1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 ክፍፍል የሚታይበት የአፍሪቃ ህብረት

ማክሰኞ፣ ጥር 23 2009

የአፍሪቃ ህብረት አዲስ የኮሚሽን ፕሬዚደንት መርጧል፣ ሞሮኮንም እንደገና በአባልነት ተቀብሏል። ይህ ሁሉ ግን ህብረቱ በወቅቱ የሚገኝበትን ከባድ ቀውስ ሊሸፍንለት አይችልም።

https://p.dw.com/p/2Wixd
Afrikanische Union Marokko nach 33 Jahren wieder aufgenommen
ምስል picture alliance/AA/Minasse Wondimu Hailu

die Afrikanische Union ist gespalten wie nie - - MP3-Stereo

ከ33 ዓመት በፊት የያኔዉ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሞሮኮ  ግዛቷ አድርጋ ለምትመለከተው አወዛጋቢው ምዕራባዊ ሰሃራ ነፃነት እውቅና የሰጠበትን ውሳኔ በመቃወም ነበር በራባት የሚገኘው መንግሥት ድርጅቱን ለቆ የወጣው። መጀመሪያ ሲያዩት ሞሮኮ አሁን ህብረቱን መቀላቀሏ ጥሩ ዜና ነው። ሞሮኮ በፖለቲካው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ፣ በኤኮኖሚ ጥንካሬዋም በአህጉሩ ስድስተኛዋ ሃብታም  ሃገር ናት።  እና ይህንኑ የንጉሥ መሀመድ ሳድሳዊን  ሃብት በማሰብ  ሞሮኮ ህብረቱን ትቀላቀል ለሚለው ጥያቄ ትናንት የአዎንታ ድምፃቸውን የሰጡት ጥቂት አፍሪቃውያን መሪዎች አልነበሩም ። ምክንያቱም ሟቹ የሊቢያ መሪ ሞአመር ኤል ጋዳፊ ለህብረቱ የሚያደርጉት ድጎማ ከተቋረጠ ወዲህ 70% በጀቱን ከአባል ሃገራት የሚያገኘው ድርጅት ትልቅ ፊናንስ ቀውስ ውስጥ ነው የሚገኘው።  
ይሁንና፣ የሞሮኮ ጉዳይ ትልቅ ችግር ይዞ ነው የመጣው። ለምዕራባዊ ሰሐራ ነፃነት የሚታገለው ፖሊሳርዮ ብቻ አልነበረም ህብረቱን መልሳ መቀላቀሏን አጥብቆ የተቃወመው። ፖሊሳርዮ በዚሁ አቋሙ ናይጀሪያ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪቃን የመሳሰሉ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሃገራትን፣ በተለይ ደግሞ በአፍሪቃ ህብረት ውስጥ ትልቅ ሚና የምትጫወተውን የሞሮኮ ጎረቤት አልጀሪያን ድጋፍ አግኝቷል። በድምፅ አሰጣጡ ላይ ከፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ አባል ሃገራት መካከል ብዙዎቹ ራባትን ነበር የደገፉት። ዓለም አቀፉን የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት ለቆ በመውጣት አለመውጣት ጥያቄ ላይ  ህብረቱ ተከፋፍሎ በሚገኝበት ባሁኑ ጊዜ፣ በሞሮኮ ደጋፊዎች እና በሳህራውያን፣ በፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ፣ በሰሜን እና በደቡብ፣ በምሥራቅ እና በምዕራብ መካከል ልዩነት መፈጠሩ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል። ያለፉት ዓመታት ፖለቲካዊ ሂደቶች እንዳሳዩት፣ ሞሮኮ ምዕራባዊ ሰሃራ ከህብረቱ እንድትወጣ መጠየቋ አይቀርም፣ ምንም እንኳን ይህ በህብረቱ አንድነት አሉታዊ ተፅዕኖ ቢኖረውም።   በሞሮኮ አባልነት ጥያቄ ላይ በተካሄደው ድምፅ አሰጣጥ፣ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ምርጫ እና በዙር የሚያዘው የህብረቱ ፕሬዚደንትነት ስልጣን በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሃገራት በመያዙ ሰበብ፣በህብረቱ መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግ የተነቃቃው ጥረት በአዲስ አበባው ጉባዔ የተፈፈለገውን ትኩረት ሳያገኝ ቀርቷል። 
 እርግጥ፣ ሰዎች የርዋንዳ ፈላጭ ቆራጭ መሪ ፖል ካጋሜን መውደድ የለባቸውም። ይሁንና፣ በህብረቱ ትዕዛዝ ያቀረቡት የተሃድሶ ለውጥ እቅዳቸው፣ ፊናንሱን  ብቻ  ሳይሆን፣ እስካሁን ከሞላ ጎደል ውጤት አልባ ሆኖ የቆየውን ድርጅት መዋቅራዊ ለውጦችን  በተመለከተም ጥሩ ሀሳቦችን መያዙን ሊክድ አይችልም። የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ባጠቃላይ ስልጣን አልባ ነው በሚባልበት ባሁኑ ጊዜ ለውጥ ማድረጉ አስፈላጊ ነው።  ምክንያቱም ዋነኛ የሚባሉ ውሳኔዎች ሁሉ የሚወሰዱት በአባል ሃገራት ርዕሳነ ብሔር እና መራሕያነ መንግሥት ነው። ከነዚህ ውሳኔዎች መካከል የዋነኛው የሰላም እና ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ኮሚሽነርን መሾም ለምሳሌ አንዱ ነው። ከዚህ ሌላም ያካባቢ ኤኮኖሚ ድርጅቶች እና የህብረቱ ማዕከላይ አካላት ስልጣን ተደጋጋሚ መሆን ህብረቱን ግልጽ ውሳኔ ከመውሰድ አስተጓጉሎታል ወይም ቀውስ ውስጥ ከቶታል። ህብረቱ በዓመት ለስራ ማካሄጃ፣ ለሰላም ተልዕኮ ጭምር የሚያስፈልገውን 1,2 ቢልዮን ዩኤስ ዶላር ራሱ ማቅረብ የሚችልበት ስልትም ተገቢውን ትኩረት ማግኘት ያለበት ነጥብ ነው። ይሁንና፣ ከ53 አባል ሃገራት መካከል ለዚሁ አዲስ ስልት መዋጮ የሚከፍሉት አምስት ሃገራት ብቻ መሆናቸው ገሀዱ ተራርቀው መገኘታቸውን ያሳያል። 
ተሰናባቿ የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ  በአዲስ አበባ የህብረቱ መሪዎች ጉባዔ መክፈቻ ላይ ባሰሙት ንግግር የአፍሪቃን አንድነት እና ትብብር የሚፈታተን ጊዜ መከሰቱን ገልጸዋል። ዙማ በዚሁ አነጋገራቸው የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የሰባት ሙስሊም ሃገራት ተወላጆች ወደዩኤስ አሜሪካ እንዳይገቡ ባለፈው ሳምንት ያሳለፉት እገዳ እና ለአፍሪቃ የሚኖረውን መዘዝ ማለታቸው ነበር። ይሁን እንጂ፣ ሉድገር ሻዶምስኪ እንዳለው፣ ይህ አባባላቸው ያን ያህል አንድነት የማይታይበት የአፍሪቃ ህብረት በወቅቱ የሚገኝበትን ሁኔታ በይበልጥ የሚጠቁም ሆኖ ሊወሰድ ይችላል።

Afrikanische Union Marokko nach 33 Jahren wieder aufgenommen
ምስል picture alliance/AA/Minasse Wondimu Hailu


ሉድገር ሻዶምስኪ/አርያም ተክሌ
ነጋሽ መሀመድ