1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከግሪክ ዳግም ስደት

ሐሙስ፣ ሰኔ 11 2007

ከተሳካላቸዉ ሽቅብ ወደ ሰሜን ሜቄዶኒያ፤ ሰርቢያ፤ ሐንጋሪ፤ እያሉ----ምናልባት ጀርምን፤ ኖርዌ፣ ስዊድን ወይም ሌላ ስፍራ እስኪደርሱ ይቀጥላሉ።አስቸጋሪዉን ጉዞ ለማሳጠር፤ የፖሊስን ቁጥጥር ለማለፍ «ቀላሉ ዘዴ አንድ ነዉ» ይላል ስደተኛ ኢማል-ለስደተኛ አሸጋጋሪዎች ገንዘብ መክፈል።

https://p.dw.com/p/1FjJz
ምስል Getty Images/AFP/B. Kilic

[No title]

ከየሐገራቸዉ ሸሽተዉ ግሪክ የገቡ ሥደተኞች ከግሪክ ዳግም ወደተቀሩት የአዉሮጳ ሐገራት ለመሰደድ እየተፍጨረጨሩ ነዉ።ግሪክ ዉስጥ ሥራ የማግኘትም ሆነ ጥሩ ኑሮ የመምራት ተስፋ የሌላቸዉ ሥደተኞች እንደ ጀርመን፤ ፈረንሳይ እና ስካዲኔቪያን ወደመሳሰሉት ሐገራት ለመግባት ረጅሙን ርቀት በእግራቸዉ ይጓዛሉ።የየሐገሩን ድንበርና የጠረፍ ጠባቂዎችን ቁጥጥር ማለፉ ግን ከባድ ነዉ።በዚሕም ምክንያት የዶቸ ቬለዉ ቶማስ ቦርማን እንደሚለዉ ስደተኛዉ ከአዉሮጳ ወደ አዉሮጳ የሚያደርገዉ ስደትም በስደተኛ አሸጋጋሪዎች ካልታገዘ ለስደተኞች ከባድ ነዉ።

አብዛኞቹ የሶሪያ፤የኢራቅ፤ የአፍቃኒስታን ዜጎች ናቸዉ።ግሪክ እስኪደርሱ የደረሰባቸዉ ሥቃይ፤መከራ፤ፈተና በርግጥ ከባድ ነዉ።እነሱ ግን እረስተዉታል።ወይም ሌላ ጉዞ ሥለሚሰሰለስሉ ባለፈዉ ለመቆዘም ጊዜ የላቸዉም።ጉዞ-ስደት-ስደት-ጉዞ። የስደት ሰንሰለት።

ከግሪኳ ሰሜናዊ የጠረፍ ትንሽ ከተማ ኢዶሜኒ አጠገብ የሚኖሩት ገበሬ ላዛሮስ ኦዉሊስ የስደተኞቹን ጉዞ እንደ ጥሩ ትርዒት በየዕለቱ ያዩታል።«በዚሕ በኩል ብዙ ያልፋሉ።በየቀኑ አንድ መቶ፤ ሁለት መቶ ይሆናሉ።መጀመሪያ ሜቅዶኒያ እና ከዚያ ጀርመን ነዉ-የምንሔደዉ ይላሉ።እዚሕ እኛ መንደር ልንረዳቸዉም፤ ልንቆጣጠራቸዉም አንችልም።በጣም ብዙ ናቸዉ።ከቤት በወጣሁ ቁጥር እርዱን ይሉኛል።ርቦናል አንድ ሁለት ዩሮ ጣሉብን፤ ዳቦ ወይም አይብም ቢሆን ስጡን ይላሉ።»

ከትንሿ ከተማ ጀርባ የሚጀምረዉ ጫካ እስከ ሜቄዶኒያ ይዘልቃል።ስደተኞቹ ቀኑን ጫካ ዉስጥ አድፍጠዉ ይዉሉና ጨለምለም ሲል ወደ ድንበሩ ይጠጋሉ።።ምሽቱ የጠረፍ ጠባቂዎችን አይን ለመያዝ የመጥቀሙን ያክል፤-አፍቃኒስታናዊዉ ሞኤስ እንደሚለዉ ጉዳትም አለዉ።

Ungarn Flüchtlinge in Asotthalom
ምስል picture-alliance/dpa/Z. G. Kelemen

«ሌሊት በጣም ይበርደናል።ብርድ ልብስ የለንም። ችግራችን ብዙ ነዉ።»----ከብዙዉ ችግር ጥቂቱን ይዘረዝራል-ስደተኛዉ።«የምንበላዉ ምንም የለንም።ወሐ የለንም።እዚሕ እኛን የሚረዳን ማንም የለም።ሌላ ሐገር መሔድ እንፈልጋለን።የሜቄዶኒያ ፖሊስ ግን አያሳልፈንም።»

የሜቅዶኒያ ጠረፍ ጠባቂዎች ቁጥጥር ከባድ ነዉ።በርከት ያለ ስደተኛ ወደ መቆጣጠሪያዉ ኬላ ከተቃረበ ሐገሩ ትቶን የመጣዉን አስደንጋጭ ድምፅ-ዳግም ይሰማታል።ጥይት።

ስደተኞቹ ከሜቄዶንያ ጠረፍ ጠባቂ ፖሊስ ጋር ድብብቆሽ በሚጫወቱበት መሐል ይታመማሉ።ከግሪክዋ የጠረፍ ከተማ ኢንዶሜኒ ዉስጥ ሕክምና የሚሰጣቸዉ፤ ዓለም አቀፉ ግብረ-ሠናይ ድርጅት የድንበር የለሽ ሐኪሞች ያቋቋማት አነስተኛ ክሊኒክ ብቻ ናት።አዉትሬሊያዊቷ ነርስ ዳንኤላ ባላንታይን እንደሚሉት አስልቺዉ ጉዞና እንግልቱ ብዙዎችን እያሳመማቸዉ ነዉ።

«ብዙዎቹ ትናንሽ ጉዳት ነዉ ያለባቸዉ።ቁስል።የተቀሩት ፈሳሽ ማጣትና ድርቀት አለባቸዉ።በቅጡ ሳይመገቡና ሳይጠጡ ረጅም ርቀት ስለሚጓዙ እንዲሕ ዓይነት የጤና ቀዉስ ያጋጥማቸዋል።እዚሕ አየሩ ቀዝቀዝ ያለ ነዉ።በዚያ ላይ ያለመጠለያ ብዙ ጊዜ ሥለሚያሳልፉ ጉንፋን ይይዛቸዋል።እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ወደዚሕ የሚመጡት ወጣት ወንዶች ነበሩ።አሁን ግን ቤተሰቦችም እየመጡ ነዉ።እንግዲሕ መንገዱን የማይችሉ እድሜያቸዉ የጠና ሰዎችም ማየታችን አይቀርም።»

Italien Frankreich Grenze Flüchtlinge
ምስል Reuters/E. Gaillard

ግሪክ ለመግባት አፍቃኒስታን፤ ኢራን፤ ኢራቅ፤ ሶሪያን፤ ቱርክን እያሉ ለተከታታይ ሳምንታት ተጉዘዋል።ለአሸጋጋሪዎች ብዙ ገንዘብ ከፍለዋል።ከእንግዲሕም ከተሳካላቸዉ ሽቅብ ወደ ሰሜን ሜቄዶኒያ፤ ሰርቢያ፤ ሐንጋሪ፤ እያሉ----ምናልባት ጀርምን፤ ኖርዌ፣ ስዊድን ወይም ሌላ ስፍራ እስኪደርሱ ይቀጥላሉ።አስቸጋሪዉን ጉዞ ለማሳጠር፤ የፖሊስን ቁጥጥር ለማለፍ «ቀላሉ ዘዴ አንድ ነዉ» ይላል ስደተኛ ኢማል-ለስደተኛ አሸጋጋሪዎች ገንዘብ መክፈል።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ