1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከፍተኛ የረሃብ ስጋት በደቡብ ሱዳን

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 15 2006

ደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ያሰጋታል ሲል የተመድ የሰብዓዊ እርዳታዎች አስተባባሪ ቢሮ አስጠነቀቀ። ድርጅቱ እንዳለው የደቡብ ሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ እየተባባባሰ በመሄዱ ደቡብ ሱዳን ውስጥ በጣም በቅርቡ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ሊከሰት ይችላል።

https://p.dw.com/p/1CgV2
Sudanesische Flüchtlinge in Äthopien
ምስል DW/C. Wanjoyi

የተባበሩት መንግሥት የምግብና የእርሻ ድርጅት በምህፃሩ FAO የደቡብ ሱዳን ተጠሪ ሚስ ሱ ላውትዘ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ለረሃብ አደጋ ለተጋለጡት ለደቡብ ሱዳን ህዝቦች እርዳታ የሚያስፈልገው በቂ ገንዘብ አልተገኘም ። ተጠሪዋ ለጋሽ ሃገራት ቀሪውን ገንዘብ እንዲሰጡ ጥሪ አስተላልፈዋል። አዜብ ታደሰ ሚስ ሱ ላውትዘን ደቡብ ሱዳን ደዉላ አነጋግራ ዘገባ አጠናቅራለች። የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ ባለፈዉ ሳምንት ባወጣው መግለጫ፤ በደቡብ ሱዳን ያለዉ የምግብ ዋስትና አስተማማኝ ባለመሆኑ፤ በሃገሪቱ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ በቅርብ ጊዜ ዉስጥ ሊታይ እንደሚችል አስጠንቅቋል። የተባበሩት መንግሥት የምግብና የእርሻ ድርጅት በምህፃሩ FAO የደቡብ ሱዳን ተጠሪ ሚስ ሱ ላውትዘም ፤ እንደሚሉት በደቡብ ሱዳን ረሃብ የመከሰቱ ጠንካራ ምልክቶች እየታዩ ነዉ ።

Flüchtlingslager Südsudan
ምስል Reuters

«ባለፉት ወራት በደቡብ ሱዳን ለረሃብ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች እየተጠናከሩ መሄዳቸው ታይቷል ። ሆኖም እስካሁን ረሃብ አላየንም። ያም ሆኖ በአሁኑ ጊዜ በሃገሪቱ የሚገኙ 3.5 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ረሃብ ባንዣበበት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት »

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ዉግያ አቁመዉ በጦርነቱ የተጎዳዉ ሕዝብ ርዳታ እንዲያገኝ የተመድ በተደጋጋሚ ቢያስጠነቅቅም በሃገሪቱ አሁንም ዉግያዉ ጨርሶ አላበቃም። እንደ ሚስ ሱ ላውትዘ የርዳታ ሰጭ ተቋማት የጦርነቱ ሰለባ ሆነዋል ። በዚህ የተነሳም የርዳታ አቅርቦቱ አዝጋሚ ሆኗል ። በሃገሪቱ የሚገኙ አንዳንድ የእርዳታ ማከማቻ መጋዘኖች ሳይቀሩ በጦርነቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል ።

«የውጊያው ባህርይ የሰብዓዊ እርዳታ አቀባይ ቢሮዎችን ና መጋዘኖችን አውድሟል። ከምንም በላይ ደግሞ 1.5 ሚሊዮን ሰዎችን አፈናቅሏል። 450 ሺህ ሰዎች ወደ ጎረቤት ሃገራት ተሰደዋል። የሚገኙበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። ቢያንስ ግን እንደ ስደተኛ እየተረዱ ነው»

በደቡብ ሱዳን የርስ በርሱ ጦርነት ከጀመረ እስካሁን በሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ። ከ 400 ሽ የሚበልጡ ነዋሪዎች ደግሞ መኖርያ ቀዬያቸዉን ለቀዉ ተሰደዋል። ቤት ንብረቱ ወድሞ በሃገሪቱ ዉስጥ ከቦታ ቦታ የተፈናቀለዉ ህዝብም ጥቂት የሚባል አይደለም ።

«የደቡብ ሱዳን ውጊያ በመቀጠሉ ምክንያት እንዳለመታደል ሆኖ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ወደ ቤታቸው መመለስ አይችሉም። ጦርነቱ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው እንዲወጡ ሥራቸውን እንዲያቆሙ ከማድረጉም በላይ ሰብዓዊ እርዳታ ለማግኘት ሲሞክሩም ለአደጋ እየተጋለጡ ነው ። ገበያዎች ወድመዋል ። ሰዎች ያጡት ምግብ ብቻ አይደለም ። የጤና አገልግሎት ውሃ በአጠቃላይ በህይወት ለመቆየት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ አጥተዋል ። በየወሩ ሁኔታው በጣም እየተባባሰ ሲሄድ ነው የምናየው»

Flüchtlingslager Südsudan
ምስል Reuters

በደቡብ ሱዳን ጀርመን የለገሰችዉን ሰብዓዊ ርዳታ ያመሰገኑት የተባበሩት መንግሥት የምግብና የእርሻ ድርጅት FAO የደቡብ ሱዳን ተጠሪ ሚስ ሱ ላውትዘ፤ሌሎች ለጋሾችም የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ ተማፅነዋል ላውትዘ እንደሚሉት ለደቡብ ሱዳን ተጨማሪ ርዳታ ካልተሰጠ ሃገሪቱ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ላይ መዉደቅዋ አይቀርም ። ለሃገሪቱ እርዳታ ለማድረስ የሚያስፈልገውና እስካሁን የተገኘው ገንዘብ ግን እንዳልተመጣጠነ ነው የሚናገሩት።

« 1.8 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ እርዳታ ጠይቀናል። ዛሬ ከጀርመን መንግሥት 19 ሚሊዮን ዶላር አግኝተናል። ። ለተደረገልን እርዳታ ምስጋናችን የላቀ ነው ። ሆኖም በጦርነቱ ክፉኛ የተጎዳውን የደቡብ ሱዳን ህዝብ ለመታደግ በሚያስፈልገውና በተገኘው ገንዘብ መካከል የ1 ቢሊዮን ዶላር ልዩነት አለ»

ገበሪዉ የአዝመራዉን ወቅት ተጠቅሞ እንዲያመርት እና የተጎዳዉ ሕዝብ ርዳታ እንዲያገኝ፤ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ጦርነቱን ለማቆም ቢስማሙም ስምምነቱ ጨርሶ ገቢራዊ አልሆነም። ባሳለፍነዉ ሳምንት መጨረሻ በደቡብ ሱዳን መንግሥት ወታደሮችና በቀድሞዉ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪክ ማቸር የሚመራዉ የአማፅያን ቡድን በስልታዊትዋ የናስር ከተማ ላይ ዳግም ዉግያ መጀመራቸዉ ይታወቃል።

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ