1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ካራጂች 40 ዓመት ተፈረደባቸዉ

ሐሙስ፣ መጋቢት 15 2008

የሰርቦቹ ፅንፈኛ ብሔረተኛ መሪ በ1995 ሴሬብሬንሳ በተባለችዉ ከተማ በሰርብ ሐይሎች እየተመረጡ በተገደሉት 8000 ሙስሊም ወንዶች ግድያም በዘር ማጥፋት ወንጀል ጥፋተኝነታቸዉ ተረጋግጧል

https://p.dw.com/p/1IJc6
ምስል Reuters

የቀድሞዉ የቦስኒያ ሰርቦች መሪ ራዶቫን ካራጂች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በፈፀሙት፤ ባስፈፀሙትና እንዲፈፀም ባዘዙት ወንጀል ባጠቃላይ የ40 ዓመት እስራት ተበየነባቸዉ።ዘ ሔግ ኔዘርላንድስ ዛሬ ያስቻለዉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ካራጂቺን እንደ ጎርጎሪያዉያኑ አቆጣጠር ከ1992 እስከ 1995 በተደረገዉ ጦርነት፤ ሰዎችን በማስገደል፤ ሰላማዊ ሰዎችን በማስጠቃት፤በማሰቃየት፤ ርዕሠ-ከተማ ሳርዬቮን በማስከበብና ሕዝብን በመፍጀት ወንጀሎች ተጠያቂ አድርጓቸዋል።የሰርቦቹ ፅንፈኛ ብሔረተኛ መሪ በ1995 ሴሬብሬንሳ በተባለችዉ ከተማ በሰርብ ሐይሎች እየተመረጡ በተገደሉት 8000 ሙስሊም ወንዶች ግድያም በዘር ማጥፋት ወንጀል ጥፋተኝነታቸዉ ተረጋግጧል።ይሁንና የቦስኒያ ሙስሊሞችንና ክሮቶችን በጅምላ በማጥፋት ወንጀል በተያዘባቸዉ ክስ ፍርድ ቤቱ አዛዉንቱን ፖለቲከኛ ተጠያቂ አላደረጋቸዉም።ካራጂች በአጠቃላይ ከተያዘባቸዉ አስራ-አንድ የወንጀል ጭብጥ በዘጠኙ ጥፋተኛ መሆናቸዉን ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አረጋግጧል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠብአዊ መብት ኮሚሽንና ሌሎች የመብት ተሟጋቾች ፍርዱን በመላዉ ዓለም ለሚገኙ ፅንፈኛ ብሔረተኛ መሪዎች የማስጠነቀቂያ ደወል ብለዉታል።በቦስኒያዉ ጦርነት ከ100 ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።አብዛኛዉ ሙስሊም ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ