1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኪንሻ-የተቃዉሞ ሠልፍ፤ ግጭትና ግድያ

ማክሰኞ፣ ጥር 12 2007

የኮንጎ ዴሚሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ዘመነ-ሥልጣናቸዉን ለማራዘም ማቀዳቸዉን በሚቃወሙ ሠልፈኞችና በፀጥታ አስከባሪዎች መካከል ትናንት የተጀመረዉ ግጭት ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1ENSz
Kongo Ausschreitungen in Kinshasa 19. Januar 2015
ምስል picture alliance/AA

የርዕሠ-ከተማ ኪንሻሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚመሯቸዉ ሠልፈኞች ፤ወደ ኪንሻሳ ዩኒቨርስቲ እና ወደ ሐገሪቱ ምክር ቤት አዳራሽ የሚወስዱ ጎዳናዎችን ለመዝጋት ሲሞክሩ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ተጋጭተዉ ሲያንስ 4፤ ሲበዛ ዘጠኝ ሰዉ ተግድሏል። መንግሥት የኪንሻሳ የኢንተርኔት አግልግሎትንና ጎዳናዎችን ዘግቷልም። ከዚሕ ቀደም ለሁለት ዘመነ-ሥልጣን የመሩት ካቢላ በመጪዉ የጎርጎሮሳዉያኑ 2016 በሚደረገዉ ምርጫ ለመወዳደር የሐገሪቱ ሕገ-መንግሥት አይፈቅድላቸዉም። ይሁንና ካቢላ ዘመነ ሥልጣናቸዉን ለማራዘም ከምርጫዉ በፊት የሕዝብ ቆጠራ ይደረግ የሚል ረቂቅ ሕግ-የሐገሪቱ ምክር ቤት እንዲያፀድቅ ጠይቀዋል። ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች የፕሬዝዳንቱን ዕቅድ «ሥልጣን ለማራዘም አዲስ ሥልት» ይሉታል። አሳዶ የተሠኘዉ የመብት ተማጋች ድርጅት ፕሬዝዳንት ዤን-ክላዉድ ካቴንደ አንዱ ናቸዉ።

Joseph Kabila Kabange 25.09.2013
ፕሬዝደንት ጆሴፍ ካቢላምስል picture-alliance/dpa

«የፕሬዝዳንት ካቢላን ዘመነ ሥልጣን ከ2016 በላይ ለማራዘም አዲስ ሥልት አግተዋል። የ2016ቱ ምርጫ እንዲደረግ የኮንጎ ሕዝብ ቁጥር መታወቅ አለበት የሚል ማሰበቢያ ሥልት ቀይሰዋል። ይሕ የሐገሪቱን ሕገ-መንግሥት የሚጥስ ነዉ።»

የኮንጎ መንግሥት፤ የኮንጎ ሕዝብ አንድነት የተሰኘዉን ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዤን-ክላዉድ ሙያንቦን አስሯል።ሙያንቦ የካቢላን አገዛዝ በመቃወም ካቢላ ከሚመሩት ገዢ ፓርቲ ወጥተዉ በቅርቡ ተቃዋሚዎችን የተቀላቀሉ ፖለቲከኛ ናቸዉ። ዘግይተዉ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የኪንሻሳን ማዘጋጃ ቤት በእሳት አጋይተዋል። በዚህ አጋጣሚም ከማዘጋጃ ቤቱ አጠገብ ከሚገኝ እስር ቤት በርካታ እስረኞች ማምለጣቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ