።

https://p.dw.com/p/2WSu7
Symbolbild Justiz Richter Gericht Richterhammer
ምስል picture-alliance/dpa/U. Deck

Ethiopian migrants deported from Zimbabwe - MP3-Stereo

በዚምባብዌ አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመሻገር ሲሞክሩ ዚምባብዌ ውስጥ የሚያዙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው ። ዚምባብዌም የሀገሪቱን የኢሚግሬሽን ህግ ጥሰዋል ያለቻቸውን በርካታ ኢትዮጵያውያን አስራለች ። ከመካከላቸው በዚህ ዓመት ታህሳስ የታሰሩ 34 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንዲባረሩ ባለፈው ማክሰኞ ተወሰኖባቸዋል ።
ባለፈው ማክሰኞ ነጭ የእስረኛ ልብስ ለብሰው ፍርድ ቤት ከቀረቡት 34 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች4ቱ ለአካላ መጠን ያልደረሱ እድሜያቸው በ11 እና በ14 ዓመት መካከል የሚገኝ ወጣቶች ነበሩ ። ጉዳያቸውን የተመለከተው ከዚምባብዌ ዋና ከተማ ሀራሬ 84 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የማሮንዴራ ፍርድ ቤት ፣ስደተኞቹ በህገ ወጥ መንገድ ዚምባብዌ ገብተዋል ሲል ወስኖ ወደ ሀገራቸው እንዲባረሩ ለኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት አስረክቧቸዋል ። እነዚህ ባለፉት ዓመታት ዚምባብዌ ውስጥ ተይዘው ወደ ሀገራቸው እንዲባረሩ ከተደረጉት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ስደተኞች ጥቂቶቹ ናቸው ። የተሻለ ህይወት ፍለጋ ከአፍሪቃ ቀንድ ተነስተው ወደ ደቡብ አፍሪቃ ረዥም ጉዞ ከሚያደርጉት በሺህዎች ከሚቆጠሩ ስደተኞች መካከል የኢትዮጵያውያኑ ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም ። ባለፈው ማክሰኞ ፍርድ ቤት ለቀረቡት ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች የቆሙት ጠበቃ ሊዮን ሙሪኒጋኒ እንዳሉት ሰሚ አላገኙም እንጂ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ደቡብ አፍሪቃ መሄድ እንዲፈቀድላቸው ተማጽነው ነበር ። ጠበቃው ከልጅ እስከ አዋቂ ድረስ የሚገኙባቸው እነዚህ ስደተኞች ከሀገራቸው የተሰደዱት ያለ ምክንያት አይደለም ይላሉ ።
«ግጭቶችን ሸሽተው ነው የመጡት ። ሰዎቹን ካየሃቸው ሃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ናቸው ። አንዳንዶቹ ቤተሰቦች አሏቸው።ቤተሰቦቻቸውን ጥለው የመጡም አሉ ። ጥቂቶቹ ደግሞ ለአካለ መጠን አልደረሱም ። ስለ እድሚያቸው እንደተነገረን ከሆነ እስከ 11 ዓመት ዝቅ የሚል እድሜ ያላቸውም ይገኙበታል ። »
በዚምባብዌ የኢምግሬሽን ህግ መሠረት አንድ የውጭ ዜጋ ሳያሳውቅ ወደ ሀገሪቱ ከገባ ህግ ወጥ ስደተኛ ተደርጎ ነው የሚወሰደው ። ወደ 399 የሚሆኑ በዚምባብዌ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመሻገር የሞከሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ዓመት በታህሳስ ወር ወደ ሃገራቸው እንዲባረሩ ተደርጓል ። እነዚህ ስደተኞች  ዚምባብዌ የሚመጡት ለሰው አሻጋሪዎች ብዙ ገንዘብ እየከፈሉ ነው ። ይሁንና የዚምባብዌ ህግ ፣ህገ ወጥ የሚባለውን ስደት የሚያመቻቹት አሻጋሪዎቹ ላይ ሳይሆን እውነተኛ ስደተኞች ላይ ማተኮሩን የሀገሪቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ፕሪስካ ሙፕፉሚራ ይተቻሉ ።በርሳቸው አባባል ግን ዚምባቤዌ የገባ ሁሉ እውነተኛ ስደተኛ ነው ማለት አይደለም ።
«ወንጀለኞቹን እያሳደድን አይደለም ። እውነተኛዎቹን ስደተኞች ነው የምንከታተለው ። ዚምባብዌ ከዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ህግ ፈራሚ ሀገራት አንዷ ናት።ትክክለኛዎቹን ስደተኞች የመንከባከብ ሃላፊነት አለብን ። እኛ ጋ እስከመጡ ድረስ ተቀብለን ልናስተናግዳቸው ልንንከባከባቸው ይገባል ።ሆኖም እውነተኛ እና እውነተኛ ያልሆኑትን ስደተኞች መለየት አለብን ። ሁሉንም አንቀበልም ። »
ዶቼቬለ ዚምባብዌ ውስጥ የሚያዙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለሄደበት ምክንያት በዚምባብዌ የኢትዮጵያ ኤምባሲን አስተያየት ጠይቆ ነበር ። ባለሥልጣናቱ ግን ይፋ መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም ። ሆኖም የኤምባሲው ባለሥልጣናት እንደሚሉት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለመሻገር ሲሞክሩ ዜምባብዌ ውስጥ የሚያዙት ኢትዮጵያውያን የተሻለ ህይወት ይጠብቃችኋል ተብለው እየተታለሉ እንደሚመጡ እና ለጉዞ የሚያወጡትን ገንዘብ በሀገራቸው ሥራ ላይ ቢያውሉት አቅማቸውን ማሳደግ ይችሉ እንደነበር ይናገራሉ ።ወደ ደቡብ አፍሪቃ የመሻገር ሙከራ ሲያደርጉ  ዚምባብዌ ውስጥ ስለሚያዙት ኢትዮጵያውያን  ቁጥር ዶቼቬለ ከዚምባብዌ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ዝርዝር መረጃ ማግኘት አልቻለም ። በጠበቃ ሙሪንጋኒ እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመሄድ ላይ የሚገኘውን ይህን ችግር ከስር መሰረቱ ለመፍትት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና አጋሮቻቸው አንድ መላ መፈለግ አላባቸው ።
«ሀገራቸውን ለቀው የሚሸሹትን ኢትዮጵያውያንን እና ደቡብ ሱዳውያንን ወደመጡበት ማባረር ለችግሩ መፍትሄ አይደለም ። ይህ መፍትሄ የሚሆን አይመስለኝም ። መፍትሄው ጉዳዩ በሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ተፈልጎ ሊገኝ እና ተግባራዊም ሊሆን ይገባዋል ። 
ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚታሰሩት ዚምባብዌ ብቻ አይደለም ። በጎርጎሮሳዊው 2016 ፣ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን በህገ ወጥ መንገድ ማላዊ ገብተዋል ተብለው ታስረዋል ።በቀደመው በ2015 ደግሞ 21 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን  ጭኖ ወደ ዚምባብዊ እና ደቡብ አፍሪቃ ድንበር በማምራት ላይ የነበረ አንድ አውቶብስ ተገልብጦ 3ቱ ሲሞቱ 16 ደግሞ ቆስለዋል ። ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ የሚካሄደው ፀረ የውጭ ዜጎች ዘመቻ ሰለባ እየሆኑ ነው ። 

Karte Ostafrikanische Flüchtlingsroute

 ሙስቫንሂሪ /ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ