1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኬንያ፤ ግድያና ዉዝግብ

ረቡዕ፣ ሰኔ 11 2006

የኬንያ መንግሥትም ፦ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በተደጋጋሚ እንዳሉት ለአሸባሪዎች ዛቻ ተንበርክኮ ጦሩን አያስወጣም።እና ለኬንያ-ሶማሊያ ዉስጥ የመዋጋት፤ኬንያ ዉስጥ የመጠቃት መወዛገቡ አዙሪት-ይቀጥላል።

https://p.dw.com/p/1CLaE
ምስል picture-alliance/AA

በኬንያ የጠረፍ ከተሞች ላይ ባለፉት ተከታታይ ቀናት የተፈፀመዉ ግድያ የሐገሪቱን ፖለቲከኞች እያወዛገበ ነዉ።ታጣቂዎች ምፔኬቶኒ እና ፖሮሞኮ በተባሉት የጠረፍ ከተሞች ባለፈዉ ዕሁድ እና ሰኞ ባደረሱት ጥቃት 65 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።ለግድያዉ የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ሐላፊነቱን ቢወስድም የሐገሪቱ ፕሬዝዳንት ግን ግድያዉን የፈፀሙት የሐገር ዉስጥ የፖለቲካ ሐይላት መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።ፕሬዝዳንቱ ትናንት የሰጡት መግለጫ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ሲያስቀይም፤ በፖለቲካ ተንኞች ዘንድ ደግሞ ጥርጣሬን ፍጥሯል።

የኬንያ-መንግሥት ሁለት የብሪታንያ ዜጎች መታገታቸዉን ለመበቀል ጦሩን ወደ ሶማሊያ ካዘመተ-እጎአ ከ2011 ወዲሕ ግጭት ትርምስ-የማያጣዉ የምሥራቅ አፍሪቃ የሠላም ደሴትነቷ አብቅቶ-ሠልፏን እንደ እና ከጎረቤቶቿ ጋር እንድታሳምር ግድ ብሏታል።

2011 ወዲሕ ከናይሮቢ-እስከ ሞባሳ፤ ከፖሊስ ጣቢያ እስከ-ገበያ አዳራሽ የሚገኙ አካካቢዎችን ላሸበረዉም ሆነ ከመሳጂዶች እስከ አብያተ ክርስቲያናት ለተፈፀመት ግድያዎች ተጠያቂዉ የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሻብብ መሆኑን የጠረጠረ፤ ያጠያየቀም የለም።ራሱ አሸባብም በተደጋጋሚ ሐላፊነቱን ወስዷል።

Kenia - Anschlag der al-Shabaab-Miliz
ምስል picture-alliance/dpa

ባለፈዉ ዕሁድ እና ሰኞም ሁለት የጠረፍ መንደሮችን ወርረዉ 67 ነዋሪዎችን የገደሉት የአሸባብ ታጣቂዎች መሆናቸዉን የቅርቡም-የሩቁም ታዛቢ አልተጠራጠረም።ግድያዉ የተፈፀመበት ግዛት ምክትል አገረገዢ ኤሪክ ሙጎም የመጀመሪያዉ ግድያ እንደተሰማ ይሕንኑ አረጋግጠዉ ነበር።

«እነዚያ ሰዎች የወሰደቱን እርምጃ ሥናየዉ አሸባብ መፈፀሙን እንረዳለን።አነሱም አሻባብ መሆናቸዉን አልሸሸጉም።ሥለዚሕ ከሠለቦችም የምንገነዘበዉ፤ ከሁሉም በላይ የዘር ማጥፋቱ የተፈፀመበትን ሁኔታ ሥንመለከት አሸባብ መሆኑን እንረዳለን።»

አሸባብም ጥቃቱን ማድረሱን አስታዉቋል።ቡድኑ «የሶማሊያን ሕዝብን ይገድላል፤ ያሰቃያል» ያለዉ የኬንያ ጦር ከሶማሊያ እስካልወጣ ድረስ ጥቃቱን ለመቀጠልም ዝቷል።ፕሬዝዳንት ኡሑሩ ኬንያታ ግን የታዛቢዎችን እምነት፤ የባለሥልጣናቸዉን መግለጫ፤ የአሸባብንም ማረጋጋጪያ ዉድቅ ነዉ ያደረጉት።

ኬንያታ ትናንት በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር እንዳሉት ሰልሳ-ሰባቱን ሰዎች የገደሉት የፖለቲካ አላማቸዉን በሐይል ለማስፈፀም የሚያሴሩ የሐገር ዉስጥ ፖለቲከኞች ናቸዉ።ጥቃቱ የታሰበበት፤የተቀነባበረና እዚያ አካባቢ የሚኖረዉን ሕዝብ አፈናቅሎ ሥፍራዉን ለመቆጣጠር ያለመ ለመሆኑ መንግሥታቸዉ በቂ መረጃ አለዉ።ኬንያታ የሐገር ዉስጥ የፖለቲካ መረብ ያሉትን ቡድን በሥም አልጠቀሱም።

አይ ኤስ ኤስ በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተመራማሪ አንድሪዉስ አታ አሳሞሕ እንደሚሉት የኬንያታ ዳርዳርታ ጥቃቱ ሲደጋገም ብሔራዊ እርቅ እንዲደረግ የጠየቁትን የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስር የራይላ ኦዲንጋን ፓርቲ ለመወንጀል ነዉ። ኮርድን።

«የመንግሥት ባለሥልጣናት ጣታቸዉን በኮርድ ላይ የሚቀስሩት።ኮርድ ደግሞ ከተፈፀመዉ ራሱን እርቋል።እንደሚመስለኝ የመንግሥት ትረካ የመነጨዉ የብሔራዊ እርቅ-ድርድር እንዲደረግ ራይላ ኦንዲንጋ ካደረጉት ጥሪ እና ግፊት።ሥለዚሕ መንግሥት የሚለዉን ለማመን ትንሽ ከባድ ነዉ።»

Symbolbild Kenia Militär Befreiung norwegische Geiseln
ምስል AP

አሳሞሐ እንደሚያምኑት አምና በተደረገዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኬንያታ የተሸነፉት ኦዲንጋ የሚመሩት ፓርቲ የተሐድሶና የዴሞክራሲ ቅንጅት (ኮርድ) የብሔራዊ እርቅ ድርድር እንዲደረግ መግፋቱን የፕሬዝዳንት ኬንያታ መንግሥት አይፈልገዉም።የመንግሥት ባለሥልጣናት ለበቀደሙ ጥቃት ጣታተቸዉን በኮርድ ላይ የሚቀስሩትም ፓርቲዉን በሕዝቡ ዘንድ ለማስጠላት ነዉ።

በሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ተቆጣጣሪ ቡድን የቀድሞ ሐላፊ ማት ብራይደንም ሥለ በቀደሙ ጥቃት ፕሬዝዳንት ኬንያታ ካሉት ይልቅ-አሸባብ ያለዉን ያምናሉ።«አሸባብ ያላደረሰዉን ጥቃት አደረስኩ ብሎ አያዉቅም።»-እንደ ብራይደን።

ኮርድ የብሔራዊ እርቅ-ዉይይት እንደጠራ-ሁሉ የጥቃቱ መደጋገም ያሰጋቸዉ ሌሎች ኬንያዉያን መንግሥታቸዉ ጦሩን ከሶማሊያ አስወጥቶብንገላገልስ» አይነት ሐሳብ በሕዝቡ ዘንድ እያሰረፁ ነዉ።አሳሞሐ ግን ኬንያ ጦሯን ማስወጣትዋ ለሠላም ዋስትና አይሆንም ባይ ናቸዉ።

«ብዙ ሰዎች፤ ኬንያ የወሰደችዉ ርምጃ ለአፀፋዉ ጥቃት ካጋለጣት ጦሯን ለምን አታስወጣም የሚል ስሜት አላቸዉ።መልስ ያላገኙለት ግን፤ ኬኒያ ጦሯን ብታስወጣ በአሸባብ በኩል ተኩስ አቁም ይደረጋል-ወይ ለሚለዉ ጥያቄ ነዉ።»

የኬንያ መንግሥትም ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በተደጋጋሚ እንዳሉት ለአሸባሪዎች ዛቻ ተንበርክኮ ጦሩን አያስወጣም።እና ለኬንያ-ሶማሊያ ዉስጥ የመዋጋት፤ኬንያ ዉስጥ የመጠቃት መወዛገቡ አዙሪት-ይቀጥላል።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ