1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ11 ሺህ በላይ ተጠርጣሪወች ከእስር ተፈቱ

ፀሀይ ጫኔ
ሐሙስ፣ ጥር 25 2009

በኢትዮጵያ ሁከት በማነሳሳት ተጠርጥረዉ በቁጥጥር ስር ዉለዉ የነበሩ ከ11 ሽህ በላይ ሰወች ከእስር ተመለቀቃቸዉን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ገለጸ። ተጠርጣሪወቹ ወደህብረተሰቡ ለመቀላቀል የሚያስችላቸዉን  ሁለተኛ ዙር የተሃድሶ ስልጠና ወስደዋል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2Wskw
Karte Äthiopien englisch

Ethiopia release 11 ,000 detainees - MP3-Stereo



በመንግስት ስራ ላይ እያሉ ተጠርጥረዉ የታሰሩ ሰወችም ወደ መደበኛ ስራቸዉ እንደሚመለሱ ተገልጿል። በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢወች ከአመት በላይ የዘለቀዉን ጸረ-መንግስት የተቃዉሞ  እንቅስቃሴ ተከትሎ በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ ከታወጀበት ካለፈዉ መስከረም ወር ጀምሮ በሽህ የሚቆጠሩ ሰወች ሁከት በማነሳሳት ተጠርጥረዉ ለእስር ተዳርገዉ ነበር።
አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመዉ የኮማንድ ፓስት ጽህፈት ቤት  ተጠርጣሪወቹ በተለያዩ ዙሮች  የታሃድሶ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ወደህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ አደርጋለሁ ማለቱን የተለያዩ ዘገባወች ያመለክታሉ። በዚህም መሰረት ከ አንድ ወር በፊት ኮማንድ ፓስቱ ከ9 ሺህ በላይ ሰወችን ከእስር ነጻ ያደረገ ሲሆን በዛሬዉ እለት ደግሞ ሁለተኛዉን ዙር የተሃድሶ ስልጠና ተከታትለዋል የተባሉ ከ11 ሺህ በላይ ተጠርጣሪወች ከእስር መለቀቃቸዉን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ይፋ አድርጓል። የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኑነት ሃላፊ አቶ መሀመድ  ሰኢድ ለዶቼ ቨለ እንደገለጹት በሰንቀሌ ፣በይርጋለም፤በጦላይና በብር ሸለቆ የሚገኙ ተጠርጣሪወች በሀገሪቱ ህገመንግስትና በሌሎች ርእሶች ስልጠና ወስደዉ በዛሬዉ እለት ተለቀዋል።  
ስልጠናዉ በተለያየ መልኩ በሁከት ተሳትፈዋል የተባሉ ሰወችን የማስተማርና የማረም አላማ ብቻ ነበረዉ ያሉት ሃላፊዉ፤በመሆኑም በመንግስት ስራ ላይ እያሉ ተጠርጥረዉ በቁጥጥር ስር የዋሉ የመንግስት ሰራተኖችና ሌሎችም  ወደ መደበኛ የስራ ገበታቸዉ እንዲመለሱ ይደረጋል ሲሉ ሃላፊዉ ተናግረዋል። ተቃዉሞዉን ተከትሎ በሀገሪቱ የተደነገገዉን የ6 ወራት  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተቀመጠለት ጊዜ ይተናቀቃል ወይ ብለን ላነሳንላቸዉ ጥያቄ በህዝብና በመንግስት ወደፊት የሚወሰን መሆኑን አቶ መሃመድ ሰኢድ ገልጸዋል። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ከ1983 አ/ም ወዲህ በአይነቱ የተለዬ ነዉ በተባለዉ  ጸረ መንግስት እንቅስቃሴ ሳቢያ ሁከት በማነሳሳት ተጠርጥረዉ ከ22 ሺህ በላይ ሰወች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከእነዚህም ዉስጥ በሁለት ዙር ከ20 ሺህ በላይ ሰወች በኮማንድ ፓስቱ ከእስር ተለቀዋል።ቀሪወቹ ከ2 ሺህ በላይ ሰወች ግን ወደ ፊት ክስ ሊመሰረትባቸዉ እንደሚችል መረጃወች ያመለክታሉ።

ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ