1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ካይሮ፥ ስድስት ሰዎች በስቅላት ተቀጡ

እሑድ፣ ግንቦት 9 2007

የግብፅ ባለሥልጣናት ስድስት እስረኞችን ዛሬ በስቅላት መቅጣታቸው ተገለጠ። ወታደሮች ላይ ጥቃት አድርሳችኋል በሚል በግብጽ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ የተበየነባቸው ስድስቱ እስረኞች በስቅላት የተገደሉት መዲናይቱ ካይሮ በሚገኝ አንድ እሥር ቤት ውስጥ መኾኑን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/1FR5N
Ägypten Militärgericht Hinrichtung
ምስል Reuters/M. Abd El Ghany

በስቅላት የተቀጡት ስድስቱ እሥረኞች እራሱን «እስላማዊ መንግስት» እያለ ከሚጠራው ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት እና ሲናይ በረሃ ውስጥ ይንቀሳቀሳል የሚባልለት አንሣር ባይት ኧል ማቅዲስ ቡድን አባላት መኾናቸውም ተዘግቧል።

ስድስቱ ሰዎች የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሙርሲ እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር 2013 .. ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ አደረሱት በተባለው የፈንጂ ጥቃት የሞት ብይን ተላልፎባቸው ነበር።

የግብጽ ፍርድ ቤት የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲ እና ሌሎች 100 ተከሳሾች በጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር 2011 .. ግብጽ ውስጥ በወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ላይ ተቀስቅሶ በነበረው ተቃውሞ ወህኒ ቤት በመስበር በቀረበባቸው ክስ ትናንት ሞት እንደተፈረደባቸው አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። ኾኖም ብይኑ ገና አልፀናም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ