1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬንያ እና ፀረ አሸባብ ርምጃዋ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 10 2007

የኬንያ መንግሥት በጋሪሳ 148 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ሠራተኞች በአሸባብ ጥቃት ከተገደሉ በኋላ በዚሁ አሸባሪ ቡድን አንፃር የተለያዩ የበቀል ርምጃዎች ወስዷል። ይኸ ርምጃውም ከፍተኛ ተቃዉሞ ገጥሞታል።

https://p.dw.com/p/1FAHy
Kenia Garissa Universität Anschlag Kenias Präsident Uhuru Kenyatta äußert sich zu demAnschlag
ምስል picture-alliance/dpa/ZUMA Press

በዚሁ ርምጃው መሠረት፣ ከጥቂት ቀናት በፊት «ሐቂ አፍሪቃ» እና «ሙስሊም ለሰብአዊ መብት» የተባሉ የመብት ተሟጋች ሁለት ድርጅቶችን ዘግቷል። ይኸው አሸባሪነትን ለመታገል በሚል ሰበብ የወሰደው ርምጃው ይህን የመንግሥቱን ዓላማ ለማሳካቱ ጥረት አንዳጽም ፋይዳ እንደማይኖረው በርካታ የመብትና የሲቭል ማሕበረሰብ ድርጅቶች አስታውቀዋል። ድርጅቶቹ ባለፈው ሳምንት በራካታ የሶማልያውያን የሐዋላ ተቋማትን መዝጋቱን፣ ከዚህ በተጨማሪ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህፃሩ «ዩኤንኤችሲአር» የተባበሩት መንግሥታት በሰሜናዊ ኬንያ የሚገኘውን 400 ሺህ ሶማሌዎች የሚኖሩበትን የዳዳብ የስደተኞች መጠለያን በሶስት ወር ውስጥ እንዲዘጋ እና ስደተኞቹን ወደ ሃገራቸው እንዲመልስ መጠየቁምንም አውግዘውታል። የድርጅቱ የኬንያ ቃል አቀባይ ኢማኑኤል ንያቤራ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ«ዩኤንኤችሲአር»መረጃውን የሰማው እንደማንኛውም ሰው መሆኑን ተናግረዋል ።

Somalia Kämpfer der al-Shabaab in Mogadischu
ምስል M:Abdiwahab/AFP/Getty Image

« መጀመሪያ የምነግረህ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግሥት በኩል በይፋ ምንም ዓይነት ግንኙነት አልተደረገም። የደረሰን ነገር የለም። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር አስተያየት መስጠት የምንፈልገው በይፋ ግንኙነት ከተደረገ በኋላ ነው። መረጃው የደረሰን እንደማንኛው ሰው ነው። ምንም ዓይነት ነገር ቢደረግ የስደተኞቹ ፍላጎት እዲሟላና የመንግሥትም ስጋቶች እንዲወገዱ ከመንግሥት ጋር መወያየት ይኖርብናል። »

ኬንያ ስደተኞችን በግዳጅ የምታስወጣበት አድራጎት አሳሳቢ ሰብዓዊ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ያስጠነቀቀው የተመድ መስሪያ ቤት «ዩኤንኤችሲአር» የኬንያ መንግሥት ዉሳኔን እንዲያጤነዉ በማሳሰብ የኬንያውያንን እና የስደተኞቹን ደህንነት ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ የዳዳብ መጠለያ ጣቢያ ጥበቃን በማጠናከሩ ተግባር ላይ ከኬንያ መንግሥት ጋ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል። እርግጥ፣ በመዲናይቱ ናይሮቢ በሚገኘው የዌስትጌት የገበያ ማዕከል ላይ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጥቃት ተጥሎ 67ሰዎች ከተገደሉ በኋላ የኬንያ ፖለቲከኞች የዳዳብ መጠለያ ጣቢያ እንዲዘጋ በጠየቁበት ጊዜ በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉትን ለመመለስ ስምምነት መደረሱ ይታወሳል። ይሁናና፣ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት፣ ለስደተኞች ከለላ የመስጠት ኃላፊነት ያለባት ኬንያ ስደተኞችን በግዳጅ ማስወጣት እንደማትችል ድርጅቱ አሳስቦዋል።

የኬንያ መንግሥት በሀገሩ ምሥራቃዊ አካባቢ የሚገኘው የዳዳብ መጠለያ ለፅንፈኛው የአሸአብ ቡድን አባላት የመመልመያ ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ነው ሲል አስታውቋል።

Kenia Garissa Universität Anschlag Trauer
ምስል picture-alliance/dpa/D.Irungu

የተመድ መጠለያ ጣቢያውን በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ካልዘጋ ኬንያ ራሷ ርምጃ መውሰድ እንደምትጀምር በጽሑፍ አመልክታለች። ይህ፣ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች እንዳሉት፣ የኬንያ አመራር ከራሱ የገዢው ፓርቲ በኩል ላረፈበት ግፊት መንበርከኩን አሳይቶዋል። ከጋሪሳው ጥቃት በኋላ በኬንያ ምክር ቤት አብላጫውን መንበሮች የያዘው የገዢው ፓርቲ አንጃ መሪ አላን ዱዋል የስደተኞቹ ጣቢያ እንዲዘጋ ጠይቀዋል።

«በሰሜናዊ ኬንያ የሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለአሸባሪዎች ድርጅቶች አባላት ሥልጠና እና መመልያ ሆኖ ያገለግላል። በዚህም የተነሳ ስደተኞቹን ድንበር አሻግሮ ወደመጡበት ወደ ሶማልያ የመመለሻው ጊዜ አሁን ነው። የኬንያ ሕዝብ ከለላ ሊደረግለት ይገባል። »

የ148 ሰዎች ሕይወት ያጠፋው የጋሪሳ የአሸባሪዎች ጥቃት በኬንያውያኑ ዘንድ የፈጠረው ድንጋጤ አሁንም ገና እንዳልወጣላቸው የገለጹት በጥቃቱ የሞተችውን የወንድማቸውን ልጅ አስከሬን ከአንድ ሳምንት በኋላ ከናይሮቢ የወሰዱት ዴቪስ ዌኬሳ የጥቃቱ ሰለባዎቹ አሟሟት እጅግ ዘግናኝ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

« አስከሬኖቹ ያየ አሟሟታቸው በጣም አሳዛኝ መሆኑን ይገነዘባል። የወንድሜን ልጅ ለምሳሌ አንገቷን ቆርጠው ነው ከገደሏት በኋላ ዓይኖችዋን አውጥተው አቃጥለዋታል። »

ተመሳሳይ ጥቃት ይሰነዘራል የሚለው ስጋትም በጣም ከፍ ያለ መሆኑን ባለፈው የሳምንት መጨረሻ በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ ንዑስ ፍንዳታ በተሰማበት ጊዜ ተማሪዎቹ በጣም ተደናግጠው እንደነበር ነው የተማሪዎች ማህበር ሊቀ መንበር ኤቫንሰን ጂቶኖ ያስታወቀው።

Explosion an der Universität von Nairobi
ምስል picture-alliance/AP Photo/Azim

« በቀላል የቴክኒክ ብልሽት መብራት በጠፋበት ጊዜ የአሸባሪዎች ጥቃት መስሎዋቸው ትልቅ ፍርሀቻ ተፈጥሮ ነበር። »

የአሸባሪዎች ጥቃት የመሰላቸው ተማሪዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከአምስተኛ ፎቅ ዘለው ሲወጡ አንድ ሞቶዋል። 100 የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል።

የኬንያ መንግሥት በዚሁ በሕዝቡ ዘንድ የተስፋፋውን ፍርሀት እና ድንጋጤ ለማብቃት፣ እንዲሁም፣ በቂ ጥንቃቄ አላደረገም በሚል ለሚወቅሱት ምላሽ ይሆን ዘንድ በሽብርተኝነት አንፃር ጠንካራ ርምጃ ለመውሰድ አቅዷል። የርዳታ ድርጅቶች ግን ርምጃው በጥቃቱ በማይመለከtzኣቸ ታቸው ንጹሓን ትከሻ ላይ መሆን እንደሌለበት እያሳሰቡ ነው። ብዙዎቹ ስደተኞች ካለፉት ሀያ ዓመታት ወዲህ በመጠለያ ጣቢያው የሚኖሩ ወይም በዚያ የተወለዱ በመሆናቸው ወደ ሶማልያ ሊመለሱ እንደማይችሉ ነው ድርጅቱ ያመለከተው። ከዚህ ባለፈም ብዙው ገጠራማው የሶማልያ አካባቢ በአሸባብ ቁጥጥር ስር የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን ስደተኞቹን ወዴት እንዲሄዱ ነው የሚፈለገው ሲል ያጠያየቀው መስሪያ ቤቱ ይህን ያህል ሰው ባጭር ጊዜ ውስጥ ማመላለሱም የማይቻል መሆኑን ነው ያስረዳው።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ